>
5:08 pm - Monday February 22, 5694

እንቅልፍ አልባ ሌሊቶችና የምስጋና ህዝበ ትይዕንት: ባህር ዳር!! (ከተማ ስንታየሁ አየለ)

እንቅልፍ አልባ ሌሊቶችና የምስጋና ህዝበ ትይዕንት: ባህር ዳር!!
ከተማ ስንታየሁ አየለ
የሰኔ 16 አአ ሰልፍ አና የደረሰው አደጋ፣ የሰሞኑ ዝናብ በፕሮጀክቴ ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ፣  ድካም•••፣  ተደማምረው ስሜቴን ረብሸውታል። ሁኔታው ከባህር ዳር ዩንቨርስቲ የምህንድስና ት/ት ክፍል ሁለተኛ ዲግሪውን ለሚቀበለው ታናሽ ወንድሜነ ምርቃት ላይ ለመገኘት ፣ በማግስቱም   የምስጋና  ህዝበ ትዕይንቱ ላይ ለመሳተፍ መልካም አጋጣሚን ፈጥሮልኛል። እንኳነ ደበረኝ! አልቀርም!!!
ከወቅቱ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ  የትራንስፖርት እጥረት ቢከሰትም ህፃኑ ጨርቆስ እረድቶኛል።
ሰኔ 21,2010 ፣ ሀሙስ ንጋት ላይ (10:30 ) “የድሮው” አብዩት/መስቀል አደባባይ፣ የአሁኑ “አንድነት/መደመር አደባባይ”( Unity Square) እንቅልፌን መስዋት አድርጌ  ከአባይ ባስ ጋር መንገዴን ጀምሬአለሁ።
መነሻየ የአብዪት ቦታ ነው፣ መንገዴም በጊወን ወንዝ መፋሰሻ፣ ከውሀ ልኩ የመሬት ንጣፍ በታች( below sea level) 150 ሜትር ጥልቀት ላይ የሚገኘውን ድልድይ ለመሻገር ጠመዝማዛ እና አስቸጋሪውን የአባይ በረሀ ቁልቁለት በመውረድ ላይ ነኝ። በጥፋታቸው ጊዜ አዳምና ሄዋን የት እንዳሉ የጠየቀበት ነጎድጓዳው የአምላክ ድምፅ  የተራሮችን ሰነሰለት እየሰነጠቀ  ሲያስተጋባ ይሰማኛል።
” አዳም ወዴት አለህ? …ወዴት አለህ..?.. አለህ.. ለህ…? (ዘፍጥረት ምዕ 3÷9 )
አልፎ አልፎም በየቦታው የተፈነገሉ መኪኖች የጉዳት ሁኔታ እያየሁ፣ ከተሳፋሪዎችም እየሰማሁ ከእንቅልፌ ጋር እታገላለሁ  ።
“ይኸ ሲኖ ትራክ ድንጋይ ተሸክሞ ሲከንፍ አህያ ገብታበት ኖሮ ኸዚህ ገደል ተዶለ!! ” አለ አንዱ አጎቴ አራት እግሮቹን ወደ ላይ አንጨብሮ ከቋጥኙ ጎን በጀርባው የተኛን ገልባጭ እየጠቆመ! !
እጂጋየሁ ሽባባው ግን አደጋውን እና ቁልቁለቱን  እንዳላየች እና እንዳልሰማች ሆና አባቷ ፣አረኞች፣ አጎቶቿ፣ በሬዎች ሳይቀሩ በናፍቆት አብሰልስለዋት ኖሮ አያና ገዳሙን ታቀልጠዋለች።
አያና ደማሙ፣ አያና ደማሙ፣
አባይ ወዲያ ማዶ ትንሽ ግራር በቅላ፣
ልቤን ወሰደችው ከነስሩ ነቅላ።
•••አባየ ናፈቀኘ የከብቶቹ ጌታ፣ ሲባርክ ሲመርቅ
ናፈቀኝ ያያ ታዴ ሆዴ
የሽመል አጓራ አይችልም ገላዪ፣
የኔ ሆድ አሌዋ ና ቁም ከኋላዪ!!
•••አያ ና ደማሙ አያና ደማሙ፣ አያና ደማሙ••••
አውቶብሱ ረጂሙን የጊወን ወንዝ በእርጋታ ተሻግሮ የደጀንን ዳገት ጀምረናል።
ፍቅር አዲስም ከጂጂ ተቀብላ ሳምንቱ በጎጃሙ “አሽከር” ፍቅር እንደተለከፈች የሚስረቀረቀው ድምጿ ያሳብቃል።
“ደግሞ በዚህ ሳምንት ደግሞ በዚህ ሰሞን፣ ደግሞ በዚህ ሰሞን፣
የአባይ ማዶ ፍቅር ጀመረኝ ማሽሞንሞን ጀመረኝ  ማሽሞንሞን።
ማፍቀር መቸ ገዶ መውደድ መቸ ገዶ መውደድ መቸ ገዶ፣
አባይ መሻገሩን ዋናውን ማን ለምዶ፣ ዋናውን ማን ለምዶ።•••••••••••••••••••
በ9 ሰዓት ውቢቷ ባህርዳር ገብቻለሁ። ከዛሬ 12 አመት በፊት የማውቃት ከተማ ተቀየረችብኝ። ያኔ በመንጋ ከሚጎርፉት ሳይክሎች ፋንታ የበውቀቱ ስዩም ባጃጆች በደቦ በደቦ ቆመዋል። ሌሎቹም ተሳፋሪወችን “አዝለው” እንደበረሮ ከወዲያ ወዲህ ይራወጣሉ።
ከሁሉም ጎልቶ የሚታየው ግን ሶስቱ ህብረቀለማት ናቸው። ሳር ቅጠሉ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ነው። ዘፍጥረት በ3ቱ ቀለማት እንቁጣጣሽ መስሏል፣ይገዛል፣
ይሸጣል!! ገሚሱ  ይለካል፣ ይመርጣል፣ ያውለበልባል፣ አቅፎ ይስማል!! በጀርባው፣ በክንዱ፣ በግንባሩ፣ ያላሰረ ግብረ ሰው የለም።
“•••አዋጅ አዋጅ የቡዳ መድሀኒት ተገኝቷል!”
“ኮከብ የሌለበት ባንዲራ መቶ መቶ ብር•••!” “•••ኮከብ ለጨለማ ጊዜ ብቻ ነው ይልሀል እዚ ጋ••! ” ፣ 
“በብርሀን ዘመን ኮከብ አያስፈልግም ብለናል•••!”፣  
“የጂቦችን አዳኝ አነበሳ ፎቶ የያዘችዋ ቲሸርት በ150 ብር•••! “
ይህ ሁሉ የነፃነት አዋጂ ከዘምባባዎቹ ስር ይበሰራል። በባህር ዳር ጎዳናዎች!፣ ከዲፖ እስከ ጊወርጊስ!፣ ከፓፒረስ እስከ ፔዳ -አባይ ማዶ!፣ ከአዝዋ እስከ ኖክ  ሁሉም ጎዳናዎች የአብዮት ገበያ ማዕከላት ሆነዋል።
ቅዳሜ ሰኔ 23, 2010! ባህር ዳር ዩንቨርስቲ በኢንጂነሪንግ ሁለተኛ ዲግሪውን የሚቀበለው ወንድሜን ለማስመረቅ በጥዋቱ ተነስቻለሁ።  ዛሬ በባህር ዳር ጎዳናዎች በተጨማሪ ህብረ ቀለማት አሸብርቃለች። እቅፍ አበባዎች፣ ተመራቂዎች የለበሱት ገዋን፣ የተመራቂ ቤተሰቦች የተዋቡበት የሀበሻ ቀሚስ።
ዊዝደም አደባባይ ፋውንቴን ተከፍቶ በሁሉም አቅጣጫ  የሚታየው የካሜራ ብልጭታ እና የተመራቂዎች ፈገግታ ልብን ይሰነጥቃል።
2:00 ሰአት! አሁን የምረቃ ስነ ስርአቱን ለመታደም ወደ ስታዲየም በሰልፍ ዘልቀን ገብተናል።
ባ/ዳ ዩንቨርስቲ ስታዲየም ዙሪያው በሙሉ ያጌጠው ኮኮብ በሌለው ሰንደቅ ነው። እዚህም ያው ነው!!  አጃዓይብ ነው!! ፍፁም እንግዳ ነገር ሆነብኝ። “የታደለ ትውልድ በሸጋ ሰንደቅ ታጂቦ ተመረቀ!!! ” አልሁ ውስጤ በቅናት መንፈስ እየተናጠ። ምንም ማድረግ አይቻልም!! እጀን በአፌ ላይ እንደጫንኩ፣  የምርቃቱ ስነስርአት ተጠናቀቀና ከወንድሜ ጋር ወደ ቤት ተመለስን።
ቀን 8:40_የምርቃተቱን ድግስ ጠረጌ ስወጣ ከተማዋ የበለጠ በህዝብ ማእበል ተጥለቅልቃለች። ሙሉአለም አዳራሽ ፊትለፊት በተሰለፉ የጃምቦና ቁርጥ ቤቶች የተከፈተው የቴዲ እና ሌሎች ባህላዊ ሙዚቃ ድምፅ  የኦዞን ጣሪያ ሳይቀር ይበሳሉ። የትዕይንተ ህዝብ ዋዜማ፣ የህትመት ውጤቶች ሽያጭ ማስታወቂያ ፣ ጭፈራ፣ የጎል ጩኸት፣ የሰልፍ አስተባባሪዎች የመኪና ላይ ድምፅ ማስታወቂያ፣ ድ••ብ••ል••ቅ••ል••ቅ•••!!
“ምን አለ አብይ ምን አለ•••!? አሀሀ•• ሀገሬን ለጂብ•• አሀሀ ሀገሬን ለጂብ•• አሀሀ•• አልሰጥም አለ!! ምን አለ አብይ ምን አለ?! አሀሀ  •••” ቱ•••ቱ•••ቱ••ቱ••!!
ተሽከርካሪወች ጥሩንባቸውን እያንባረቁ፣ የአደጋ ምልክት መብራት እያሳዩ፣ በሰንደቁ ታጂበው በዋና ዋና መስመሮች በመንጋ ይዞራሉ። ጩኸቱ፣ ጭፈራው፣ ደስታው፣ መዝሙሩ፣ ሽለላው፣ አሽሙሩ ••• የቀረ ነገር የለም።
ይህ ሁሉ ሲሆን የፀጥታ አካላት በቡድን ቦታ ቦታቸውን ይዘው የግል ጨዋታቸውን ይጠስቃሉ።  አንቡላንሶችም አልፈው አልፈው ይታያሉ።
—–
 እሁድ! ሰኔ 24, 2010፣ ጠዋት 12:00 ሰዓት፣ የሰልፉ ቀን!!! እፎይ! ልብ አንጠልጣይ `ረ••ጂ••ሙ••• ሌሊት ነጋ!!
ከቤቱ የቀረ የባህር ዳር ህዝብ ይኖራል ለማለት  አልደፍርም!! ሰው እንደ ጉንዳን ወደ ስታዲየም ይግተለተላል፣ የህዝብ ማእበል የከተማዋን አየር ሲያናውጠው ለአይን ያታክታል፣ ጎዳናወች በሰንደቅ ጭጋግ ተሸፍነዋል፣ ህንፃወቹን መለየት የማይታሰብ ነው፣ ሱቆችም በሰንደቅ ብርድልብስ ተጀቡነው ነው ሌሊቱን ያሳለፉት!! ህፃን፣ ሽማግሌ፣ ወጣት፣ ሴት፣ወንድ፣ ቄስ፣ ሸክ፣ሸፍ፣ •••ሁሉም በነቂስ ወጥቷል!! ሁሉም ፈታሽ፣ ሁሉም ተፈታሽ፣ ሁሉም ተባባሪ••• ሆኖ ስታዲየም በር ገባን። እግዜብሄር ያክብራቸውና የሰልፉ አስተባባሪዎች ለኔ እና ለታማኘ በየነ ሰው ቀለል ባለበት መስመር እንድናልፍ ፈቀዱልን።  ታማኝ በየነ በጥቁር ቶክሲዶ ሱፉ ላይ የገነት በር ሊከፍት የሚችል ሀይል ያለውን ፈገግታ ደርቦ ወደተዘጋጀለት የVIP  ቦታ እያመራ ለሰልፈኛው ሰላምታ በመስጠት ትእይንተ ህዝቡን ትኩረት ሳበ!!
ግባ በለው ታማኝን ግባ በለው••አሀሀ••• ግባ በለው ታማኝን ግባ በለው•••!” እንዴ!!
ተቀወጠ ስላችሁ?!
•••የቴዲ አፍሮ የእጂ ስራ፣ የበዛብህ “ጧፍ” “ሰብልዬ” ጣዕመ ዜማ ሲያነጠንጥ ደግሞ የመድረኩን ልኬተ ሙቀት ጨመረችው!! ሁሉም በያለበት ሆኖ ይሄን እስክስክስታ ያራግፈዋል?! •••
“•••ያዝ እንግዲህ•••!! ኧሽ እሽ•••ኧሽ እሽ•••ኧሽ እሽ •••ኧረ ተው ተው•••!!!”
የቴዲ ስራዎች እነ ኢትዮጵያ፣ ያስተሰርያል፣ ቴወድሮስ በየተራ ቀረቡ። የፋሲል ደመወዝ አረሱት(እቴቴ) ተከትሎ ሲቀርብ ግን ስቴዲየሙ አበደ!! ሰው አቅሉን ሳተ!!
3:00 ሰዓት ሆኗል! ድንገት ሳይታሰብ በስቴዲየሙ በስተምስራቅ አንዲት ሄሊኮፍተር ዝቅ ብላ  ቄጠማ እየበተነች ከውስጧ ያሉ ሰዎችም ሰላምታ እየሰጡ ወደታች ለመሬት 6 ሜትር እስኪቀራት ዝቅ ብላ በስቴዲየሙ ውስጥ ተዘዋወረች፣ ከፍተኛ የሰው መጨናነቅ ስለነበረ ግን ማረፍ አልቻለችም። ተመልሳ ወደ ላይ ተሳበች። የመድረክ መሪው ሄሊኮፍተሯ ማረፍ እንድትችል ቦታውን ክፍት እንዲሆን ደጋግመው ቢማፀኑም አልተቻለም፣ ከሰው ኮቲ የተረፈ ቦታ የት አለና!!?
ሌላ ትይዕንት!! 500 ሜትር በ6ሜትር ሰንደቅ በኳስ ሜዳው ዙሪያ ባለው የመሮጫ መም(lane) ተጠመጠመ። የጩኸት፣ የደስታ ሲቃ ጣሪያ ጥግ ደርሶ ሲመለስ ሌላ ድራማ!
 ቀጥሏል!! አንድ የቀድሞውን ሰራዊት የክብር ልብስ የለበሰ፣ ሌላ የኢትዮጵያን ሰራተኞች የሚወክል የስራ ልብስ የለበሰ፣  እና በግራ እጁ ደብተር የያዘ የኢትዮጵያን ተማሪወች ሊወክል የሚችል ለግላጋ ወጣት (ሶስቱም የበፊቱን original ሰንደቅ አላማ እያውለበለቡ) በወታደራዊ አጀብ አለፉ።  ያው የደስታ ስካር! ያው ህልም የሚመስል እውነት፣ ያው  ጩኸት፣ ያው እምባ •••!!
የመድረክ መሪው በጠንካራ ግን ወርቃማ እና ጥልቅ ድምፁ ጣልቃ ገብቶ ሞገዱን ለሁለት ገመሰው። የነ ገዱ፣ ደመቀ፣ ሽባባው፣ አሳምነው፣ እና እማዋይሽ እንደተገኙ እና ተራ በተራ “ንግግር” እንደሚያደርጉ አበሰረ! ጎበዝ የመድረክ መሪ ነው፣ ድንቅ ችሎታ!!
ገ••ዱ! ገ••ዱ !ገ••ዱ! ገ••ዱ••• ! ማእበሉ ድንገት ተናወጠ። እንዴት ልግለፀው!?  ኧረ ተውኝ ጓደኞቸ?!!!
ገዱ አንዳርጋቸው: የመድረኩን መንበረ ዙፋን ሲቆጣጠረው ስቴዲየሙ ለቅፅበት ቀልቡን ሰብሰብ አድርጎ ነበር፣ ተመልሶ ሊከንፍ!!
“•••የአማራ ህዝብ በሀገራችን ጠንካራ መንግስት እንዲመሰረት•• ፣ ታሪክ እንዳይበላሽና፣ ነፃነት እንዳይገፈፍ ከጥንት ጀምሮ የሰራ እና የታገለ ••ባለታሪክ •••ለተራበ ፈትፍቶ አጉራሽ፣ ለተጠማ ጠልቆ የማይበቃው፣ለወደደው ማር እና ለጠላው ኮሶ ነው። ••••••ኢትዮጵያ ንፁህ ደም ሳይሆን ነፁህ ፍቅር ይፈስባት ዘንድ ያስፈልጋል•••፣ ፍቅር ያስፈልጋል•••፣ •••ስንፋቀር የይቅርታና የምህረት ዝናብ ይዘንባል•••፣አንድ እንሁን••፣ ••• አንድ ባለመሆናችን [እስካሁን] የጂብ እራት ሆንን ቆይተናል፣ ••• ••• [አሁን ግን] አንድ መሆናችን የእግር እሳት የሆነባቸው••• የአሮጌው ዘመን ቁማርተኞች ከእግር እግራችን ስር አየተከታተሉ ሰላማችንን ፣ ለማወክ እየጣሩ  ነው••• ፣ አይሳካላቸውም እንጂ•••! ፣••የጥይት ድምፅ የሚያደነቁራቸው ከተሞቻችን [የሰላምና ፍቅር አየር እንዲነፍስ] ስንቅ ያስፈልገናል •••አንድነት፣ ፍቅርና ተስፋ•••ይህም የሚጀምረው [ከእያንዳንዳችን ቤት ነውና]••• የደጃችንን  ቆሻሻ እናፅዳ•••ከዚህ በኋላ የአማራ ህዝብ አንገቱን ደፍቶ እና ተሸማቆ የሚኖርበት ሳይሆን ቀና ብሎ በኩራት የሚራመድበት ጊዜ ይሆናል•••!!”
ኧረ የመድሀኒያለም ያለህ?!! ኧረ እመብርሀን!?
እድምተኛው በገዱ ንግግር መሀል መሳጭ አረፍተ ነገሮችን እንዲደገሙ (እንደሙዚቃ) ፣ ይደገም••• ይደገም••• እያለ ይጮህ ነበር።
ምክትል ጠ/ሚር አቶ ደመቀ መኮነንም በተራቸው ከወትሮው ደፈር ባለ መልኩ ጠንካራ ንግግር አድርገዋል፣ ለችግሮች ፈጥነው መልስ እንደሚሰጡ፣ ለዚህም በአማራው ብሂል ” የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ” በማለት በተዘዋዋሪ በልጃቸው ምለው ተገዝተዋል።
ጀነራል አሳምነው ፅጌም የእስራኤሏ ራሄል በፈርኦኖች የተፈፀመባት ፅንሷን አስወርደው ከጭቃ ጋር አቡክታ ለፒራሚድ መገንቢያ እንድታደርግ መገደዷን ጠቅሰው ኢትዮጵያ ውስጥም ተመሳሳይ ድርጊት በወያኔ እስር ቤቶች እንደተፈፀመ በምሳሌ ተናገሩ። ግን  ሙሴ እስራኤላውያንን ነፃ እንዳወጣ ሁሉ ኢትዮጵያንም አብይ ነፃ ማውጣቱን እርግጠኛ ናቸው።
አቤት በራስ መተማመን! ፣ አቤት እርጋታ፣ አቤት መድረክ  አያያዝ!! ወቸ ጉድ!! የዚህኛው ደግሞ የተለየ ነው።
ወ/ሮ እማዋይሽም ደስ ብሏቸዋል፣ ከአሳሪወቿ ጎን መድረክ ላይ ተቀምጠዋል።  ነገር ግን  አንድ ያልተመለሰላቸው  ጥያቄ አለ!  የሽግግር መንግስት ይካሄዳል ወይስ የኢሀዲግ መዋቅር ይቀጥላል? ••• በለው!! የሴት ሀይለኛ! ነበልባል! ብረት!! በስማም!!
ደመቀ ደግሞ ገልመጥ እያደረገ ያያታል••• !!!
ደክሞናል አቦ!!! ፕሮግራሙ ባይጠናቀቅም ወደቤት መመለስ ጀመርን!!
ደህና ሁኑ፣ ጓደኞቸ!! 
ከተማ ስንታየሁ። 
ከጊወን  ወንዝ ማዶ!!
Filed in: Amharic