>

ጨካኙ የማዕከላዊ ገራፊ  ከዶ/ር አብይ አሕመድ ጋር አሜሪካ ሊመጣ ነው!  (አቻምየለህ ታምሩ)

ጨካኙ የማዕከላዊ ገራፊ  ከዶ/ር አብይ አሕመድ ጋር አሜሪካ ሊመጣ ነው! 
አቻምየለህ ታምሩ
መለስ አለም   ባሁኑ ወቅት የወያኔ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ ነው። መለስ  በአገዛዙ ውስጥ  ስራ የጀመረው የወያኔ ልሳን  የፋና ሬዲዮ ሪፖርተር በመሆን ነበር። ከዚያም በቤተ ወያኔ እድገት አግኝቶ  በኬንያ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ውስጥ ዲፕሎማት ሆኖ ኬንያ በሚገኙ የኢትዮጵያ ስደተኞች ላይ ስቃይ፣ አፈናና ግድያ  ሲያካሂድ ነበር።
በመጋቢት ወር ፍርድ ቤት የቀረበው ጋዜጠኛ ሰይፉ አለሙ  ማዕከላዊ በሚባለው የወያኔ  ሲኦል ውስጥ  አረመኔዎቹ የትግራይ መርማሪዎች ጭካኔና ስቃይ እንደፈጸሙበት ተናግሯል። ጋዜጠኛ ሰይፉን በማዕከላዊ  ገላውን ይተለትሉና   «ጉራጌ ሌብነት እንጂ ፖለቲካን የት ያውቃል» እያሉ ምራቃቸውን በመትፋት  ይመትሩት  ከነበሩ  የትግራይ መርማሪዎች መካከል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃለ አቀባይ  የሆነው አቶ መለሰ አለም አንዱ ነው። ይህንን  እውነት  መለስ ስቃይ የፈጸመበት ጋዜጠኛ ሰይፉ ለፍርድ ቤቱ  ስሙን ጠቅሶ ተናግሯል።
መለስ አለም እስረኛ ሲደባደብ በጋዜጠኛ ሰይፉና በሌሎች የማዕከላዊ የሲኦል ቤት ግፉዓን ላይ ያካሄደው አረመኔነት የመጀመሪያው አይደለም። ወያኔና ሻዕብያ የበታችነትና የባልይነት ልባቸውን አሳብጦት  ጦርነት ባካሄዱበት ወቅት የፋና ጋዜጠኛ ሆኖ  ለሪፖርት ወደ  ጾረና ግንባር  «ለስራ» ተልኮ ነበር።
በዚህ ግንባርም  የሻዕብያ ምርኮኞችን አግኝቶ  ሪፖርት በሚሰራበት ወቅት ቃለ መጠይቅ ሲያደርግላቸው ምርኮኞቹ  አለም እንዲሰማ  የማይፈልገውን መልስ ስለሰጡት የያዘውን ማይክራፎን  መሬት ላይ ጥሎ የጦር እስረኞችን[POW] መደባደብ ሲጀምር አብረውት የነበሩት  ሰዎች እንዳስጣሉት  በወቅቱ አብሮት ለስራ ወደ ቦታው አቅንቶ  የነበረው ጋዜጠኛ መኩሪያ ወልደ ሚካኤል ምስክርነቱን ሰጥቷል። አሁን የት እንዳለ ባላውቅም የቀድሞው የኢቲቪ ጋዜጠኛ  የነበረው  መኩሪያ ወልደ  ሚካኤል እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የኢሳት  ጋዜጠኛ ነበር።
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አሕመድ  የፌዴረል ማረሚያ ቤት የሚባለውን የትግራይ መርማሪዎች  የማሰቃያ ቤት የበላይ ገራፊዎችን ማንሳቱን ነግሮናል። ይህ ጥሩ እርምጃ ቢሆንም  ግፈኞቹ ለፍርድ ቀርበው የእጃቸውን እስካላገኙ ድረስ ግን እነሱን  ከቦታቸው ማንሳት  ብቻ ፍትሕ አይደለም።
በአብይ አሕመድ መንግሥት ውስጥ አሁንም ገራፊዎች ቁልፍ የአገዛዙን ስልጣን እንደያዙ አሉ። አንደኛውና ዋነኛው ገራፊ  የወያኔ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ የሆነው  መለስ አለም  ነው። መለስ አለም  አብይ አሕመድን ተከትሎ አሜሪካን ሊመጣም እንደሆነ እየሰማን ነው። ይህ የጭካኔ አባትና ያሰቃያቸው የሕሊና እስረኞች እነ ሰይፉ አለሙ ሳይቀሩ የፈጸመባቸውን ጭካኔ ጠባሳቸውን ለፍርድ ቤት ቀርበው   ምስክርነታቸውን  በሰጡበት ሁኔታ  ገራፊውን  መለስን  የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ አድርጎ ማቆየቱ በማረሚያ ቤት የስቃይ ኃላፊዎች ላይ የተወሰደውን የሚበረታታ እርምጃ የሚያጎድል ነው።
መለስ የሚባለው ገራፊ ከውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይነቱ ተወግዶ በሕሊና እስረኞች ላይ ለፈጸመው የጭካኔ ተግባር  የእጁን እስካላገኘ ድረስ  በግፉዓን ዘንድ የአብይ አሕመድ መንግሥትም  የሰቆቃ  ፈጻሚዎች አገዛዝ  ከመሆን አይዘልም። «መደመር» ለሚፈልጉም ከነ መለስ  ጋር መደመር አስቸጋሪ ነው።
Filed in: Amharic