>

የትግራይ ሕዝብ ልጓሙን ይበጥስ!! (ዳንኤል ተፈራ)

የትግራይ ሕዝብ ልጓሙን ይበጥስ!!
ዳንኤል ተፈራ
ሐምሌ 7 ትግራይ ሰላማዊ ሰልፍ ታደርጋለች እየተባለ ነው፡፡ እሰይ ታድርግ፡፡ ትተንፍስ፡፡ ይህንን ኩሩ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሕዝብ አክቲቪስት ነን የሚሉት፣ ተቃዋሚ ነን የሚሉት እና ‹‹የትግራይ ሕዝብ እና ህወሃት አንድ ነው›› እያለ የሚምለው ያረጀው የህወሃት ቡድን ግንባር ፈጥረው ከሌሎች ወንድሞቹ በመነጠል በስሙ የበሉትን አራጣ ማወራረጃ እያደረጉት ነው፡፡ ግራና ቀኝ ተናጠቁት እኮ!! ፈርዶበት፡፡
እንደ ድሮ ህፃን ‹‹ጭራቁን እንዳልጠራው!›› እያሉ የራሳቸውን ምኞት እና ጉጉት እንዲሁም ዕዳ አብሯቸው እንዲሸከም ያልማሱት ጉድጓድ የለም፡፡
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ሰላም፣ ፍቅር እና አንድነት በተሰበከበት የባለፉት 3 ወራት እንኩዋን የትግራይን ሕዝብ ከሌሎች ወንድሞቹ ለመነጠል የሄዱበት ርቀት እጅግ አስተዛዛቢ ነው፡፡ አሸማቃቂ ነው፡፡ ሰላሙን ጦርነትና ማት አድርገው ሲሰብኩት ስቅቅ የማይላቸው፣ ሁልጊዜ ችግርና ስጋት እንዳለ የሚሰብኩ ቆሞቀር ፖለቲከኞቹን አንቅሮ መትፋትና አፉ ውስጥ ወሽቀው እንዳይናገር የሚጎትቱበትን ልጓም በጣጥሶ በመጣል ከወንድሞቹ ጋር መደመር ለዛሬ የማይለው ጉዳይ መሆን አለበት፡፡
ችጋር ጠሪ እና ጦር ሰባቂ ልጆቹን መቆንጠጥ ይገባዋል፡፡ እነሱ እንደሁ ይሉኝታቸውን ሸጠው የበሉ ናቸው፡፡ ስለዚህ በስሙ የሚቸረችሩትን ዞር በሉልኝ ማለት አለበት ባይ ነኝ፡፡
እናም በሰልፉ የትግራይ ህዝብ ለለውጥ ያለውን ዝግጁነት የሚያረጋግጥበት መድረክ ይሆናል ብየ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ስላነበባችሁኝ አመሰግናለሁ!!!
Filed in: Amharic