>

"ግንቡን በማፍረስ ድልድዩን መገንባት"ዶ/ር አብይን ለመቀበል የተቋቋመው ኮሚቴ በአባላትና በአወቃቀሩ ላይ ማስተካከያ አደረገ!!! (ብርሀነ መዋ)

“ግንቡን በማፍረስ ድልድዩን መገንባት”
ዶ/ር አብይን ለመቀበል የተቋቋመው ኮሚቴ በአባላትና በአወቃቀሩ ላይ ማስተካከያ አደረገ!!!
ብርሀነ መዋ
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በአሜሪካ የሚያደርጉትን የሥራ ጉብኝት
የዋሸንግተን ዲሲ አስተባባሪ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በአሜሪካ የሚያደርጉትን የሥራ ጉብኝት ለማመቻቸት በዋሽግተን ዲሲና በሎስ አንጀለስ ከተሞች ኮሚቴዎች ተዋቅረው ሥራ መጀመራቸው ይታወቃል፡፡
 በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢፌዲሪ
ኤምባሲ አስተባባሪነት የተዋቀረው የዋሽንተግን ዲሲ አስተባባሪ ኮሚቴ ሥራውን ማከናወን ከጀመረ ከአንድ ወር በላይ ሆኖታል፡፡
ዘመኑ የመደመር በመሆኑ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ሊያካትት በሚያስችል ሁኔታ ከተለያዩ ማኅበረሰቦች፣
እምነቶች፣ የፖለቲካ አመለካከቶች፣ ጾታዎች፣ ቡድኖችና ድርጅቶች በራስ ተነሣሽነት የመጡትን ሁሉ በማካተት ሲሠራ ቆይቷል፡፡
ዋና ዓላማው “ግንቡን በማፍረስ ድልድዩን መገንባት” ስለሆነ፡፡
ይህ ሂደት አዲስ በመሆኑ የሚያጋጥመን ፈተናም አዲስ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በነበረው አለመተዋወቅና አለመቀራረብ የተነሣ የተለያዩ ኢትዮጵያውያንን ሊወክሉ የሚችሉ አካላትን በሚገባ ለማወቅ ችግር ያጋጥማል፡፡
መቀራረቡ እስኪፈጠር ጊዜያት ያልፋሉ፡፡ በግለሰቦች መካተትና ባለመካተት የሚቀርቡ ሐሳቦችን ለማጥራትም የራሱን ጊዜ ይፈልጋል፡፡ ይህን ፈተና ለመወጣትና ሥራውን በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ለማከናወን እንዲቻል ባለፈው ሰኔ 29 ቀን 2010 ዓ.ም በዋሽግተን ዲሲ የኢፌዲሪ ኤምባሲ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡
የጋዜጣ መግለጫውን ተከትሎ የተለያዩ ኢትዮጵያውያን በሂደቱ እየተደመሩ ለመሳተፍና የዚህ ታሪካዊ ሂደት አካል ለመሆን ተነሣሽነታቸው ጨምሯል፡፡
ከየአቅጣጫውም ልዩ ልዩ አካላት የዝግጅቱ አካል ለመሆን ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡ በሌላ በኩል
ደግሞ በኮሚቴው አባላት፣ በኮሚቴው አደረጃጀትና አወካከል ላይ ልዩ ልዩ ቅሬታዎችና ገንቢ አስተያየቶች ተሠንዝረዋል፡፡የሚቀርቡት አስተያቶችና ቅሬታዎችም ለተሻለ ውጤት መሆኑን እንረዳለን፡፡ አንድ ሥራ ፍጹም የሚሆነው በሂደት ነው፡፡
በጎውን እያጎለበቱና ስሕተቱን እያረሙ በመሄድ፡፡ የአንድ ነገር በይፋ መገለጥ የሚጠቅመውም ለማረሚያ የሚሆን ሐሳብና መንገድ ለማግኘት ነው፡፡ የጋዜጣዊ መግለጫው አንዱ ዓላማም ይህ ነበር፡፡ በመሆኑም ከተለያዩ ወገኖች የተሰጡትን ሐሳቦች በማካተት፣ ጥያቄዎችን በመቀበል፣ አሠራሮችን በመውሰድ ለተሻለ አሠራር የምንጠቀምባቸው ይሆናል፡፡
1. የተሰጡትን የማስተካከያ ሐሳቦችን በመቀበልም የጠቅላይ ሚኒስትሩን የለውጥ አጀንዳና በኢትዮጸያ የሚካሄደውን ለውጥ ለማገዝ በኮሚቴ አባላትና በአወቃቀሩ ላይ ማስተካከያና ማረሚያ ተደርጓል፡፡ ይህም ሂደቱን ቀናና የተሻለ ለማድረግ እንዲረዳ ነው፡፡
2. ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመቀበል የቀረን ጊዜ አጭር በመሆኑ መሳተፍ ያለባቸው ሁሉ እንዲሳተፉ፣ ሐሳብ ያላቸው ወገኖች ሁሉ ኮሚቴውን ለማገዝ የበኩላቸውን እንዲወጡ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
3 በዋሸንግተን ዲሲ እ.አ.አ ጁላይ 28/ 2018 ዓ.ም. በኮንቬንሸን ማእከል ህዝባዊ ስብሰባ በነፃ የተጠራ ሲሆን ለሁሉም ክፍት ነው።
በስብሰባው ለመሳተፍ የሚሸጥ ትኬት የለም፡፡
Filed in: Amharic