>
5:13 pm - Sunday April 18, 6032

ስማኝማ አንት … (ዘመድኩን በቀለ )

ስማኝማ አንት …
“ጠማማና አመንዝራ ትውልድ “
ዘመድኩን በቀለ 
~ ፈርዶብኝ መንጋውን ለመመስል አልታደልኩም። ከምር ይሄ ፍርጃ ነው። እውነቱ ግን ብቻዬንም ቢሆን ከእውነቴ ጋር እስከሞት ለመታመን መዘጋጀቴን ማረጋገጤ ነው።
ዛሬ ጦማሬን የጥላሁን ገሰሰን ዘፈን ሪሚኪስ በማድረግ በዘፈን ነው መጀመር የማረኝ። ያዝ እንግዲህ ማነህ ባለማሲንቆ ተቀበልልኝማ !
ያዋከቡት ነገር ምዕራፍ አያገኝም
ፍቅሬ ፍቅር በዝቷል፣
ዐቢይ ዐቢይ በዝቷል፣
ለማ ለማ በዝቷል፣
ገዱ ገዱ በዝቷል፣
ሻእቢያ ሸእቢያ በዝቷል፣
ዶላር ዶላር በዝቷል፣
አረብ አረብ በዝቷል፣ እኔ አለማረኝም።
ከስምንት መቶ ሺህ በላይ የሚሆኑ የጌዲኦ ነገድ አባላት ከኦሮምያ ክልል ተፈናቅለው በደቡብ ከረልል አውላላ ሜዳላይ ፈስሰው በዝናብ፣ በውርጭ፣ በበረዶ፣ በረሃብና በጥም በበሽታም ጭምር በመሰቃየት ላይ ይገኛሉ።
ከቤኒሻንጉል ክልል የተፈናቀሉ የዐማራ ነገድ አባላት ዛሬ በባህርዳር መፍሰሳቸው እየተነገረ ነው። የዐማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትም ዛሬ በባህርዳር ስብሰባውን ጀምሯል። ዐማራው ደግሞ ተፈናቅሎ በብርድና በዚህ የክረምት ዝናብ እየተደበደበ ከክልሉ ምክር ቤት በራፍ ላይ መፍትሄ ቢሰጡኝ ብሎ ፈስሷል። መፋጠጥ ብቻ።
ሌሎች ኢትዮጵያውያን ደግሞ በጠሚዶኮ ዐቢይ አህመድና በኢሳይያስ አፈውርቂ ፍቅር እብድ ብለው አቅላቸውን ስተው ጨርቃቸውን አውልቀው የሚሆኑትን እያሳጣቸው ነው። ሀገሬው በአስመራ ፍቅር ወድቋል። ክርክሩ ሁሉ የአውሮፕላን ትኬቱ ተወደደ ይቀነስልን ። አስመራን፣ ምጽዋን ዐይተን እንምጣ እንጂ ከዚያ በኋላ ብሞትም አይቆጨኝ  ባይ ብቻ ሆኗል። የቴሌ የአስመራ ታሪፍም ከሙከጡሪ እኩል ይሁንልን ባዩም ቀላል አይደለም።
የኢትዮጵያ ችግር ፈጣሪዎች ህውሓትና የህውሓት ፈጣሪ የሆነው አባቱ ሻአቢያ መሆናቸውን ዘንግተው ብዙዎች አሁንም ዳግም ለሻአቢያ ኢትዮጵያን ያተራምስ ዘንድ በሩን  ወለል አድርገው እየከፈቱለት ይገኛሉ። ኤርትራ በድጋሚ በዓለም የቡና አቅራቢ ሀገራት ሊስት ውስጥ በ4 ተኝነት ልትሰለፍልህ ነው። ለዚሁ ሲባል ከአሁኑ የጌዲኦ ህዝብ ከአካባቢው በኦሮሞ እንዲጸዳ እየተደረገ ነው የሚሉ አሉ። አዲስ አበቤ ሆኖ የአስመራን ሴት ለመተኛት እንቅልፍ ያጣውን ኢትዮጵያዊ አመንዝራ ቤት ይቁጠረው። የፋሲል ከነማ አስመራ ሄጄ ከኤርትራ ቡድን ጋር ኳስ ካልተጫወትኩ በፕሪምየር ሊጉ የምቀጥል አይመስለኝም የሚል መንፈስ ያለው ደብዳቤ ወደ አሰይመራ ለመላክ የጠሚዶኮን ከአስመራ መውጣት እንኳን አልጠበቀም።
በሌላ በኩል ለዐማራም ለኢትዮጵያም በምእራቡ በኩል የጥፋት ደመና አንዧቧል። ባለተጻፈና ባልተነገረ ህግ በሱዳን በኩል ያለውን የኢትዮጵያ ድንበር መከላከያ ሠራዊቱ እንዳይጠብቀወ በመደረጉ ምክንያት የፈረደበት የዐማራ ገበሬ እስከ አፍንጫው ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ከታጠቀ የሱዳን ሠራዊት ጋር እንዲዋጋ ተፈርዶበታል። የዐማራ ህዝብ ግብር እየገበረ ደሞዝ የሚከፍለው መከላከያ ሠራዊት የት እንደገባ ኤታማዦር ሹሙ ጄነራል ሰዐረ መኮንን ብቻ ናቸው የሚያውቁት። ዐማራ ሆይ ተበልተሃል።
ለማንኛውም ለጊዜው ሁሉም የጠሚዶኮ ዐቢይ ደጋፊ በመሆን ያልተመዘገቡ የኢህአዴግ ደጋፊዎች ሆነዋል። ጠሚዶኮ ድርጅታችን ኢህአዴግ እንዲሉ ያው ሁሉም ኢህአዴግ ሆነዋል። እስከአሁን ድረስ እግር የቆረጡ፣ ቶርቸር የፈጸሙ፣ ነፍስ ያጠፉ የኢህአዴግ አባላት ” በመደመር ” ሰበብ ለፍርድ አለልቀረቡም።
77 ቢልየን ብር፣ 10 እና 5 ቢልየን የዚያች ደኻ ሀገር አንጡራ ሀብት የዘረፉ ግለሰቦች ” መደመር ” ዋስትና ሆኗቸው እንደፈለጉ ዘና ብለው የሚኖሩባት ሀገር ተፈጥሮላቸው በሸነና እያሉ ዘና ብለው ይኖራሉ።
በስመ ተቃዋሚ ኢትዮጵያ እንዲገቡ የተፈቀደላቸው የፖለቲካ ኃይሎች እስከ አሁን ምርጫ ቦርድ ሄዶ የተመዘገበ የለም። ኢትዮጵያን ካለፈረስን እረፍት ብሎ ነገር የለንም የሉት የለንደኑ ሰውዬም ቀይ ምንጣፍ ተነጥፎላቸው በቦሌ በኩል ከገቡ በኋላ የት እንደደረሱ እስከአሁን የታወቀ ነገር የለም። ኢትዮጵያን የማፍረስ ፕሮጀክታቸውን ይዘው። ደምቢዶሎ ይሁኑ፣ አጋሮ፣ ከሚሴ ይሁኑ ወሊሶ የታወቀ ነገር የለም።
በቅርቡ የህግ የበላይነት ድራሿ ይጠፋል። በኦሮሚያ ኦህዴድና ኦነግ ይጠዛጠዛሉ፣ ሶማሌ ኦሮሞን አሁንም ይገርፋል፣ ዐማራ ከሱዳንና ከህውሓት ጋር ጦርነት መግጠሙ አይቀሬ ነው። የዐማራ ገበሬ ጦርነት ከተጀመረ የውጊያ አድማሱ ይሰፋበታል።
ህውሓት ብቻውን አይሆንም። የመከላከያ ሠራዊቱ ለህውሓት ነው። የሱዳን ጦር ለህውሓት ነው። ሻአቢያ ድንበር ስለተከፈተለት ለልጁ ህውሓት ነው የሚያግዘው። ኤርትራ ውስጥ በስመ የትግራይ ተቃዋሚነት ይንቀሳቀስ የነበረውና የፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ልዩ ጠባቂ የነበረው ደምሂት የተባለው ጦር በወልቃይትና በራያ በኩል ጭራሽ ከነመሳሪያው ሊሰፍር ነው እየተባለ ነው እናም መጪው ጊዜ ለዐማራም ለኢትዮጵያም ብሩህ አይመስለኝም።
ቆም ብሎ ነገሮችን በሰከነ መንገድ ለማየት የሚሞክር ሰው ጠፍቷል። አንድስ እንኳ ኧረ ይኼ ነገር በምን የህግ አግባብ ነው እየሄደ ያለው ብሎ በድፍረት የሚጠይቅ ሰው ጠፍቷል። እርቅ የሚባለው ነገርም የሆዱን በሆዱ ቂሙን ሁሉም በጉያው ይዞና ተሸክሞ ትከሻ በመሳሳም ነገሮችን አለባብሶ እያለፈው ነው። እንደ መንጋው ያለማሰብ መብቴ ነው።
ያዋከቡት ነገር ምዕራፍ አያገኝም
ፍቅሬ ፍቅር በዝቷል፣
ዐቢይ ዐቢይ በዝቷል፣
ለማ ለማ በዝቷል፣
ገዱ ገዱ በዝቷል፣
ሻአቢያ ሸአቢያ በዝቷል፣
ዶላር ዶላር በዝቷል፣
አረብ አረብ በዝቷል፣ እኔ አለማረኝም።
” አንተ አመንዝራና ጠማማ ትውልድ ሆይ ” ለማንኛውም ከሆቴልና ከምግብ ወጪ ውጪ ስምንት ሺህ የኢትዮጵያ ብር ለአውሮፕላን የደርሶ መልስ ትኬት ከፍለህ ከአስመራ ሴት ጋር ለመተኛት ከመጣደፍህ በፊት፣ በስምንት ብር ሜዳ ላይ ለፈሰሱት የጌዲኦ ህጻናት ለረሃባቸው ማስታገሻ ዳቦ ግዛላቸው። አንተ አለቅላቂ፣ አዳማቂ፣ እዩኝ እዩኝ ባይ !  ያልበላህን የምታክ ፎከቴያም ባዶ ሆድህን ምጽዋን ከመመኘትህ በፊት ባህርዳር ጣና ሀይቅ ሥር የፈሰሱትን የዐማራ ነገድ አባላት ወገኖችህን ሄደህ ጎብኝ። መፍትሄም ይሰጧቸው ዘንድ ታገል።
መቼም በአስመራ ፍቅር የሰከረ ህዝብ ባለበት ሀገር እኔን የሚሰድበኝ እንጂ የሚሰማኝ ይኖራል ብዬ አይደለም ይኽን መቸክቸኬ። የቤት አልጋ የውጭ ቀጋ የሆነ ህዝብም፣ መንግሥትም በበዛበት ዘመን ነገራችንም፣ ንግግራችንም ባይሰማም ደግሞም ለታሪክ ይቀመጥ ዘንድ ከመጻፍ አንቦዝንም።
የአስመራው መከፈት የሚጠቅመው ለሻአቢያና ለህውሓት ብቻ ነው። ለኢትዮጵያውያን 05 ሳንቲም ጠብ የሚል ነገር የለውም። የሆነ የተደገሰልንማ ድግስ አለ። ነገርየውን መለየት ነው ያቃተኝ እንጂ ሽታውማ ይሸተኛል። ቁሌቱ ያውደኛል፣ ያስነጥሰኛል። በርበሬ ይሁን ሚጥሚጣ፣ ቀይ ወጥ ይሁን ዶሮወጥ፣ ብቻ ቁሌቱ ይሸታል። ይሰነፍጣል፣ ያስነጥሰኛል።
እናም ወገኔ ፍቅሩ ፣ እርቁ ፣ እንዳለ ሆኖ ከአስመራ በፊት ለአዲስ አበባ፣ ከኤርትራ በፊት ቅድሚያ ለኢትዮጵያ እንስጥ። ተናግሬያለሁ።
ያዋከቡት ነገር ምዕራፍ አያገኝም
ፍቅሬ ፍቅር በዝቷል፣
ዐቢይ ዐቢይ በዝቷል፣
ለማ ለማ በዝቷል፣
ገዱ ገዱ በዝቷል፣
ሻአቢያ ሸአቢያ በዝቷል፣
ዶላር ዶላር በዝቷል፣
አረብ አረብ በዝቷል፣ እኔ አለማረኝም።
#ማስታወሻ | ~ እኔ ዘመዴ ለውጡን አልቃወምም፣ እንቅፋትም አልሆንም፤ አይደለሁምም። ነገር ግን ለውጡን በጥንቃቄና በጎሪጥ የማየት ሕገ መንግሥታዊም ሕገ ተፈጥሮም እንዳለኝ አሳምሬ አውቃለሁ። እናም በነጻ የማሰብ፣ የማሰላሰል፣ የመናገርና የመጻፍ መብቴን መቶ በመቶ ሳይሸራረፍ በነጻነት እጠቀምበታለሁ። ይኸው ነው።
ሻሎም !  ሰላም !
ሐምሌ 5/2010 ዓም
ከራየን ወንዝ ዳር።
Filed in: Amharic