>

እንዲመጣ ለምንፈልገው ለውጥ ሲባል ወጣቱ ከመንጋ ዳኝነት መራቅ ይኖርበታል፤  (ያሬድ ጥበቡ)

እንዲመጣ ለምንፈልገው ለውጥ ሲባል
ወጣቱ ከመንጋ ዳኝነት መራቅ ይኖርበታል፤
ያሬድ ጥበቡ
የወዳጄ የበረከት ስምኦን መኪና መቃጠሉና ሰነዶች መሰረቃቸው በስዩም ተሾመ ተዘግቦ አነበብኩ ። ባለፈው ሳምንት በረከት ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሰ ለውጡን ለማኮላሸት የሚያደርገውን ሩጫ አቁሞ በፈቃዱ ከፓርቲ መሪነቱ እንዲወርድ ጠይቄ ነበር ። ለጥያቄዬም መነሻ የሆነኝ፣ ከማምነው ምንጭ በረከት የቅማንትን ጉዳይ ለማጦዝ እየሠራ መሆኑን ሰምቼ ስለነበር ነው ። ዛሬ በደረሰበት ጥቃት ደስተኛ አይደለሁም ። ይህ የለውጥ ሂደት ከግቡ ሊደርስ የሚችለው፣ በሥርአቱ ውስጥ የቆዩት ጎምቱዎች ፍርሃት እስካልተሰማቸውና፣ ያጋበሱትን ንብረትና የሠሩትን ወንጀል የሚከታተልና የሚያሳድድ ስሜት እስከሌለና ሂሳብ የማወራረድ ግፊት እስከሌለ ድረስ ነው። እንደ በረከትና ህላዌ ያሉት ጎምቱዎች ደግሞ ይቅርታ መጠየቅ የሚያስገድዳቸው  ወንጀል ሊኖር ቢችልም፣ ንብረት በህገወጥ መንገድ በማጋበስና በማሸሽ ስማቸው ሲነሳ አልሰማሁም። አንድም ነባሩን ሥርአት ለማስቀጠል የሚደክሙት በእርጅና ዘመን ለመጦሪያ የሚሆን ሃብት ያልያዙና፣ ለውጡ ድንገት ከተፍ ያለባቸው በመሆኑ ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ። በእርጅና ዘመናቸው ተንከባክቦ ሊይዛቸው፣ ሊያሳክማቸው ይችል የነበረው ሥርአት ድንገት ሲፈርስ ባዶነት ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ። በቂ ያሸሹና በወዳጅ ዘመዶቻቸው ሚሊዮኖች ያሸጉ ላይበረግጉ፣ ወደ ሌብነቱ እጅጌያቸውን ጠቅልለው ያልገቡበት የነበረከት አይነት ሰዎች ደግሞ ቀቢፀተስፋ ላይ ሊወድቁ ይችላሉ። ይህን በማመዛዘን ህዝቡ በተለይ ወጣቱ ከዚህ አይነት የ(ሞብ ጀስቲስ) የመንጋ ዳኝነት መራቅ ይኖርበታል። ይህ ለውጥ በህዝብ ትግል ብቻ የተገኘ አይደለም። ሥርአቱ ውስጥም ያሉ ሰዎች ያልተናነሰ፣ ምናልባትም ያመዘነ አስተዋፅኦ ማድረጋቸው መረሳት የለበትም። የኦቦ ለማን የግንቦት 20 ንግግር ማስታወስ ያስፈልጋል። ዛሬ በነበረከት ላይ የተቃጣው አመፅ ነገ በነለማ ላይም የማይመጣበት ሎጂክ ስለሌለ፣ ለውጡ በሙሉ አቅሙ እንዳይጓዝና ዳተኛ እንዲሆን ሊያደርግ ስለሚችል፣ የለውጡ ሃይሎች ሁሉ እነዚህን መሰል የመንጋ ተግባራት ማውገዝ ይኖርብናል። የፍትህ ሥርአቱም ህግና ሥርአት ለማስጠበቅ፣ የህን በመሰሉ ሥርአተአልበኞች ላይ ጠበቅ ያለ እፍምጃ መውሰድ ይኖርበታል። ይህ ለውጥ ከእሸትነት ወደ አዝመራነት መብሰል የሚችለው፣ ህግና ሥርአት እስከተከበረ ድረስ ነው።

Filed in: Amharic