>
5:13 pm - Thursday April 19, 1387

ብዙ አስቸጋሪና ፈታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩም ከ5 አመት በኋላ ከህዝቤ ጋር ለመገናኘት በመቻሌ ፈጣሪን አመሰግናለሁ!!!  ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)

ብዙ አስቸጋሪና ፈታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩም ከ5 አመት በኋላ ከህዝቤ ጋር ለመገናኘት በመቻሌ ፈጣሪን አመሰግናለሁ!!! 
ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)
በመጀመሪያ ለኢትዮጵያውያንና ለኤርትራውያን በሙሉ እንኳን ለዚህ ታሪካዊ የፍቅር ቀን አደረሳችሁ። “ፍቅር የሕግ ሁሉ ፍፃሜ ነው” እንደሚለው መፅሃፉ ዛሬም መለያየት ሳይገባን ተለያይተን፣ ጦርነት ሳያስፈልገን ተዋግተን፣ መጣላት ሳያስፈልገን ተኳርፈን በከንቱ ያባከናቸውን ወርቃማ ጊዜያት፣ የገበርናቸውን ወድ የሰው ልጆች ሕይወት፣ ያደቀቅናቸውን የሀገር ምጣኔ ሀብትና ለስደት የዳረግናቸውን የሃገር ልጆች ምን ያህል እንደጎዱንና ዋጋ እንዳስከፈሉን የምንረዳበት ጊዜው ደርሶ እንደገና የፍቅር ቃልኪዳናችን አድሰን፣ የሚያምርብንና የምንኮራበትን ኅብረታችንን ወደቀድሞ ቦታው መልሰን በአዲስ ራዕይና በአዲስ ፍቅር መጭውን ዘመናችንን ለመዘመን ስላበቃን ለክቡር እግዚአብሔር ምስጋና ይድረሰው። ለዚችም ታሪካዊ ቀን እንድንበቃ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱት ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፣ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፍወርቂና የሁለቱ ሃገራት አንድ ሕዝቦችም ምድስጋና ይድረሳችሁ።
ምንም እንኳን በስራ ምክንያት በሰሜን አሜሪካ ለወራት የነበረኝን የሙዚቃ ኮንሰርት አጠናቅቄ በትናንትናው ምሽት ወደሃገሬ የተመለስኩና በዛሬው ታሪካዊ መርሃግብር በተጋባዥ እንግድነት በመጠራቴ በደስታ የተገኘሁ ቢሆንም፤ በአዳራሹ መገኘቴን አውቃችሁ ለሰጣችሁኝ ምስጋናና ላሳያችሁኝ ፍቅር እጅግ አድርጌ አመሰግለናሁ። በዕለቱ ምንም መድረክ ላይ ወጥቼ ለመዝፈንም ሆነ ንግግር ለማድረግ ያልተዘጋጀሁ ቢሆንም የመድረክ መሪውና ታዳሚው ድምፄን እንዳሰማ የቀረበልኝን የአክብሮት ጥሪ ተቀብዬ ከነበርኩበት የቪአይፒ ቦታ ወደ ውጭ በመውጣት ወደ መድረክ ጀርባ (Backstage) ከፀጥታ አስከባሪዎች ጋር ያመራን ቢሆንም የመድረኩ ጀርባ በር ከውስጥ የተቆለፈ በመሆኑ የፀጥታ አስከባሪዎቹ ወደ 20 ደቂቃ ያህል 5 በሮችን ለማስከፈት ያደረጉት ጥረት ባለመሳካቱ እንደገና ወደ አዳራሹ በዋናው በር በመግባት በሕዝብ መሃል አቋርጬ ለመሄድ ረዘም ያለ ጊዜ ወስዶብኛል። የሙዚቃ ባንዱ ጋርም አስቀድሜ ልምምድ ያላደረግሁ ስለሆነ መድረክ ላይም ተለማምዶ ሙዚቃ ለማቅረብ በቂ ጊዜ ባለመኖሩ ለማከብራችሁ ወገኖቼ የተለያዩ ስራዎቼን ለማቅረብ አልቻልኩም። ቢሆንም አሁንም በድጋሜ ከ 5 አመታት በኋላ ከምወደው ሕዝቤ ጋር በአዲስ አበባ በእንደዚህ አይነት መድረክ አይን ለአይን ለመተያየት በመቻሌ ፈጣሪን አመሰግናለሁ።
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር። 
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ኤርትራን ይባርክ።
ፍቅር ያሸንፋል!
Filed in: Amharic