>

በሕግ አምላክ!!! ቀኖና ቤተክርስቲያን ሁለት ፓትርያርክን በአንድ ዘመን አይፈቅድም!!! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው) 

በሕግ አምላክ!!! ቀኖና ቤተክርስቲያን ሁለት ፓትርያርክን በአንድ ዘመን አይፈቅድም!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
* ሕዝበ ክርስቲያን ሆይ! አልቅሱ እግዚኦ በሉ!!! 
የዚህ መናፍቅ የዐቢይ አፍዝ አደንዝዝ አዚም የኢትዮጵያን ሕዝብ ብቻ አጃጅሎ አልቀረም፡፡ ስለ እግዚአብሔር ክብር፣ ስለ ቅድስት ቤተክርስቲያን ልዕልና ሲሉ “ቀኖና ቤተክርስቲያን ተሻረ ተጣሰ!” ብለው ሀገራቸውን ጥለው በስደት ለ27 ዓመታት እየተንከራተቱ ዋጋ ሲከፍሉ የነበሩትን አባቶችንም አሳስቶ “የፓትርያርክ ሥልጣን በአንድ ዘመንና በአንድ ሀገር ለ2 አባቶች ልትሆን አይገባም! በአጋጣሚ በተለያየ ምክንያት ተፈጽሞ ከተገኘ ግን መንበሩ (ሥልጣኑ) ቀድሞ ለተሾመው ትጽናለት!” ፍ/ነ/ፍ/መ አንቀጽ 4 ቁ.70
የሚለውን ሠለስቱ ምዕት በመንፈስ ቅዱስ የደነገጉትን ቀኖና ቤተክርስቲያን አስጥሷቸው “ፓትርያርክ በሕይወት እያለ ፓትርያርክ አይሾምም!” ፍ/ነ/ፍ/መ አንቀጽ 4 ቁጥር 68-70፡፡ በማለት የተደነገገውን ቀኖና ጥሰው “ፓትርያርክነት ተሾሙ!” የተባሉትን የወያኔ ሹም አቦይ ማትያስን በፓትርያርክነት በመቀበል በአንዲት ቤተክርስቲያን ሁለት ፓትርያርክ እንዲኖር እንዲስማሙና እስከዛሬ የከፈሉት ዋጋ እንዲከስር፣ እዚህ ሀገር ውስጥ ያሉት የወያኔ አገልጋዮች ጳጳሳት በወደቁበት በደል ላይ እንዲወድቁ አደረጋቸው!!! እግዚኦ በሉ!!!
ይሄ ስሕተት ለዚህች ሀገር ከእንግዲህ ከእግዚአብሔር የሚላክ ምሕረት አለመኖሩን ጠቋሚ ነው!!! እግዚኦ በሉ!!!
የቀኖና ቤተክርስቲያን መጣስ፣ መሻር፣ መፍረስ ማለት ሌላ ትርጉም ያለው እንዳይመስላቹህ፡፡ የእግዚአብሔር ክብር ተደፈረ፣ እግዚአብሔር ተናቀ፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ተሰደበ ማለት ነው፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔር ተንቆ ተደፍሮ ተሰድቦ ምሕረት አለ እንዳትሉ!!!
እስከዛሬም ጨክኖ ያልጨከነብን ወያኔ ያሰደዳቸው አባቶች ለቀኖና ቤተክርስቲያን መጠበቅ በመቆማቸው ነበረ፡፡ አሁን ግን እነሱም ቀድሞ ከሳቱት፣ ከወደቁት፣ ከበደሉት ጋር መተባበራቸውን አወጁ እግዚኦ በሉ!!! የዚህን በደል ድፍረት ዋጋ ከእንግዲህ በኋላ ታዩታላቹህ! ሞት የሚያስናፍቅ መከራ፣ ቁጣ፣ መዓት መግቢያ ሲያሳጣህ ታየዋለህ!!!
ልብ በሉ በዚህ ስሕተት የእግዚአብሔር ቁጣ በእኛ ላይ የሚበረታበት ምክንያት ቀኖና ቤተክርስቲያን የተጣሰው በአደባባይ “የኦርቶዶክስን አከርካሪ ሰበርኩት!” እያለ የሚደነፋውን አላዊ አረማዊ አገዛዝ ግፍ የተሞላበት ጥቅም ለመጠበቅ ሲባል በመሆኑ ነው፡፡
ቀኖና ቤተክርስቲያን ቀኖና ስለሆነና ዶግማ ስላልሆነ ማንም ቅጥረኛ እየተነሣ ለማንም አላዊ ሲባል እንደፈለገ ያሻሽለዋል ማለት አይደለም!!! ከቀኖና ሕግጋትም እንደ ዶግማ ሕግጋት በርካታ ፈጽሞ የማይሻሻሉ ሕግጋት አሉ፡፡ ይሄኛው ቀኖና ከማይሻሻሉት ቀኖና ቤተክርስቲያን አንዱ መሆኑን ሠለስቱ ምዕት ሲያጠይቁ አንቀጹን በማያሻማ መልኩ ደምድመው ነው የዘጉት፡፡ ልብ በሉ!!! አንተ መከራኛ ሕዝብ ሆይ! እንግዲህ ከለላ የለህም!!! እንዴት ብለህ ከቁጣው እንደምታመልጥ እሱ ይወቅልህ!!!
የንስሐ ሕይዎት እንደሰማይ የራቃቹህ፣ ጸጸት የሚባል ያልፈጠረባቹህ፣ በቤተክርስቲያን ላይ በደል ግፍና ዐመፃ መፈጸም የማይሰለቻቹህ ልበ ደንዳና የወያኔ መለካውያን ጳጳሳት ተብየዎች ሆይ! እግዚአብሔር ግልጽ የመማሪያ፣ የመመከሪያ፣ የመመለሻ ተአምራቱን እያሳየ ጭምር ትመለሱ ዘንድ የመመከሪያ፣ የመጸጸቻና የመመለሻ በቂ ጊዜ ሰጥቷቹህ ነበረ፡፡ በመመከር፣ በመጸጸትና ንስሐ በመግባት ፋንታ ልበ ደንዳናና ዐመፀኛ በመሆናቹህ በጥፋት መንገዳቹህ ጸንታቹህ ተገኛቹህ፡፡
በመሆኑም እግዚአብሔርን ተስፋ አስቆርጣቹሃልና፣ አስቀድሞም በቅዱስ ቃሉ “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ከሔድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፥ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ!” ሐዋ. 20፤28-30
ብሎ እንደተናገረባቹህ
ከራሳቹህ ምቾትና ድሎት በቀር ታጥቃቹህ በምታገለግሉትና በምትሳሱለት በዚህ አላዊ አገዛዝ ቤተክርስቲያን የደረሰባት ኪሳራ፣ አደጋ፣ ጉዳት፣ ስብራት ጨርሶ የማይሰማቹህ፣ በዚህ አገዛዝ በደል የተነሣ ቤተክርስቲያን ለተበላባት ግማሹ መንጋ የማትራሩ፣ ከቤተክርስቲያን ጠላት ጎን የምትቆሙ ጨካኞች ተኩሎች መሆናቹህን በምግባራቹህ አረጋግጣቹሃልና እግዚአብሔር ከእንግዲህ ወደ እናንተ በምሕረት አይመለስም!!! በቁጣው በመዓቱ ለመርገፍ ለመገረፍ ብቻ ተዘጋጁ!!!
በእናንተ በደል፣ በእናንተ ድፍረት፣ በእናንተ ዐመፃ ሀገርና ሕዝብ ጭምር መቀጣታቸው ነው የሚያሳዝነው!!! ለነገሩ ሕዝበ ክርስቲያኑስ ከዚህ በደል መቸ አመለጠና??? ከቤተክርስቲያን ታሪክ እንደምንረዳው “ፓትርያርካችን ቅዱስ አትናቴዎስ በሕይዎት እያለ በሱ ላይ ከቀኖና ውጭ ሌላ ፓትርያርክ አንቀበልም!” ብለው በተቀሰቀሰው የሕዝቡ ቁጣ በግርግሩ መሃል “ተሾመላቹህ!” የተባለው ፓትርያርክ ተረጋግጦ እስኪሞት ድረስ ተቆጥተው ፓትርያርካቸውን ከስደት ተመልሶ መንበሩን እንዲይዝ እንዳደረጉት እንደ እስክንድርያ ክርስቲያኖች ዋጋ ከፍለን ቀኖና ቤተክርስቲያንን ማስጠበቅ ሲኖርብን ይሄንን ሳናደርግ በዝምታ ተመልክተናልና በደለኞች ነን፡፡ ስለዚህም ቁጣው ይገባናል!!!
ቅዱስ ልዑል እግዚአብሔር ሆይ! አዎ በደላችን፣ ድፍረታችን፣ ዐመፃችን፣ ንቀታችን ከሰብአ ትካት ሰዎች፣ ከኖኅ ዘመን ሰዎች፣ ከሰዶምና ገሞራም ሰዎች ከብዷልና ፍርድህ ትፈጸም!!!
መጨረሻችን እንዲህ መሆኑ በእጅጉ ያሳዝናል!!!
Filed in: Amharic