አቻምየለህ ታምሩ
የኢትዮጵያ ፖለቲካ አማራ ሲናገራቸው ወንጀልና የሚያስወግዙ፤ ከአማራ ውጭ ያለ ኢትዮጵያዊ ሲናገራቸው ግን ሐቅና ቅቡል ተደርገው በሚቆጠሩ ጉዳዮች የተሸበበ ነው። ይህ እውነት የኢትዮጵያን ፖለቲካ አማራ ጠልነት ፍንትው አድርጎ የሚያስረግጥ ሁነኛ ማሳያ ነው።
ይቺን አጭር ማስታወሻ እንድሞነጭር የገፋፋኝ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ በአሜሪካን አገር ያደረገው ንግግር ነው። ዐቢይ አሕመድ ወያኔ በግፍ ያሰደዳቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አራተኛ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት አቡነ መርቆሬዎስ ወደ መንበራቸው እንዲመለሱ ስምምነት ላይ መደረሱን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ የሚከለተውን «መንግሥታዊ» አቋም ተናገረ፤
«ኢትዮጵያ ከቅድስት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውጭ አትታሰብም፤ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሀገር ናት፤ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን የሚያክል እድሜ ጠገብ፣ ብዙ ሚሊዮን ሕዝብ ያለው፣ ትውፊት ያለው፤ታሪክ ያለው ተቋም በአለም ላይ ያለም።»
የሼሕ አሕመድ ልጅ ኦሮሞው ዐቢይ አሕመድ ይህንን የመንግሥቱ አቋም በመናገሩ «ጨቋኞቹ የኦርቶዶክስ እና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ መንግሥታት ያካሄዱትን ጭቆና ለመመለስ የሚሰራ»፤ «ክርስትናን በኃይል ለመጫን የሚታገል»፤ «ብሔር፣ ብሔረሰቦችን የሚጠላ»፤ «የነፍጠኛ ስርዓት አራማጅ»፤ ወዘተ እየተባለ በማንነቱ አልተወገዘም። የዐቢይ አሕመድን የዛሬ የአሜሪካ ንግግር ግን አማራ አድርጎት ቢሆን ኖሮ በማንነቱ ብቻ «የነፍጠኛ ስርዓት አስቀጣይ»፤ «ጨቋኞቹ የኦርቶዶክስ እና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ መንግሥታት ያካሄዱትን ጭቆና ለመመለስ የሚሰራ»፤ «የድሮ ስርዓት አራማጅ» ፤ «ማንነታችንን ለማጥፋትና ሃይማኖታችንን ለማስቀየር አማራ ዛሬም አይተኛም» ፤ ጁነይዲ ሳዶ ናዝሬት ላይ እንዳለው «ኢልሜን ቦፋ ቦፋደቴ» ወይንም «የእባብ ልጅ እባብ» እየተባለ መከራውን ይበላና በብሔርተኛ ዶክተሮችና ፕሮፌሰሮች ጉባኤ ተጠርቶ «ኢልሜን ቦፋ ቦፋደቴ» የሚል ይዘት ያላቸው በርካታ ወረቀቶች ይቀርቡበት ነበር።
ባለፈው ሰሞን 500 ሜትር ያለው የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ባሕር ዳር ላይ መውለብለቡን ተከትሎ ሰንደቅ አላማውን ቤተ ክርስቲያኗ ስለምትጠቀምበት ባሕር ዳር ላይ በአማራ ልጆች መውለብለቡ «የብሔር ብሔረሰቦችና ከኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ውጭ ያሉትን መብት የጣሰ ነው» እየተባለ የተነሳውን አቧራ መቼም አንረሳውም። 1200 ሜትር የሚረዝም የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ በአርባ ምንጭ፣ በሳውላና በተለያዩ የደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ሲውለበለብ ግን ምንም አልተባለም።
ታሪካችንን ከካድሬ ሳይሆን በታሪክ አዋቂዎች ከተጻፉ ምርምሮች የምናውቅ አንዳንዶቻችንም በኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ ውስጥ ቤተ ክርስቲያኗ የነበራችን ሚናና ሰንደቅ አላማ በመላው ጥቁር ሕዝብ ዘንድ ያለውን የነጻነት ምልክትነትና ሳውዲ አረቢያን ጨምሮ በዘውዳዊ አገዛዝ ስር የነበሩና ያሉ አገሮችን ሁናቴ እያነሳንና ታሪክ እያጣቀስን በመሟገታችን በማስረጃ ሊረቱን የተሳናቸው አንዳንድ አፍ ነጠቆች ወደተለመደው የያ ትውልድ ማሸማቀቂያ ወርደው «የነፍጠኛ ስርዓት አስቀጣይ»፤ «ጨቋኞቹ የኦርቶዶክስ እና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ መንግሥታት ያካሄዱትን ጭቆና ለመመለስ የሚሰራ»፤ «የድሮ ስርዓት አራማጅ» ፤ «ማንነታችንን ለማጥፋትና ሃይማኖታችንን ለማስቀየር አማራ ዛሬም አይተኛም» ወዘተ እየደረደሩ የእውቀት ጾመኝነታቸውን ሪቁን እንዳናወጣውና ዝም እንድንል ሞክረው ነበር።
ባጭሩ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እውነት እንደ ወንጀል እየተቆጠረ ያለው አማራ ብቻ ሲናገረው እየሆነ ነው። ይህ ደግሞ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምን ያህል ከአማራ አንጻር ወይንም በጸረ አማራነት እንደቆመ የሚያሳይ ነው። ለዚህ ነው አንድን እውነት አማራ ሲናገረው ወንጀል ያደረገው የወያኔ ስርዓትና የዛሬው የኢትዮጵያ ፖለቲካ እስካልተነቀለ በስተቀር የአማራ ሕልውና አደጋ ላይ እንደወደቀ የሚቀጥል ነው የምንለው።