>

የሽመልስን ልብ ይስጠን! (ጌታቸው ሽፈራው)

የሽመልስን ልብ ይስጠን!
ጌታቸው ሽፈራው
ሰው ተቃውሞ የሚያሰማው በሚጠላው ሰው ላይ ብቻ አይደለም። ትክክል አይደለም የሚለውን ሀሳብ፣ መስተካከል አለበት የሚለውን ጉዳይ ላይ ማንም ላይ ተቃውሞ ሊያሰማ ይችላል። ይገባልም።
ይህ ሰው በአንድ ወቅት አሜሪካ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ንፁሁን ሰንደቅ አላማ የሰቀለው ሽመልስ እንደሆነ ጋዜጠኛ ካሳሁን ይልማ ፅፏል።
ኢምባሲው ውስጥ ገብቶ ሰንደቅ አላማ ሲሰቅል በተቀረፀ ቪዲዮ ላይ እየተተኮሰበት እንኳ  አልተመለሰም። ትናንት ደግሞ ብቻውን ተቃውሟል ተብሏል።
የአብይን ፕሮግራም ያዘጋጁት ሰዎች ታማኝ በየነን ለምን ያገልሉታል ብሎ ተቃውሟል። ብዙው ዲያስፖራ ይህ ተቃውሞ እያለም ዶክተር አብይን ለማግኘት ሳይጓጓ አይቀርም።  ዲያስፖራው ለአብይ ባለው ድገፍ ይህ የመርህ ሰው ብቻውን ተሰለፈ ማለት ነው። የሽመልስ ጥያቄ “አሁንም ማግለል ይቁም!” ነው። “ሰውን ማግለል ይቁም” ብሎ ተቃውሞ ሲያሰማ ግን ከጎኑ ሰው አልነበረም። ድሮ በዚሁ ጥያቄ ብዙ ሰው ከጎኑ ሊሰለፍ ይችል ነበር።   ትናንት ከዳያስፖራው ይልቅ አብይ ከጎኑ ነበር። “አንተ እየተቃወምክ እኔ አልገባም” አለው ተብሏል።
 ሽመልስ አብይን ወደደውም አልወደደውም ይህ ጥያቄ መነሳት ያለበት ጥያቄ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩን ስለወደድከው  ብቻ ማግለልን ተሸከመህ ልትቀጥል አትችልም። አብይ እያባበለ አስገብቶት እንኳ ፊቱ ላይ ቅሬታውን ታየዋለህ!  የሚጠላቸው ሰዎች ጥይት እየተኮሱበትም አልተመለሰም። አብይን ቢያከብረውም ይመስላል “ሸብረክ” ብሎለታል። ያም ሆኖ ቅሬታው ፊቱ ላይ ይነበባል። ሰንደቅ አላማውን የየዛውን ያህል አብይን አልያዘውም። ከእነ ተቃውሞው ትህትናው፣ ከእነ ትህትናው ተቃውሞው ይታይበታል!
የመርህ ሰው ስትሆን እንዲህ ነው። ብዙውን ነፋስ ጠርጎትም ቢሆን ብቻህን ትገኛለህ። እንደ ሽመልስ።  ሽመልስ ድሮ ከጎኑ ከነበሩት ይልቅ ከጎኑ ያገኘው ተቃውሞ ያቀረበበትን ዶክተር አብይን ነው!
ዶክተር አብይ አህመድ ሽመልስን የተለማመጠው የተሳሳተ ተቃውሞ ስላቀረበ  አይደለም። ያነሳው ጥያቄ እውነት ስለሆነ ነው። ይቅርታ የማለት ያህል ነው። የመርህ ሰው ስለሆነም የበለጠ ያከበረው ይመስለኛል። ዶክተር አብይ እየጨፈረ ከሚቀበለው ሕዝብ በላይ ለዚህ ሰው ትኩረት የሚሰጠው ይመስለኛል።
አብይን ከተቀበሉት ዳያስፖራዎች መካለል በጣም ምክንያታዊው ሽመልስ መሆን አለበት። “እንደመር” እየተባለ፣ ታዋቂው መድረክ አስተዋዋቂ መቀነስ ከመርህ ውጭ ነው።  ሽመልስ የተቃወመው ይህን የመርህ ጥሰት ነው። ለመርህ እንጅ ለሰሞነኛ ፖለቲካ፣ በግል ለምታከብረው ሰው ካልቆምክ እንደ ሽመልስ  ያለህን ቅሬታ ታቀርባለህ!  ትሁት ሆኖ ሲቀርብህ፣ ከእነ ቅሬታህ በትሁትነት ትቀበለዋለህ! መቃወምህን በጥላቻ ሳይሆን “ትክክል ነህ” የማለት ያህል ሲቀበልህ ለጊዜው በቅሬታህ ትቀበለዋለህ! ፊትህ ላይ ሳይጠፋ፣ መሪ ሆኖ ስላቀፈህ ብቻ ጥያቄህን አሽቀንጥረህ ሳትፈነጥዝ በሽመልስ ገፅታ ትገኛለህ! የሽመልስ ፊት እንደዛ ይነበባል!
ዝም ብሎ መንጎድ፣ እንደመር ሲባልም “መግተልተል” በበዛበት ወቅት እንደ ሽመልስ በቅንነት የሚቃወሙ፣ የመርህ ሰዎች በርከት ቢሉ ገዥዎቹንም እንዲህ ይበልጥ እንዲሰማቸው፣ ነገም ከመርህ እንዳያፈነግጡ ባደረጉ ነበር። ለመርህ መቆምን፣ ከግለሰቦች ፍቅር፣ ከመሪዎች ጋር ባለን ቅርበት ወይንም ርቀት ባንንደው ሀገር ትውልድ ተሸገሪ፣ የመርህ ፖለቲካ፣ ከሰሞነኛ፣ ከወረት የዘለለ የፖለቲካ ባህል በገነባን ነበር! ከእምቧይ ካብነት ይልቅ የረገጠ፣ የረጋ የመርህ ስርዐት በገነባን ነበር!
የሽመልስን ልብ ይስጠን!
Filed in: Amharic