>
5:18 pm - Saturday June 14, 9575

የወንበዴ አማራጭ፦ መገንጠል ወይስ መበታተን (ጌታቸው ሺፈራው)

ለእነ ደብረፅዮን መከባበር ማለት ሲዘርፉም፣ ሲገርፉም፣ ሲዘልፉም “አሜን” ብሎ መቀበል ነው። “ዘረፍከኝ፣ ገረፍከኝ፣ ዘለፍከኝ” ብሎ መጠየቅ ለእነሱ ከቆየው የገዥነት ደረጃቸው ያወርዳቸዋል። ሰው እኩል ይሆናል። ለእነሱ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ፈፅሞ እኩል መሆን የለባቸውም። ከእነ ደብረፅዮን ኢትዮጵያ፣ የዘራፊና የተዘራፊ፣ የገራፊና የተገራፊ፣ የዘላፊና የተዘላፊ ሀገር ሆና መቀጠል አለባት። ካልሆነ መከባበር የለም ማለት ነው። ባለፉት 27 አመታት ሲዘርፉ፣ ሲገርፉ፣ ሲዘልፉ በመቀዋቅር ነው። ይህ መዋቅራቸው ሀገር ለማበልፀግ ባይችል፣ ለመበተን አያንስም። ደብረፅዮን ያወራው ስለዚህ ሀይል ነው። ስለዚህ አማራጭ ነው።

ካለፉት ወራት ወዲህ እንደአዲስና በተጠና መንገድ ማፈናቀል፣ እንደአዲስ ማጋጨት፣ እንደአዲስ መግደል ተጀምሯል። ለመበተን ከበቂ በላይ ማስፈራሪያም ሙከራም አድርገዋል።

ደብረፅዮን ዛሬ ያወራው ትግራይን ስለመገንጠል አይደለም። ኢትዮጵያን ለመበተን ነው። ትግራይ ከኢትዮጵያ ትገነጠላለች ለማለት አሳማኝ ምክንያት የለም። በምንም ምክንያት ትግራይ ተገንጥላ ኢትዮጵያ አትኖርም አይባልም። ማን ነው ትግራይን የኢትዮጵያ ማሰሪያ ገመድ ያደረጋት? ደብረፅዮንም ትግራይን ስለመገንጠል አላወራም። ደብረፅዮን ያስተላለፈው ግልፅ መልዕክት ነው። “እኛ ያልነው ካልሆነ ኢትዮጵያን እንበትናታለን!” ነው ትርጉሙ። “በመዳፋችን ላይ ነች፣ ስንፈልግ እንደፈለግን እናደርጋታለን” ነው ቅኔው። “ስንዘርፍ፣ ስንገርፍ፣ ስንዘልፍ ዝም ካላላችሁ፣ ይህን ሁሉ ተግባር ስንፈፅምበት የነበረውን ሀይል ለመበተን እናውለዋለን” ማለቱ ነው።

ትግራይን መገንጠል ለእነ ደብረፅዮን አይጠቅማቸውም። ይህን ሁሉ ሀብት ያካበቱት በትግራይ ለም መሬት አይደለም። ከትግራይ ውጭም በርካታ ሀብት አላቸው። መንገስ የሚፈልጉትም ከትግራይ ውጭ ነው። ትግራይንማ አሁንስ ማን ነካባቸው? አረና ነው? እነሱ የሚፈልጉት ቀሪውን ከሰው በታች አድርገው፣ ረግጠው መግዛት ነው። አሁን ለዚህ ሁሉ ዛቻ ያደረሳቸው ይህ ክፉ ተግባራቸው፣ ሌላውን ረግጦ መግዛት የሚቀር ስለመሰላቸው ነው።

ደብረፅዮን የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ነው። ያለው መቀሌ ነው። ከ100 ሚሊዮን ሕዝብ መካከል የ5ሚሊዮን ሕዝብ ምክትል አስተዳደር ነው። ክፉ ቢያስብ ቢያስብ ማሰብ ይችል የነበረው ትግራይን መገንጠል ነው። ዛሬ የነገረን ግን ትግራይን ስለመገንጠል አይደለም። “እኛ ከሞትን ሰርዶ አይብቀል” ነው ያለው። “እኛ እንደፈለግን የማንዘርፋት፣ የማንገርፍባት፣ የማንዘልፍባት ኢትዮጵያ ትበተን” ነው ያለው። የ5 ሚሊዮን ሕዝብ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ሆኖ 100 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን ስለመበተን ነው ያወራው! ደብረፅዮን የተናገረው አንደኛው ሀገር በሌላው ላይ የሚዝተውን ያህል ነው። አሜሪካ አሸባሪ ነህ ያለችው አንዱ ተነስቶ “አሜሪካን እናቃጥላታለን” እንደሚለው የአሸናሪና የወንበዴ ዛቻ ነው። እቅድም ነው!

ትግራይን ለመገንጠል በቂ ምክንያት የለም። ይሁንም ከተባለ ግን ትግራይን ገንጥሎ ከሌላው ጋር በሰላም ስለመኖር አላወራም። ያወራው ሌላውንም መበተን ነው። ይህ የ27 አመት ስራቸው አይደለም። ከአርባ አመት በፊት የቋመጡበት ነው። በ26 ገፅ ፕሮግራማቸው ያስቀመጡት የፋሽስት ራዕይ፣ የመለስ ዜናዊ ተልዕኮ ነው! ወንበዴ እየተባሉ ያሰራጩት ፕሮግራማቸው ሙሉ አላማ ነው። አሁን አማራጭ አድርገው አቅርበውታል!

ደብረፅዮን አማራጩን እንዲሁ አልተናገረውም። ለትህነግ አዋጭ አማራጭ ስለሆነ ነው። ትህነግ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚጠቀመው በሁለቱ አማራጮች ብቻ ስለሆነ ነው።

የመጀመርያው መከባበር የሚሉት ነው። ባለፈው 27 አመት እንደሆነው ኢትዮጵያውያን በትህነግ እየተዘረፉ፣ እየተገረፉ፣ እየተዘለፉ መኖር ሲችሉለት ነው። ለትህነግ ይህ እጅግ አዋጭ ነው። ያ ሁሉ ዘረፋ የተፈፀመው በዚህኛው አማራጭ ነው! ሁለተኛው አማራጭ መንግስታዊ መዋቅርን ለሽብርና ለውንብድና ለሚጠቀም አካል የሚጠቅም ነው። ብጥብጥና ሁከት ሲፈጠር፣ ሀገር ሲበተን ከሶማሊያ የጎሳ ታጣቂም በላይ በገንዘብና በታጠቀ ቡድን ዘረፋን ማስቀጠል ይቻላል። ለትህነግ! ይህኛው አማራጭ ሁለተኛው አዋጭ አማራጭ ነው። ከመጀመርያው አንፃር ዋስትናው አስቸጋሪ ነው። ተረጋግተው አይዘርፉም! ተረጋግተው አይኖሩም! ግን አይጠየቁም፣ ከሌላው የተሻለ አቅም ይኖራቸዋል። የሌላውን ያህል አይጉዱም። ሌላውንም በማዳን ሰበብ ወደ መንበሩ ይመለሳሉ። ተረጋግቶ ወደ መዝረፍ!

ትግራይ ተገንጠለች አልተገነጠለች ኢትዮጵያ ሰላም ሆና ትህነግ አይጠቀምም። ላላፉት 27 አመታት ለተፈፀመው ሁሉ ይጠየቃል። ማወራረድ ይኖራል ብሎ ይጠብቃል። ሲወራረድ ደግሞ “ነገቲቭ” ውስጥ እንደሚገባ ያውቀዋል። ስለዚህ ሁለት አማራጭ አስቀመጠ። “ወይ እንግዛችሁ፣ ወይ እንበትናችሁ”! ነው የሚለው! “ወይ ተረጋግተን እዘርፍሃለሁ፣ ካልሆነ ገድዬ እዘርፍሃለሁ” ማለት ነው!

የወንበዴ አማራጭ!

ወንበዴ፣ ውንብድናውን ለመቀጠል ከዚህ አማራጭ ውጭ የለውም። ከዚህ ተግባሩ ለመውጣት ግን ሌላ አማራጭ አለው። አንደኛው ምህረት መጠየቅ ነው። የሚምረው አካል ጋር ተደራድሮ ሊሆን ይችላል። መዝረፊያዎቹንና መግረፊያዎቹን ግን ይጥላል። ካልሆነ ግን በሽፍትነቱ ይቀጥላል። ታድኖ ከተያዘ ደግሞ የከፋው ዕጣ ይገጥመዋል። ካልተያዘም እየተንከራተተ መኖሩ ነው። እነ ደብረፅዮን ምህረቱን የመረጡ አይመስሉም! ትግራይ ውስጥ ሸፍተዋል።

Filed in: Amharic