>

የ“ሲርት” ፖለቲከኞች (መስከረም አበራ)

የ“ሲርት” ፖለቲከኞች

 መስከረም አበራ

አሥራ ሰባት ዓመት በዱር በገደል የታገሉት ህወሃቶች ደርግን የጣለው የእነሱ ጠመንጃ ብቻውን ይመስላቸዋል፡፡ይሄው ግማሽ እውነት ደግሞ ራሳቸውን ሁሌ ሥልጣን ላይ መኖር የተገባቸው፣ አሸናፊነት ብቻ እጣ ፋንታቸው የሆነ ብቸኛ ኃያላን አድርገው እንዲያስቡ ሳያደርግ አልቀረም፡፡ ይህ ስህተት ስህተትን እየወለደ ሄዶ ከስልጣን መውረድ፣ከአድራጊ ፈጣሪነት መጉደል ሊመጣ እንደሚችል እንዳያስቡ እና አሁን ላሉበት ሁኔታ የስነ-ልቦና ዝግጅት እንዳያደርጉ ከልክሏል፡፡ ጠመንጃ ወደ ስልጣን መምጣት ያስችል ይሆናል እንጅ ስልጣን ላይ እንደማያኖር መረዳት አልሆን ያላቸው ህወሃቶች ባላሰቡት ብቻ ሳይሆን ባላሰብነው መንገድ ብቻቸውን ሃገር ከመዘወሩ ገለል ብለዋል፡፡እውነቱን የተቀበሉት ግን አይመስልም፡፡

እንደ ህወሓት ያለ “ሁሉ በእጁ ሁሉ በደጁ” የሆነ፣ ሥልጣን ላይ ተወዝቶ ሥር የሰደደ ፓርቲ እንዲህ በቀላሉ እንደጉም ብን ብሎ ከመንበር ይታጣል ብሎ መገመቱ ራሱ ከባድ ነበርና ህወሓትም ይህን መቀበል ቢያስቸግረው አይፈረድበትም፡፡ በዚህ ላይ የኢህአዴግን ሥጋ ለብሶ ሁሉን የሚያደርገው ህወሃት አጥብቆ ይመካ የነበረው አለቅነቱን በግድ በጫነበት ኢህአዴግ ውስጠ- ፓርቲ አንድነት ነበር፡፡

በህወሓት የበላይነት ሳይነጋገር ተስማምቶ ለጥ ሰጥ ብሎ በሚገዛው የአጋር እና አባል ፓርቲ ካድሬ አስተማማኝ ባርነት አጥብቆ የሚመካው ህወሃት ነግ በእኔ ሳይል በተቃዋሚ ፓርቲዎች እንደ አክርማ መሰንጠቅ ይስቅ ነበር፡፡በጌታ-ሎሌ ግንኙነቱ የቆመውን ‘ውስጡን ለቄስ’ የነበረውን የፓርቲውን አንድነት የፓርቲ ዲስፕሊን በማጎልበት ይተረጉመው ነበር፡፡ ህወሓት ያለ አባል ፓርቲዎች  እኩልነት አንድነት አመጣለሁ ብሎ ማመኑ ድንገት ሞቶ መገኘትን አመጣበት፡፡ ይህን ማመን ህወሃትን ሆነው ሲያስቡት ከባድ ነው፡፡

ህወሓትን የመሰለ ሁሉን በጉልበት ማድረግ የሚቀናው፣ፈርጣማ ፓርቲ ገፍትሮ ለመጣል ከህዝብ የተፋፋመ ትግል ጋር የወገኑት አዲሶቹ የኢህዴድ አመራሮች ድፍረታቸው የሚደነቅ ነው፡፡ በህወሃት ቤት ማደጋቸው የፓርቲውን የቤታቤት ደባ፣ሼር እና ተንኮል በደንብ መረዳት ስላስቻላቸው የህዝብ ትግል ወዝውዞ ወዝውዞ ባደከመው ህወሃት ላይ የመጨረሻውን ሃይለኛ ምት ሰንዝረዋል፡፡ ውድቀቱ ከወደ ብረት አንጋች ተገዳዳሪዎቹ መንደር (በተለይ ከአርበኞች ግንቦት ሰባት) ብቻ እንደሚመጣ ይጠብቅ የነበረው ህወሓት “ይህን ድንገቴ የማንጅራት ምት” መቋቋም አቅቶት ተሽመድምዷል፡፡

ህወሓት የመጨረሻ የውድቀት ደወሉን የደወለው አቶ ኃይለማርያምን ተለማምጦ ሥልጣን ላይ ለማቆየት “ኩራቱ በጄ” ያላለው ጊዜ ነው፡፡ በህወሓት ነቃፊዎች ዘንድ የዓለምን ውርጅብኝ እያስተናገዱም ቢሆን ‘አቤት ወዴት’ ሲሉ የኖሩትን አቶ ኃ/ማርያምን ክፉኛ ያስከፋው ህወሓት ሰውየው በእጁ እያሉ ለሚፈልገው በሰው ክንድ የአዞ ጉድጓድ የመለካት ፖለቲካ የሰጡት ጥቅም አልታየውም ነበር፡፡

ባልጠበቀው ሁኔታ፣ኦህዴድ ክፉኛ ባንጓጠጠበት ወቅት፣በሃገር ዳርቻ በተነሳ ተቃውሞ ወንበሩ እንደወተት እየተናጠ ባለበት ወቅት በአደገኛ መገጣጠም ስልጣን በቃኝ ያሉትን አቶ ኃ/ማርያምን በግማሽ ቀን ሲያሰናብት የሚመጣውን አላመዛዘነም፣ያንዣበበት አደጋ አቶ ኃ/ማርያምን ከመለመን የበለጠ መዘዝ እንደሚያመጣበት አላሰበም ነበር፡፡ የአቶ ኃ/ማርያምን መነሳት ተከትሎ በመጣው ውስጠ-ፓርቲ ጉሽሚያ ባለጠመንጃው ህወሃት በባለ ብዙ ህዝቡ ኦህዴድ መሸነፉ ለሽንፈት ተዘጋጅቶ ለማያውቀው ህወሃት ሊዋጥ የማይችል እንደ ህልም ያለ ነገር ነው፡፡

ህወሓት ባላሰበው አቅጣጫ የመጣበት ምት ሥልጣኑን እንዳሳጣው ለመረዳት ብቻ ሳይሆን ሽንፈቱን ለመቀበልም ያስቸገረው ይመስላል፡፡ በፍጥነት እየተቀያየረ ያለውን የሃገራችን ፖለቲካ ጭራ ለመያዝም ግር እንዳለው ያስታውቃል፡፡ ፈጣኑ የፖለቲካ ሁነት በመንገዱ ሁሉ የህወሃትን ስር እየነቀለ የሚሄድ መሆኑ ግርታውን አብሶታል፣የሚይዝ የሚጨብጠውን አሳጥቶታል፡፡ለወትሮው ሲያሾረው የነበረው ኦህዴድ የማይጋፉት ባለጋራ ሆኖበታል፡፡ ብአዴንም የድሮው አይደለም፡፡ ቀን ከዞረበት ጋር ጉዳይ የሌለው የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡም ከአሸናፊው ጋር ሽው እልም እያለ ነው፡፡

ልክ ባልሆነ ከመጠን ያለፈ የአሸናፊነት ስነ-ልቦና ሰክሮ የኖረው ህወሃት ሽንፈትን መቀበል በራሱ ችግር እንደሚሆንበት ባያጠራጥርም እንደ ባዶ እቃ እየሞላ የፈለገውን ሲያደርጋቸው ከነበሩት ገባር ፓርቲዎች የመጣበትን ሽንፈት እንዲህ በቀላል ተቀብሎ እኛ እንደምናስበው ሟሽሾ እንደማይቀር መገመት ደግ ነው፡፡ገሃድ የሆነውን የፖለቲካ ስልጣን ቢያጣም በስልጣን ላይ ስር ሰዶ እንደ መኖሩ የልቡን ባያደርስለትም፣የንዴቱን ያህል ባይሆንም አንዳንድ ከፀጥታ እና ደህንነት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍጠር የሚያስችል ጉልበት አያጣም፡፡

ይህ ከህወሃት የአልሸነፍ ባይ እልኽኝነት፣ስር ለስር ሄዶ የጨለማ ስራ የመስራት ልምድ እና በአመዛኙ ወታደራዊ ማንነት ውቅር ጋር ሲዳመር የሃገራችን መከራ በምናስበው ፍጥነት እንደማያበቃ ያመላክታል፡፡በሌላ በኩል ቁጣው በነደደው ህወሃት ተቃራኒ የቆመው የጠ/ሚ/ር አብይ አስተዳደር ህወሃት በማያውቀው የሲቪል እና ይቅር የመባባል ቋንቋ ብቻ አነጋግሬ ህወሃትን ገራም አደርጋለሁ ባይ ነው፡፡

ይህ ነገር ሁለት ቋንቋቸው የማይመሳሰል ሰዎች በየቋንቋቸው ሲያወሩ የሚፈጠረውን ነገር ይመስላል፡፡ ለህወሃት አይሆኑ ሆኖ ያኖረውን ወንበሩን የቀማው ሰው በምንም ቋንቋ ቢያናግረው ለበጎ መስሎ አይሰማውም፡፡ ለህወሃት መልካም የሆነችው አብሮነት እሱ ወንበሩ ላይ ሆኖ ሌሎች ወረድ ብለው ቆመው የምትደረገዋ ነች፡፡ያለ እንደዚህ ያለች አብሮነት ሃገርም ብትሆን በህወሃት ልቦና ትርጉም የላትም፡፡ አብይ ደግሞ “ሊያስሩኝ ይፈልጉ ነበር” ያሏቸውን ህወሃቶችን ዝም ብሎ በመተው ብቻ ፍቅርን ለህወሃት ማስተማር ይቃጣቸዋል፤ህወሃትን ህወሃት ያደረገውን የውድድር፣የበቀል እና ሁሌ የማሸነፍ ማንነት እንዲህ ባለ መንገድ የሚቀይሩ ይመስላቸዋል፡፡የትግራይን ህዝብ ደህንነት ማንም እንዳይጋፋ በማሳሰብ ብቻ በግድም በውድም ህወሃት በትግራይ ምድር የገነባውን ተቀባይነት ሊገዳደሩ ይሞክራሉ፡፡

በህወሃት ባህል ይህ ሁሉ ዋጋ ያለው አይመስለኝም፡፡ ህወሃት የሚያውቀው ሁለት ተቃራኒ ነገሮችን ነው-ማሸነፍ ወይ መሸነፍ፡፡ ማሸነፍ የእሱ ነው መሸነፍ ደግሞ የሌላ! ስለዚህ ጠ/ሚ አብይ ዛሬ ያሸነፉት ለህወሃት ብቻ የተሰጠውን ማሸነፍ ሰርቀው ነው፡፡ በተሰረቀ የማሸነፍ ሜዳ ላይ ቆመው የሚያናግሯቸው ዶ/ር አብይ የመደመር ሆነ የፍቅር፤ ሃገር ማዳን ሆነ የፍትሃዊነት ቋንቋ ለህወሃቶች እንደ ሚንሿሿ ፀናፅል ትርጉም አልቦ ነው፡፡ ማሸነፋቸውን ከሰረቃቸው ሰው ጋር መደማመጥ ለዘመናት ሲገነቡት የመጡትን፣ደርግን በማሸነፍ ደግሞ “ያረጋገጡትን” መሰረታዊ የአሸናፊነት ስነ-ልቦናቸውን የሚገዳደር አካሄድ ነው፡፡በህወሃቶች እሳቤ አሸናፊ ማለት እነሱ በአሸናፊነታቸው ዘመን እንደሚያደርጉት ባለጋራውን ለቃቅሞ የሚያስር፣የሚገድል፣የሚገርፍ፣የሚሳደብ፣የሚያሰድድ ነው፡፡

ይህን ያላደረጉት አብይ በህወሃቶች ዘንድ  አሸናፊ ናቸው ተብለው ይቆጠሩ ዘንድ የሚሆን አይመስለኝም፡፡ አሸናፊ፣ጉልበታም ማሰር እየቻለ ነገር ግን መንግስትነቱን በሚመጥን ማስተዋል አስተውሎ፣ የቂም በቀልን፣ የጥርስ መናከስ ፖለቲካዊ ባህላችንን የሆነቦታ ለመስበር ሲል ብቻ ማሰር የሚገባውን ላያስር እንደሚችል በህወሃቶች ዘንድ ግንዛቤው ያለ አይመስለኝም፡፡ አዲስ ባህል ሊያመጡ የሚቸገሩት ጠ/ሚ/ር አብይ የገጠማቸው ትልቅ ፈተና ቋጠሮው ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡ አብይም የህወሃትን ነገራ ነገር አይተው የመደመር ፍልስፍናቸው በተደማሪው ሁሉ ዘንድ እሳቸው የሚሰጡትን (ከነተበው ፖለቲካችን የመውጣት መንገድ አይነት) ትርጉም ብቻ ሊይዝ እንደማይችል የተረዱ አልመሰለኝም፡፡በሁለት አካላት ዘንድ የሚደረግ የመስተጋብር ዘይቤ አንደኛው አካል የተረዳበት አረዳድ መልካም ስለሆነ ብቻ መልካም ፍፃሜ ላይኖረው ይችላል፡፡

የጠ/ሚር አብይ የመደመር ፍልስፍና የ “ኑ ተደመሩ ግብዣ” ለቀረበለት ህወሃት የሚሰጠው ትርጉም ፍፃሜውንም ሆነ ሂደቱን በመወሰን ረገድ ከፍ ያለ ሚና አለው፡፡ ህወሃት የፖለቲካ ስልጣን ላይ ብቻ ሳይሆን የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ላይም ተንሰራፍቶ የኖረ ሥረ-ብዙ ፓርቲ እንደመሆኑ ስልጣንን አጥቶ ለመደመር ያለው ዝንባሌ ለወደፊቱ የፖለቲካችን ጉዞ የማይናቅ ሚና አለው፡፡ በተመሳሳይ ጠ/ሚር አብይ ህወሃትን ጨምሮ የመደመር ፍልስፍናቸው ለማይዋጥላቸው አካላት ተለዋጭ መላ መዘየዱን መርሳት የለባቸውም፡፡ እንጂ እሳቸው ያመጡት (ብዙዎችም የወደዱላቸው) የመደመር ፍልስፍና እንደ አየር ሁሉም ደስ እያለው ይስበዋል ብለው ማሰብ የለባቸውም፡፡ በጎ ነገርን ለመቀበል በጎ ማንነት ያስፈልጋል፡፡ በጎነት ሁሉ ስልጣን ላይ መውጣት ብቻ የሚመስለው ህወሃት ደግሞ ስልጣኑን ጥሎ የሚያነሳው ምንም ምድራዊ ስጦታ የለም፡፡ስለዚህ የከዳውን የስልጣን ገድ ለመፈለግ የሚማሰውን ሁሉ ይምሳል፤የሚጎነጎነውን ሁሉ ይጎነጉናል፤ ሚሴረውን ሁሉ ያሴራል፤ ለዚሁ ይረዳኛል ያለውን የክፉ ቀን ወዳጅ ሁሉ ይጠራል፡፡

በድንገት የቆመበት መሬት እየተናደበት ያለው ህወሃት እንደፈለገ ሲያደርጋት የኖረውን ሸገርን ለባለ ጊዜ ሰጥቶ መቀሌ መሽጓል፡፡ በመቀሌው የድንጋጤ ቁዘማ የተሰየመው ግን ህወሃት ብቻውን አይደለም፡፡ ለወትሮው ህወሃትን በሰብዓዊ መብት ረጋጭነቱ፣በአምባገነንነቱ፣ በሙስናው ህዝብን በማስመረር ሲከሱት የነበሩት የቀድሞ አባሎቹ አይተ ግደይ ዘርዓፅዮን እና ዶ/ር አረጋይ በርሄ፣ተቃዋሚ ነን ብለው አረና ትግራይን የመሰረቱ አመራሮች፣አቶ መለስ አፈር ሳይጫናቸው ከህወሃት ተሰነጠርን ያሉ ግለሰቦች እና ሌሎች ትግራዊያን ሁሉ ከህወሃት ጋር ለስብሰባ ተሰይመዋል፡፡

እነዚህ በህወሃት ጭንቅ ጊዜ ከበውት ስብሰባ የተቀመጡ ሰዎች ከትግሬነታቸው በቀር ከህወሃት ጋር የሚያዛምዳቸው ነገር ግልፅ አይደለም፡፡ ሁሉም በሚባል ሁኔታ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ህወሃትን በዘረፋ እና ኢ-ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን በማስፈን የሚከሱት ነበሩ፡፡አብሮ ስብሰባ ለመቀመጥ የሚያስችል የቀደመ ይፋዊ ውይይት አድርገው እንደሁ ግልፅ ያደረጉት ነገር የለም፡፡አሁን የሚያደርጉትም ህወሃት የቀድሞ ስህተቱን አምኖ ወደፊት አብሮ ለመስራት የሚያስችል ድርድር ለማድረግ እንደሆነ የተነገረ ነገር የለም፡፡ከዚህ ይልቅ በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዘንድ የህወሃት የወንጀለኝነት ምልክት ተደርጎ በሚወሰደው ኢፈርት እጣ ፋንታ ላይ መምከር አንዱ የስብሰባቸው አላማ እንደሆነ ነው ከገለልተኛ ምንጮች እየተዘገበ ያለው፡፡

በግል ትዝብቴ ከአቶ ገብረመድህን አርአያ በቀር የኢፈርትን ወንጀል-ወለድ ድርጅትነት እና የህወሃት የአድሎ ምልክትነት አንስቶ ሲያወግዝ የሰማሁት የትግሬ ፖለቲካኛ፣አክቲቪስትም ሆነ ልሂቅ አላጋጠመኝም፡፡በተቃራኒው በሌላ ጉዳይ ህወሃትን የሚያብጠለጥሉ የትግሬ ፖለቲከኞችም ሆኑ አክቲቪስቶች በኢፈርት ጉዳይ ላይ ወይ የትግራይ ህዝብ አንጡራ ሃብት እንደሆነ ፈርጠም ብለው ይናገራሉ አለያም፤ ለትግራይ ህዝብ ሳይሆን ለህወሃት በመጥቀሙ ይቆጫሉ፤ ካልሆነም ኢፈርትን መንካት የትግራይን ህዝብ የሚያስቆጣ መዳፈር እንደሆነ ያስጠነቅቃሉ፡፡የአሁኑ ከምድር ዳርቻ መቀሌ ላይ  ከትሞ የኢፈርትን እጣ ፋንታ ለመወሰን መሟሟቱ የኢፈርትን አፈጣጠር ጤናማነት በወል የመቀበሉ ቅጥያ ነው፡፡

ኢፈርት የተፈጠረው በዘረፋ፣ ቆሞ የሚሄደውም የኢትዮጵያ ህዝብ ለፍቶ ወይ በስሙ ተለምኖ በሚመጣ ዶላር  በሚንቀሳቀሱ ባንኮች ላይ በሚደረግ ደባ እንደሆነ ህወሃት ላልሆኑት ዛሬ ህወሃትን ከበው መቀሌ ለከተሙት ምሁራን፣ታላላቅ ሰዎችም ሆነ ወጣት ፖለቲከኞች እና አክቲቪስቶች የሚጠፋቸው ጉዳይ አይደለም፡፡ትክክል መስሎ የተሰማቸው በወንዛቸው ልጆች በእነሱ ቀየ የተደረገ ነገር ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ ተመሳሳዩ በሌላ ቦታ ቢደረግ ኖሮ ለእሪታው የሚቀድማቸው እንደማይኖር የመንደራቸው ጥቅም የተነካ ሲመስላቸው በሚያሰሙት ሮሮ አንፃር መገመት አይቸግርም፡፡

በሃገራዊ ደረጃ ተደመሩ በሚለው የዶ/ር አብይ ብሄራዊ ጥሪ ሰበብ መጥተው ከህወሃት ጋር ለመደመር መቀሌ ያቀኑት የትግራይ ተወላጅ ጉምቱ ፖለቲከኞች ስብሰባ የተቀመጡት እንደፓርቲ  ወንጀለኝነትን ከጠገበው ህወሃት ጋር ነው፡፡በግል ደግሞ ማዕከላዊው መንግስት በወንጄል ሲፈልጋቸው አሻፈረኝ ብለው ወደ ትውልድ ቀያቸው ከኮበለሉት እስከ ህወሃት ከወረደ ስልጣን ላይ አልቀመጥም ብለው ስልጣን ካስረከቡት የህወሃት አባላት ጋር ነው፡፡ ግፋ ሲልም በትግራይ ቴሌቭዥን መስኮት ብቅ ብለው ጥፋቱ ምን እንደሆነ ግልፅ ባልሆነው ጠ/ሚ አብይ ላይ ውግዝ የሚያወርድም አለ፡፡ አብይ ቢያጠፉ ቢያጠፉ ከህወሃት የበለጠ ያጠፉት ነገር አይኖርም፡፡ለዲሞክራሲ፣ለህግ የበላይነት እና ነፃነት እንታገላለን ይሉ የነበሩት ስደተኛ ፖለቲከኞች የህግን ጥሪ አሻፈረኝ ካለ ሰው ጋር ምን እንጋራን ብለው እንደተቀመጡ ብቻ ሳይሆን ቀድሞስ ከህወሃት ጋር ተጣላን የሚሉት ለምን እንደሆነ ግር ያሰኛል፡፡

በመደመር ስም ወደሃገር ቤት የመጡ ስደተኛ ፖለቲከኞች ምን እየሰሩ እንደሆነ ነገሬ ብሎ የማይከታተለው የዶ/ር አብይ መንግስትም እኩል ግር ያሰኛል፡፡ኢትዮጵያን ሁሉ የሚያስተዳድረው የዶ/ር አብይ መንግስት መቀሌ ወርዶ በወንጄል የሚፈለጉ ግለሰቦችን ማምጣት ካልቻለ እንዴት በብዙ ሊታመን ይችላል? በዚህ ሁኔታ ህወሃት ከስጣን ገለል በማለቱ በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዘንድ የተፈጠረው ተስፋስ እንዴት ሊፀና ይችላል?

ከፅንሰት ውልደቱ ጀምሮ ትግራይን እስከመገንጠል በደረሰ አክራሪ የትግራይ ብሄርተኝነት የሚታወቀው ህወሃት በስልጣን ዘመኑ ሁሉ የትግራይ ህዝብ እና ህወሃት አንድ ነው ሲል ኖሯል፡፡ የትግራይ ህዝብ ደግሞ ለዚህ ያለውን መልስ በገሃድ ወጥቶ ተናግሮ አያውቀምና ‘አንድ ነው አይደለም?’ የሚለው ክርክር የሚደራው በትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲከኞች እና አክትቪስቶች እንዲሁም ትግሬ ባልሆኑ የሃገራችን ፖለቲከኞች እና በህወሃት መሃል ነው፡፡ ህወሃት ‘የትግራይ ህዝብ እና እኔ አንድ ነን’ ሲል ቀደም ብለው የተጠቀሱት ፖለቲከኞች ደግሞ የለም የትግራይ ህዝብ እና ህወሃት አይገናኙም ይላሉ፡፡ ከባለቤት የወጣ ነገር በሌለበት የትኛው ክርክር እውነታውን ወካይ እንደሆነ ለማወቅ አዳጋች ነው፡፡ የሆነ ሆኖ ህወሃት የስልጣኑ መሰረት ሲያረገርግ ወደ ትግራይ መንጎዱ ቀድሞም ‘እኔ ህዝብ ነኝ ህዝቤም እኔ ነው’ ሲል ከኖረው ነገር ጋር በደንብ ይገጥማል፡፡

ይህ ነገር የማይረታውን የህዝብ ትግል ለማሸነፍ ሲንተፋተፍ ኖሮ በስተመጨረሻው ተስፋውን ወደ ትውልድ መንደሩ ወደ ሲርት ያደረገውን አምባገነኑን የሙአምር ጋዳፊን መጨረሻ ያስታውሳል፡፡ ጋዳፈ ተስፋ ያደረጉበት የሲርት ህዝብም ባለው አቅም የለውጥ ሃይሉን በመፋለም ለሰውየው የስልጣን እድሜ መራዘም አጋርነቱን አሳቷል፡፡ዝምታው የበዛው እና ከስንት ዘመን በሀኋላ አደናጋሪ ሰልፍ እያደረገ ያለው የትግራይ ህዝብ መቼ ምን እንደሚያደርግ ማወቅ ባይቻልም ህወሃት ግን ጨራረሱን እንደ አጀማመሩ ወደ ትውልድ መንደሩ በማድረግ እስትንፋሱን ለማቆየት ያሰበ ይመስላል፤በትውልድ ቀየው ከወንዙ ልጆች ጋር መክሮ ሞቱን በህይወት ለመቀየር፣ዳግም ለማንሰራራት ማሰቡም የማይጠበቅ አይደለም፡፡ህወሃት ሲዳከም ህወሃትን ተክቶ የትግራይን ህዝብ ከመጣው አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ጋር ማላመድ፣የትግራይ ህዝብንም (እንደሚባለው ከህወሃት የሚለይ ከሆነ) ከኢትዮጵያ ህዝብ ትግል ጋር ማሰለፍ ይገባው የነበረው አረና ትግራይ የተባለው ፓርቲም ፀሃይ ከጠለቀችበት ህወሃት ጋር በር ዘግቶ መቆዘሙን መርጧል፡፡

የዶ/ር አብይ መንግስትም ለህግ እምቢኝ ባይ የህወሃት ባለስልጣናትን  ትግራይ ዘልቆ ከህግ በላይ አለመሆናቸውን ለማሳየት አቅም ይጠረው፣ ፍላጎት አይኑረው፣ በይደር ያቆየው በውል የታወቀ ነገር የለም፡፡ ሆኖም ዶ/ር አብይ እነዚህን አሻፈረኝ ባይ ባለስለጣናት ከመቀሌ አምጥቶ በሚፈልጋቸው ህግ ፊት ለማቆም የትግራይን ህዝብ ቅዋሜ እንደፈራ ከሰሞኑ ከዩኒቨርሲቲ መምህራን ጋር ባደረጉት ንግግር ላይ ጠቆም አድርገዋል፡፡ይህ ነገር ዶ/ር አብይ እንደ አብዛኛው ኢትዮጵዊ  የትግራይ ህዝብ የህወሃቶችን ክፉ እንደማይወድ እንሚያስቡ ያመላክታል፡፡

ከሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በተለየ ህወሃት ጥፋተኝነቱ እየታወቀ ሳይቀር ቆምኩለት ባለው ህዝብ ዘንድ ግዙፍ  ተቀባይነት ያለው ፓርቲ ከመሆኑ አንፃር የዶ/ር አብይ ንግግር ስህተት የለውም፡፡ይህ ንግግራቸው ዶ/ር አብይ ለአብሮነት ሲባል የሚያደርጉትን እላፊ መጠንቀቅ ቢያሳይም ስህተት ግን አለው፡፡የትግራይ ህዝብ በህግ የሚፈለግ ሰው እንደማናቸውም ሰዎች ዝም ብሎ ካልተንጎራደደ ብሎ የመቀየም መብት የለውም፡፡ የትግራይ ህዝብ እውን በዚህ ጉዳይ ይቀየማል ወይ በሚለው ጉዳይ እርግጠኛ መሆን ባይቻልም የሚቀየም ከሆነ ቅያሜው ህጋዊነትም አግባብነትም ያለው ነገር አይደለም፡፡

በአሁኑ ወቅት መቀሌ የሰፈሩ ከስልጣን ተነሽ የህወሃት የቀድሞ ባለስልጣናት አንዳንዶቹ ቢሮ ለማስረከብም አሻፈረኝ እንዳሉ ነው የሚነገረው፡፡ይህን የልብ ልብ የሰጣቸው ምንድን ነው? ብሎ መመርመሩ አይከፋም፡፡ የመጀመሪያው ምክንያት ህወሃት ወንበር ላይ ተወዝቶ ብዙ በመኖሩ በቀላሉ እፍ ብለው የማያጠፉት  ቅሪት ተፅዕኖ ሃያልነት ነው፡፡ህወሃቶች የተካኑበት በድለው እንኳን የተበደሉ ያህል ገርፎ የመጮህ ልማድ እውነትን የያዘን ሰው ሳይቀር የተሳሳተ መስሎት  ግራ የሚያጋባ ነገር ነው፡፡ጠ/ሚር አብይ በዚህ ነገር ሳይቸገሩ አይቀሩም፡፡

አብይ እንደ መንግሥት በሚያደርጓቸው የህወሓትን ጥግ የነካ የጥቅመኝነት ዝንባሌ የሚነኩ ውሳኔዎች ሳቢያ በህወሓት እና ጋሻ ጃግሬ እህት ድርጅቶቹ ካድሬዎች የድርጅት ግምገማ እና ስብሰባ ወቅት መብጠልጠላቸው አይቀርም፤አልፎ ተርፎ የድርጅት ኪዳን በመብላት ሊከሰሱ ይችላሉ፡፡መንግስትን ይመራል የሚባለው የፓርቲያቸው ዘይቤ ደግሞ ለዚህ ይረዳል፡፡ ይህ ደግሞ አብይ ከድርጅት መንፈስ ውጭ እንደ መንግስት በሚያደርጓቸው ውሳኔዎች ላይ እንደልባቸው እንዳይሆኑ ማድረጉ አይቀርም፡፡በዚህ ምክንያት ህዝብ እንደሚጠብቀውም ዶ/ር አብይ ራሳቸው እንደሚመኙትም ለመራመድ ፈተና ይሆንባቸዋል፡፡

ሁለተኛው ምክንያት ህወሃት በትግራይ ክልል ሰፊ ተቀባይነት ያለው ፓርቲ መሆኑ ነው፡፡በዚህ ምክንያት የክልሉ የፀጥታ ሃይሎች የፌደራል መንግስት ተፈላጊ የህወሃት ባለስልጣናትን ለመያዝ የሚያደርገውን ጥረት ከልባቸው ላያግዙ ይችላሉ፡፡ አልፈው ተርፈውም ለመከላከል ሊሞክሩ ይችላሉ፡፡ኤፍ.ቢ.አይ ባጣራው መረጃ መሰረት ደግሞ አዲስ አበባ ያሉ ባለስልጣናትም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡እነዚህን ሰዎች በቁጥጥር ስር አውሎ ህጋዊ በሆነ መንገድ በፍትህ ፊት እንዲቆሙ ለማድረግ የአብይ የፀጥታ ሃይሉን የማዘዝ ጉልበት ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ እርግጠኛ መሆን ባይቻልም ቀስ በቀስ ጉልበቱን እያበረታ እንደሆነ ከሚደረጉ ሹም ሽሮች መረዳት ቻላል፡፡

ሆኖም ህወሃት ለረዥም ዘመን የፀጥታ ሃይሉን ቀፍድዶ የመቆየቱ ነገር ከገሃዱ ስልጣን ወርዶ እንኳን ለረብሻ የሚሆን ጉልበት እንዳያጣ ሊረዳው ይችላል፡፡ በዚህ ላይ የሰሜን ዕዝ እና የማዕከላዊ እዝ ሰራዊት ትግራይ መከተማቸው፣የእዝ አዛዦቹም ከህወሃት ሊወግኑ የሚችሉ ሰዎች መሆናቸው፣የደብረዘይቱ የአየር ሃይልም በከፊል ወደ መቀሌ እንደተጓዘ ከሚነገረው ጋር ተደምሮ አብዝተው በወታደራዊ ጉልበት ለሚያምኑት ህወሃቶች የልብ ልብ ሊሰጣቸው ይችላል፡፡

ሶስተኛው ምክንያት ህወሃት በስልጣን ላይ በነበረበት ዘመን ኦሮሚያ ክልል በአልገዛም ባይነት ሲያስቸግረው እንደነበረ፤ኦህዴድም በሌሎቹ እህት ድርጅቶች መጠን ገራም ሎሌ እንዳልነበረ  (መለስ ሳይሞቱ ጭምር አንዳዴ ሲያስቸግር እንደነበረ ይታወቃል) እና ይሄው እርሾ አድጎ እነ ለማ/አብይን እንደወለደ ስልጣን ለማይጠግቡት ህወሃቶች በቁጭት እና በቂም የሚታሰብ ሃቅ ነው፡፡ስለዚህ ዛሬ ቀን ተቀይሮ ኦህዴድ ባለ ወንበር ሲሆን ህወሃቶች ደግሞ ወደ ትውልድ ቀያቸው አቅንተው ትግራይ ክልል ደግሞ በተራው ለኦህዴድ ዙፋን የማይመች ሁከተኛ ቀጠና (Restive political zone) ሊያደርጉት ሊመኙ ይችላሉ፡፡

ኦህዴድ ወደስልጣን ሳይወጣ  በኦሮሚያ ካለው ተቀባይነት ይልቅ ህወሃት ከስልጣን ወርዶም ሆነ ስልጣን ላይ እያለ ትግራይ ውስጥ ያለው ተቀባይነት ላቅ የሚል መሆኑ ለዚህ እሳቤው ማገር ሊሆን ይችላል፡፡ ከኤርትራ ጋር የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ እንደሚደረግ የሚታሰበው የድንበር መካለል በኢሮብ ህዝቦች ላይ ሊያመጣ የሚችው ተፅዕኖ ደግሞ ህወሃት ስልጣኑን በማጣቱ የሚያደርገውን የማጯጯህ አካሄድ ለህዝብ የማሰብ መጋረጃ ሊሰጥለት ይችላል፡፡ህወሃት ብቻ ሳይሆን የህወሃትን ስልጣን ላይ መቆየት ለማይጠላው ዘረኝነት ሽው ያለበት ሁሉ የድንበር ማካለሉ ነገር ሰም ሆኖ ለወርቁ (የህወሃት ከስልጣን መታጣት ሃዘን) ጮክ ብሎ  እንዲያለቅስ ያግዘዋል፡፡

ከዚሀ በተጨማሪ ዋነኛ መነጋገሪ ነጥብ የሚሆነው የዶ/ር አብይ የመደመር እና የይቅርታ ፍልስፍና የህግ የበላይነትን ከማስከበር እና ወንጀለኞችን በህግ ፊት ከማቅረብ ጋር ያለው ፍቅር እና ጠብ እንዴትነት አለመታወቁ ነው፡፡ወንጀል የሰራ ሰው በህግ ፊት ቀርቦ ህጋዊ የእርምት እርምጃ ሊወሰድበት ግድ ነው፡፡ይህ ካልሆነ ወንጀለኞች ቀድመው በሰሩት ወንጀል አለመጠየቃቸው አንድ ጥፋት ሆኖ በህግ ጥላ ስር አለመሆናቸው ተጨማሪ ጥፋት እንዲስከተሉ ያግዛቸዋል፡፡በጉጉት የምናየውን የለውጥ ሂደት እስከማደናቀፍም ሊደርሱ ይችላሉ፡፡ ‘እኔ ከሌለሁ ትፈራርሳላችሁ’ እያለ ሲያስፈራራ የኖረው ህወሃት እሱ ሳይኖር ሃገር በተቀበለችው መሪ ተሰትራ ስትመራ ማየት ደስ ላይለው ይችላል፡፡

አብሮነት በመዝራቱ፣ከዘረኝነት ጋር በመፋለሙ፣ህዝብን በማክበሩ፣ስልጡን ፖለቲካ ለማምጣት በመድከሙ ጠ/ሚ አብይ አጠገብ ለመድረስ የሚያስችል ማንነት እንደሌለው ህወሃት አሳምሮ ቢያውቅም በተካነበት የመተኮስ ጥበብ ፀጥታ በማስጠበቁ ረገድ አብይን እንደሚበልጣቸው ማሳየት ሳይፈልግ አይቀርም፡፡ ስለዚህ የህወሃትን ከስልጣን መውረድ ተከትሎ ሊመጣ የሚችለውን ብጥብጥ አይጠላውም፤ሊያነሳሳው፣እየቆሰቆሰ ሊያባብሰውምይችላል፡፡

ይህን ለማስታገስ አብይ ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር የቀደመ የፖለቲካ ባህላችንን የገመገሙበትን እና አስቀያሚውን የመበላላት ፖለቲካዊ ዘያችንን ሊያስቀሩ ያሰቡበት መንገድ እንደገና ማጤን ነው፡፡ ሁላችንም እንደምንስማማው እና ዶ/ር አብይም አጥብቀው እንደሚያምኑት የቀደመ የመግደል መጋደል፣የማገት መታገት፣የማመቅ መታመቅ ፖለቲካዊ ባላህችን መቀየር አለበት፡፡ ይህን ማድረጊያው ጥሩ ሰዓትም አሁን ነው፡፡

ለምን ቢባል የከረመው የፖለቲካ ባህላችን እግር ከወርች ቀፍድዶ አላራምድ ያለ የችግራችን ሁሉ ራስ መሆኑን ለመረዳት የቻሉ ጠ/ሚ ወንበር ላይ በመሆናቸው ነው፡፡ለዚሁ መልካም ነገር ልባቸውን ማስነሳታቸው ዶ/ር አብይን በእጅጉ የሚያስመሰግናቸው ሆኖ የከረመውን ልማድ በአንዴ ለማስወገድ ብቻ ሳይሆን እላፊ ሄደው “ማሰር ያለፈበት ነው አናስርም” በሚል እሳቤ ወንጀለኞችን ሳይቀር ህግ እንደሚያዘው በህግ ጥላ ስር ለማድረግ ዳተኛ መሆናቸው የሚያስኬድ አልመሰለኝም፡፡አልፎ ተርፎ ለራሳቸው ህይወት እስከማስጋት፣ የተጀመረውንም የለውጥ ጭላንጭል እስከማዳፈንም ሊደርስ ይችላል፡፡ ከሁሉ በላይ የህግ የበላይነትን የሚጋፋ ይመስለኛል፡፡

መሆን ያለበት “አላስርም” ሳይሆን “ቀዳሚዎቼ በደምፍላት ያደርጉት እንደነበረው ያለ በቂ ምክንያት አላስርም፣አስሬም አልደበድብም፣ደብድቤ ያልሰሩትን እንዲናገሩ አላደርግም፣ባላደረጉት ሃጢያት ስማቸውን ጭቃ አልቀባም” ነው፡፡ ‘አስበው አልመው ባጠፉት፣ማስረጃ በተገኘበት ጥፋትም ቢሆን ጭርሱኑ አላስርም’ ማለት ግን ወደተፈለገው ስልጡን ፖለቲካ የሚወስደንን መንገድ ለአሰናካይ አሳልፎ መስጠት እንዳይሆን ስጋት አለኝ፡፡ ነገሩ ለወንጀለኛ ተጨማሪ በደል እንዲያደርስ፤ስልጣኑ ሲያምረው ለቀረው ቢሆንለትም ባይሆንለትም ለማንሰራረት እንዲፋትር እጣ ፋንታ ዕድል ተርታ መስጠት ነው፡፡

Filed in: Amharic