>

አገሬ ደርሼ መጣሁ! (ደረጀ ደስታ)

አገሬ ደርሼ መጣሁ!

ደረጀ ደስታ

ከ17 ዓመት በኋላ መሆኑ ነው። የቤተሰብ አባልና ወዳጅ ዘመድ በጠቅላላው ቁጥሩ ሰባት እሚደርስ የቤተሰብ አባል “በነቂስ” ወጥቶ “ከፍተኛ” አቀባበል አደረገልኝ። 13 ቀናት ቆየሁ። ባልቴቷ እናቴ የሞተ ሰው ተነስቶ አየሁ አለችኝ። “አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም” ብሏል ጸሐፊውም። “የማርያም ስም ማን ነበር ቢለው አግኝተህ አጣኸው” እንዳለው አገሬንም አይቼ አጣኋት። ለማንኛውም በጨረፍታ አይቻት በትዝታ አጥቻት ተመልሻለሁ። ፍቅሯ ግን ፍቅር ነው። አገሬን ለማየት ምክንያት ከሆኑኝ ከቲም ለማ እና ከጠቅላይ ምኒስትር አብይ ጋር አየር ላይ ተላለፍን። እሳቸው ዛሬ አዲስ አበባ ሲገቡ እኔ ተመልሼ ዋሽንግተን ገባሁ። እዚህ ሆኜ አዲሳባ እንዳየኋቸው አዲስ አበባም ሆኜ አሜሪካ ላይ ሲናገሩ አየኋቸው። ድሮ ቢሆን ኢንተርኔቱም ፌስቡኩም ገና አልደረጀምና ዋሽንግተንን በዘኢትዮጵያ ጋዜጣችን ሸልለንባት ነበር። ዛሬ ደግሞ ዋሽንግተን በተራዋ ታላላቅ መሪዎችዋን ይዛ ዘነጠችብን። አዲስ አበባ ሆነው ወዲህ ሲያዩት ነገረ ድራማው የተለየ ስሜት ይፈጥራል። ለካ ፈቀቅ ሲሉ ዓይን ይገለጣል። ከሁሉ በላይ ግን ከዚሁ ሁሉ ጊዜ በኋላ አገሬን ማየቴ የበለጠ ስሜት ፈጥሮብኛል። እንኳን እንዲህ ተሰምቶኝ ድሮም ጻፍ ጻፍ ይለኛልና ሰሞኑን እወርድበታለሁ ብያለሁ። በዚያ ላይ ደግሞ እግሬ ወጣ ከማለቱ ስንት ነገር ተደበላልቆ ቆየኝ። እናንተም እንኳን ደህና ቆያችሁኝ! አገራችንም ውላ ትግባ!

Filed in: Amharic