>

ከምርጫ በፊት ሀገር ይኑረን (ዶ/ር ዘላለም እሸቴ)

ከምርጫ በፊት ሀገር ይኑረን

ዶ/ር ዘላለም እሸቴ

የሕዝብ መንግስት ለመመስረት ምርጫ ከማድረግ በፊት መንግስት የሚያስተዳድራት ሀገር ትወለድ። አሁን ያለን “ሀገር” ለቅርጫ ቀርባ ሁሉም ጎሣ ድንበሩን ለማስከበር ጦር እየመዘዘና ያልመዘዘው ለመምዘዝ አድፍጦ ጊዜ እየጠበቀ ነው። በቀረን ሁለት ዓመት ምርጫ ለማድረግ ከተነሳን፤ ሀገር እንድትወለድ መሰራት ያለበት ሥራ ለመስራት አንድ ቀን እንኳን ላይኖረን ነው። ባለ ሀገሩ ሀገር ሳይኖረው ንጉሶችን መምረጡ ምን ይፈይድለታል? ንጉሥ ለመሆን አራራ ያለው ካልሆነ በቀር፤ በሕዝብ ዘንድ ይህን ያህል ተቀባይነት ያለውን ጠቅላይ ሚኒስቴር ሀገርን እንዲያዋልዱ መተባበር ትልቅ ክብር ነው።

ሀገሪቷ በጎሳ ተሸንሽና ሰላም ቢገኝ ኖሮ ሸንሽኖና ተለያይቶ መገላገል ይቻል ነበር። ግን ብዙ ንጉሶችን ፈጥሮ እርስ በርስ ያባላን እንደሆነ እንጂ መቼም ቢሆን የሰላም እንጀራ ልንበላ አንችልም። ምክንያቱም ተደበላልቀን ስናበቃ አሁን እንዴት ተሸንሽነን በድንበር ልንስማማ እንችላለን? የተደባለቅነው ወረቀት በእስፒል እንደተያያዘ ዓይነት ሳይሆን ወረቀት በሙጫ የተያያዘ ያህል ነው። በሙጫ የተጣበቁ ወረቀቶችን መለየት ፍዳ ነው። ከተሞከረ ደግሞ ሁሉም ይበጣጠሳል።

በዚህ ታሪካዊ በሆነ ወቅትና ሁሉም የዲሞክራሲን አየር እየተነፈሰ ባለበት ሁኔታ፤ ሁሉም ከጎሣው አጥር ወጥቶ የኢትዮጵያ ነፃ አውጭ ለመሆን መሽቀዳደም ሲገባው አሁን ምን እንደሚጠበቅ አላውቅም። ምርጫ ከማድረጋችን በፊት ይህ አዕምሮ በመደመር መንፈስ እንዲታደስና ጊዜውን የሚመጥን አካሄድ እንዲኖረን ለምክክር ፋታ ያስፈልገናል።

ያለፈውን በደል ስናወራ ግን ጊዜ ወስደን ተናዘንና ይቅር ተባብለን ሂሳቡን ዘግተን ወደፊት እንዳንራመድ ተደርገን ዛሬ ደረስን። ዛሬ ብሔራዊ እርቅ አድርገን ከትላንት የምንፋታበት ጊዜ ነው። ሀገር እንዲወለድ ትላንት ተብትቦ ያሰረንን ሰንሰለት ለመበጣጠስ ቅድሚያ እንስጥ። ነፃ ያልወጣ ሕዝብ ነፃ የሆነ መንግስት ሊመሰርት አይችልም።

ለጊዜው ነው እንጂ በጊዜ ሂደት ሁሉም ተደማሪ ይመስለኛል። ይህችን ጊዜ በአግባቡ ካልተጠቀምን እንደ ዶ/ር አብይ ያለ የአዋላጅነት ስብዕና ያለው መሪ እንደገና ለማግኘት አንችልም። ወደፊት ሊኖር ይችላል ቢባል፤ እስከዚያ ድረስ ተጠፋፍተን ባዶ እንቀራለን። ስጦታችን የሆኑትን ዶ/ር አብይን ብንጠቀም አስተዋይነት ነው። እንደ እኔ ቢሆን ሀገር አዋልደው ሲያበቁ ከምርጫ በሁዋላ እርሳቸው የኢትዮጵያን ፖለቲካ ትተው ለአፍሪካ አንድነት ራሳቸውን የሚሰጡ ሰው እንዲሆኑ ነው።

አዲሱ ሀገር በቀል የይቅርታና ፍቅር የመደመር ርዕዮተ ዓለምን የሚመጥን የሀገር አስተዳደር ውቅር ያስፈልገናል። ኢትዮጵያ በምትባለው ሀገር ላይ ብሔራዊ መግባባት እንድረስ።  አሁን እርስ በርስ ከሚያባላን የጎሳ ፌድራል ስርዓት ወደ ቤተሰብነት የሚያዘልቀን ሀገር በቀል የሆነ አዲስ የፌድራል ስርሃት ፈጥረን እንሻገር። ሁሉም ቀልቡን ወደዚያ ቢያደርግና የመደመሩን ፈዋሽ ራዕይ በስራ ለመተርጎም ይሰማራ። ዲሞክራሲን ለምርጫ ከመሞከራችን በፊት፤ ሕዝብ በእኩልነትና በፍቅር የሚተዳደርበት ጤናማ ሰዋዊ ስርዓት ለመፍጠር ዲሞክራሲን እንጠቀም። የመጀመሪያው የምርጫ ልምድ መደመር ይሁን።

የፀሐፊው አድራሻ፥ myEthiopia.com

Filed in: Amharic