>
5:13 pm - Sunday April 19, 3772

ጠመጃ ያነገተ ሁሉ ተጠባባቂ ነፍሰ ገዳይ ነው!!! (ወሰን ሰገድ ገ/ሚካኤል)

ጠመጃ ያነገተ ሁሉ ተጠባባቂ ነፍሰ ገዳይ ነው!!!
ወሰን ሰገድ ገ/ሚካኤል


* …እኔ ኢትዮጵያን እወዳለሁ፤ ልኖርባትም እፈልጋለሁ፡፡ ልሞትላትም፤ ልገድልላትም ዝግጁ አይደለሁም፡፡…… ጀግናም ሆነ ፈሪ፣ ካህሳይ ሆነ መገርሳ፣ ሟችም ገዳይም ያው ልጇ ነው፡፡ አገር ልጆቿ እንዲኖሩባት፣ እንዲኖሩላት እንጂ እንዲሞቱላትና እንዲገድሉላት አትፈልግም፡፡”

እየገቡ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ለውጥ መምጣት አለበት ብለው፣  ተሰባስበው የሆኑ ቡድን ፈጥረው፣ ፓርቲ መስርተው፣ ወ.ዘ.ተ (በነፍጥም ያለ ነፍጥም) ሲታገሉ የነበሩ የፖለቲካ ሰዎች ወደ ሃገር ቤት እየገቡ ነው፡፡ ከወራት በፊት ወደ ሃገር ቤት ከመግባት የዘገዩት ኦነግ እና ኦብነግም በዚህ ሳምንት ገቡ፡፡ አርበኞች ግንቦት ሰባትም በቅርቡ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ብቻ …. በተቃውሞ ጎራው የሰነበቱት በሙሉ እየገቡ ነው። በሰላማዊ ትግል ተሳትፈው እውነተኛ ዲሞክራሲ ለማስፈንን አልመው ነው ወደ ሃገር ቤት እየመጡ ያሉት፡፡ ወደ ሀገር መግባታቸው ጥሩ ነው፤ ተገቢም ነው፡፡ አመጣጣቸው “አሮጌ ጠላ በአዲስ ጋን ለመጥመቅ” እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
““አሮጌ ጠላ በአዲስ ጋን ለመጥመቅ” የሚለውን አገለለፅ የመኢሶን መስራች ከነበሩት ደረጄ አለማየሁ ከተባሉ ምሁር ድንቅ ፅሁፍ ነው የወስድኩት፡፡ አቶ ደረጄ፤ በሰኔ ወር 1985 ዓ.ም “ታዝቤ ዝም ከምል” በሚል ርዕስ ፅፈው በበተኑት (ባለ 43 ገፅ) ፅሁፍ ውስጥ ነው የተጠቀሙበት፡፡ ፀሐፊው ልክ እንደአሁኑ በ1960ዎቹ አጋማሽ በውጭ አገር የሚኖሩ የፖለቲካ ልሂቃኖች ወደ ሃገር ውስጥ መግባታቸውን፣ እሳቸውና የመኢሶን መስራች ጓዶቻቸው ወደ አገር ውስጥ የገቡበትን ምክንያት ሲያወሱ “ጠላ ለመጥመቅ….” ነበር ይላሉ፡፡ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ማለታቸው ነው፡፡
ሁሌም ባነበብኩት ቁጥር የሚያስገርመኝን፣ ይህንን የአቶ ደረጄን በጥቂቱ ብቀንጭብ ነው የሚሻል ይመስለኛል፡፡ እነሆ፡-
“…..የኢትዮጵያ ሕዝብ አዲስ ጋን ምንም አያደርግለትም፤ ያማረው ቀምሶት የማያውቀው አዲስ ጠላ ነው፡፡ …. አዲስ ጠላ የመጥመቅ ሙከራ ውስጥ ….ተሳትፌ አውቃለሁ፡፡ …. አሁን ይህን ደብዳቤ የምፅፍበት ከተማ (በርሊን) እያለሁ፤ ሀገሬ አዲስ ጠላ የመጥመቅ ጥንስስ መጠንሰሱን ሰማሁ፡፡ …. በነበረችን አቅምና ችሎታ ጌሾ ወቀጣው ላይ ለማገዝ (ወደ ሃገር ቤት) ተመለስን፡፡……በዋና ጠማቂነት በታሪክ ተሹሜያለሁ ይል የነበረው የያኔው ባለ ክላሺን ከፋም ለማም ጥሩ ጠላ ይውጣው አይውጣው ሳይታወቅ ዓመት ያህል ጌሾ ወቀጣው ላይ እንደተሳተፍን፣ ‹ጌሾ እንዲህ አይወቀጥም› ብሎ …. ወዳጆቼን ጨረሰ፡፡”
የመኢሶን አመራር ከነበሩት ከአቶ ደረጄ አለማየሁ ድንቅና ዘለግ ያለ ፅሁፍ ውስጥ ከላይ ያነበባችሁትን ሃሳብ የነቀስኩት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ አንደኛውና ዋነኛው ምክንያቴ የፅሁፋቸው ጥበባዊነት፣ ውበትና ተምሳሌታዊነት ነው፡፡ ፖለቲካም Art (ጥበብ) ነው እንዲሉ ምሁራኑ፡፡ በሌላ አነጋገር ፖለቲካ ዝም ብለው የሚደነቀሩበት ሳይሆን ጥብብን የሚጠይቅ ሥራ ነውና፡፡ ሁለተኛው ምክንያቴ፤ ፅሁፋቸው ልክ እንደአሁኑ የለውጥ ወይም የሽግግር ዘመንን (1960ዎቹ) የሚያስታውስ በመሆኑ ነው፡፡ ሶስተኛው ምክንያቴ፣ “ያ ትውልድ” ያለፈበት፣ ያ የለውጥ ዘመን ልክ እንዳሁኑ ግርግር፣ አለመግባባትና ሁከት የነገሰበት መሆኑ ነው፡፡ የአሁኑን ዘመን ለየት የሚያደርገው (የዲሞክራሲን ጠላ ለመጥመቅ) “በዋና ጠማቂነት ተሹሜአለሁ” የሚለው ወገን ቄሮ፣ ፋኖ እና ዘርማ …. ወ.ዘ.ተ የሚባሉ መሆናቸው ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ አብነቱ በየቦታው የሚለኮሰው የእርስበርስ ቁርቋሶ፣ ግድያና ዘረፋ ነው፡፡
በአጭሩ፣ የአሁኑ ፀያፍ ክስተት የሚያሳየው ካለፈው ታሪክ አለመማራችንን ነው፡፡ አለመማር ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ባለፈው ትውልድ “ለጠላ ጠመቃ” የመጡት የፖለቲካ ሰዎች ጌሾ ወቀጣው ላይ እንኳ ሳይሳተፉ ዕድላችንን ለማባከን የቆረጥን መምሰላችን ነው የሚያሳዝነው፡፡ ይህ ጀግንነት አይደለም፡፡ ጀግንነት የደፈረሰውን፣ መልሶ ማደፍረስ አይደለም፡፡ የደፈረሰውን ወደ ጭቃነት መለወጥ አይደለም፡፡ ጀግንነት፣ የፖለቲካ ጭቃ ውስጥ መንከባለልም አይደለም፡፡
እንደውም እዚህ ላይ አቶ ደረጀ አለማየሁ በፅሁፋቸው መግቢያ ላይ የተንደረደሩበትን ጥቅስ ብዋስ ነው የሚሻለው፡፡
“ጀግና የማያስፈልጋት ሀገር የታደለች ናት” (በርቶልድ ብሬሽት) ይላሉ በመግቢያቸው አቶ ደረጀ፡፡  በፅሁፋቸው መሃል ደግሞ ፀረ- ፋሺስቱ ካርል ክራውስ “ጠመንጃ ያነገተ ሁሉ ተጠባባቂ ነፍሰ ገዳይ ነው” ማለቱን ይጠቅሳሉ፡፡
እኔ ደግሞ ይህንን አባባላቸውን ትንሽ ቀየር አደርግና “…. አዎ ክላሽ ያነገተ ሁሉ ተጠባባቂ ነፍሰ ገዳይ ነው፤  በደቦ ወገኑን ለማጥቃት የሚያስብ ሁሉ ተጠባባቂ ነፍሰ ገዳይ ነው፡፡” እላለሁ፡፡  በደቦ ያጠቃ፣ የዘረፈ የገደለ ብቻ ሳይሆን፣ እነዚህን ነገሮች ለማድረግ ያሰበ ተጠባባቂ ነፍሰ ገዳይ ነው፡፡
(በነገራችን ላይ ይህንን ፅሁፍ የምታነቡ፣ የመኢሶኑን አቶ ደረጀ አለማየሁ የምታውቋቸው አድናቂያቸው መሆኔን ንገሩልኝ፤ “እኛ እንዳለን አለን፣ እርስዎ እንዴት ነዎ? በሉልኝ፡፡) 
መውጫ
—–
አሁንም ከአቶ ደረጀ ፅሁፍ “እምነታቸውን” ልዋስና ይህንን ፅሁፍ ልደምድም፡፡ 
እነሆ፡-
“….ጀግና ሆኖ በፈሪ ጥይት፣ ፈሪ ሆኖ በጀግና ጥይት አንድም ሰው በፖለቲካ ምክንያት በሚሞትባት ኢትዮጵያ የፖለቲካ ነፃነት እና ማሕበራዊ ዕድገት ሊኖር አይችልም፡፡ በፖለቲካ እምነት ሰው የማይሞትባት ኢትዮጵያን ለማምጣት ለፖለቲካ ዓላማ ለመሞት ዝግጁ መሆንን መተው አለብን፡፡ በዚህ መንፈስ ሞትን መፍራት አለብን ለማለት ነው፡፡ ……..እኔ ኢትዮጵያን እወዳለሁ፤ ልኖርባትም እፈልጋለሁ፡፡ ልሞትላትም፤ ልገድልላትም ዝግጁ አይደለሁም፡፡…… ጀግናም ሆነ ፈሪ፣ ካህሳይ ሆነ መገርሳ፣ ሟችም ገዳይም ያው ልጇ ነው፡፡ አገር ልጆቿ እንዲኖሩባት፣ እንዲኖሩላት እንጂ እንዲሞቱላትና እንዲገድሉላት አትፈልግም፡፡”
እኔ እንደገባኝ ይህ ማለት “ሀገር በፖለቲካ ምክንያት የሚሞትላትም፣ የሚገድልላትም ጀግና አያስፈልጋትም” ማለት ነው፡፡
.
ይኸው ነው!!
Filed in: Amharic