>
5:13 pm - Monday April 19, 7593

ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም አሉ (ከይኄይስ እውነቱ)

ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም አሉ

ከይኄይስ እውነቱ

በውኑ ወያኔ ትግሬ ለለውጥ ጕዞው እንቅፋት አይደለምን? እነዚህን ጉዶች የተቆራኛቸው ክፉ መንፈስ በውሸት/ቅጥፈት እንደታጀሉ ወደ ጥልቁ ሊያወርዳቸው ሳይሆን አይቀርም፡፡

ነውርና ሐሰት ገንዘቡ የሆነው የመንደርተኞቹ ስብስብ ሕወሓት ሁሌም የኢትዮጵያን ሕዝብ እያታለለ እንደሚኖር በመገመት በቀጥታና በእጅ አዙር የሽብር ድርጊቶች አገራችንን እያመሰ፣ ሕዝባችንን እያተራመሰ መሆኑ የተጀመረውን ለውጥና የለውጡን አመራሮች እንደ ዓይኑ ብሌን የሚጠብቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚገባ ያውቃል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዚህ ከይሲ ቡድን ምንም በጎ ነገር ሊጠብቅ አይችልም፡፡ ክፋትና ተንኰል፤ ጭካኔና ድንቁርና እንደተጣባው ግብዓተ መሬቱ እንደሚፈጸም አልጠራጠርም፡፡ ለጊዜው መወራጨቱ የሚጠበቅ ቢሆንም አዲሱን የለውጥ አስተዳደር ለማሳጣት የሚያደርገው ማናቸውም ሙከራ ግን በጭራሽ አይሳካለትም፡፡ ይልቁንም በተጣለው በጎ የለውጥ መሠረት ላይ ኹላችንም የድርሻችንን ጡብ እናኖራለን፡፡

ሰሞኑን የትግራይን ክ/ሃገር በጉልበት የሚመራውና ለትግራይ ሕዝብ ማፈሪያ የሆነው የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን አለቃ ደብረ ጽዮን ወያኔ ለለውጡ ደጋፊ እንጂ እንቅፋት አይደለም በማለት ሲወሸክት ተሰምቷል፡፡ ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም ይሉኸል ይሄ ነው፡፡

  • ጅጅጋ ላይ አብዲ ኢሌ የተባለ ወፈፌ ከፈጸመው ግዙፍ ጥፋት በስተጀርባ የሕወሓት አመራሮች እጅ እንዳለበት ማጋለጡ፤ ‹የፌዴራሉ መንግሥት› የመከላከያ ኃይል ወደዚህ ክ/ሀገር (ኦጋዴን) ሲገባ ሕወሓት ያሰማው ተቃውሞ፤ በኦጋዴን ያቀነባበረው ሤራና ዱለት ለመሸፈን በማሰብ ‹ክልል› የተባለውን (ኢትዮጵያን ለመበተንና ለዝርፊያ ያዋቀረውን) የአፓርታይድ ‹ጋጣ› እንደ ‹ፌዴራል› ሥርዓት ቆጥሮ ‹የፌዴራሉን ሥርዓት› አደጋ ላይ የሚጥል ነው እያለ ያደረገው መንጫጫት፤ ለ27 የሽብር ዓመታት የሕግ የበላይነት ጠፍቶ አገርን ለመበታተኛ ያዘጋጀውን የይስሙላ ‹ሕገ መንግሥት› (ሕገ አራዊት) ያላንዳች መሸማቀቅ ሲተላለፍ ኖሮ ዛሬ ላይ የሽብር ዓላማው እንዳይስተጓጎልበት ‹ሕገ መንግሥት› አስከባሪ ለመምሰል ያሰማው የቁራ ጩኸት፤
  • በጉልበት የሚገዛውን የትግራይ ክፍለ ሃገር እንደ አንድ የኢትዮጵያ ግዛት ሳይሆን እንደ ሉዐላዊ አገር ቆጥሮ የሚያወጣው ትእቢትና ንቀት የተሞላበት ዛቻና መግለጫ፤
  • ቀደም ሲልም በቤንሻንጉል፣ በአዋሳ፣ ከቅማንት ማኅበረሰብ ጋር በተያያዘ በጎንደር ወዘተ. ጥቅማቸው የተነካባቸው ዘረኞችን በመጠቀም የፈጠረው ሽብር፤
  • በዝርፊያ ያደለበውን ሀብት በመጠቀም የተዛቡና የሐሰት መረጃዎችን በማሠራጨት፣ ጥርጣሬንና ውዥንብር በመንዛት እየፈጸመ ያለው ሽብር፤
  • በአገር ውስጥና በውጭ በሚቋቋም የብዙኃን መገናኛ ይህንኑ የተዛባ መረጃዎች ለመፈብረክና ለማሠራጨት በኅቡዕና በግላጭ የሚያደርገው እንቅስቃሴ፤
  • በማጅራት መቺ የ‹እንከባበር› ቋንቋ ወንበዴው ቡድን የኖረበትን የአገር ሀብት ዝርፊያ ለመቀጠል ካልቻለ ኢትዮጵያን ከመበታተን ወደኋላ እንደማይሉ ራሱ ደ/ጽዮን በይፋ ያደረገው ንግግር፤
  • ከሥልጣን የተባረሩት የውሸት ‹ጄኔራሎች› መለ መሽገው ሕዝብ የደገፈውንና የተቀበለውን የለውጥ አመራር ላይ የትግራይ ሕዝብ ንብረት በሆነ ቴሌቪዥን ሲያሰሙት የነበረውን ዛቻና ድንፋታ ወዘተ.

ምን እንበለው? ኢትዮጵያ ታላቅ አገር እንጂ እነሱ እንዳሰቧት የአእምሮ ድንክዬዎች መጫወቻ አትሆንም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እስከ የሌለውን ድንቁርና፣ ግበረ ገብ አልባነት፣ ዘረኝነት፣ ንቅዘት፣ ቅጥፈት፣ ወስላታነት፣ አጠቃላይ ማኅበራዊ ድቀት በወያኔ ይብቃ ብሎ ተማምሏል፡፡

ባለጌም ልጅ ልጅ ነውና በወያኔ መርዛማ ፕሮፓጋንዳ ተመርዘው ዘረኝነት፣ ጥላቻና በመንጋ ስሜት የሚነዱ አንዳንድ ወጣቶችን ኢትዮጵያዊ ያልሆነ፣ ከሰውነት የወረደ፣መረን የለቀቀና እጅግ ጸያፍ ተግባራቸውን በምክር፣ በተግሣፅ፣ በበጎ ሥነ ምግባር ቤተሰብ÷ መምህራን÷ የሃገር ሽማግሌ÷ የሃይማኖት አባቶች÷ እንደ አስፈላጊነቱ በሕግ ጭምር እነዚህ ልጆች መልካም አገር ተረካቢ ዜጋ እንዲሆኑ እናስተምራለን፣ እናርቃለን እናርማለን፡፡ ወያኔ ሆይ! የዘራሁት እንክርዳድ አፍርቷል ብለህ ደስ አይበለህ፡፡ እርምህን አውጣ፡፡

ሁላችንን የሚረብሸን ጉዳይ ቢኖር ይህ ኹከት እየፈጠረ ያለ የማጅራት መቺዎች ቡድን አባላት ጠ/ሚር ዐቢይ በሚመራው የለውጥ አስተዳደር ውስጥ በተለያየ የሥልጣን አካላት ‹በፌዴራሉ መንግሥትም› ሆነ በየክፍላተ ሀገሩ ከላይኛው የሥልጣን ዕርከን እስከ ቀበሌ ድረስ መገኘታቸው ነው፡፡ ስለሆነም ጥንቃቄን መሠረት አድርገው የሚወሰዱ ወሳኝ የፖለቲካ ውሳኔዎች የአገር ደኅንነትና ጸጥታን ለማረጋጋት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት፤

1ኛ/ የወታደራዊና ደኅንነት/ጸጥታ መዋቅሩን ከሕወሓት አባላት የማፅዳቱ ሥራ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በተለያዩ የሚኒስትር መ/ቤቶች ከሚኒስትርነት ማዕርግ እስከ የክፍል ኃላፊነት፤ በመንግሥት አስተዳደር መ/ቤት (ሲቪል ሰርቪስ) ከበላይ አመራር እስከ ታች የሥራ ክፍሎች በኃላፊነት የተቀመጡ፤በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ውስጥም ከላይ እስከ ታች በኃላፊነት ቦታ የሚገኙ፤ የሕወሓት አባላት በሙሉ ደረጃ በደረጃ ከኃላፊነት ማንሳት፡፡ ሕወሓት እንደ ድርጅት ወንጀለኛ ነው፡፡ የፈጸማቸው የወንጀል ድርጊቶች ባገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ የወንጀለኛ መቅጫ ፍ/ቤቶች ጭምር የሚታዩ ናቸው፡፡ የአገርን ደኅንነትና ጸጥታ የማረጋጋቱ አንድ ወሳኝ ርምጃ አድርጌ እወስደዋለሁ፡፡ ምክንያቱም የወንበዴው ቡድን አፍራሽ እንቅስቃሴውን እያደረገ ያለው በወንጀል ከሰበሰበው ሀብት በተጨማሪ እነዚህን የመንግሥት መዋቅሮችና በመዋቅሮቹም ውስጥ ተሠግሥገው በኃላፊነት የተቀመጡትን አባላቱን በመጠቀም መሆኑ ለማንም የተሠወረ አይደለም፡፡

2ኛ/ የወንጀል ፍሬ ሆኖ ሕወሓት በዝርፊያ ያግበሰበሰው ንብረት የኢትዮጵያ ሕዝብ አንጡራ ሀብት በመሆኑ በቅድሚያ እንደ ኤፈርት ዓይነት ድርጅቶችን (ያለባቸውን የባንክ ዕዳ እስከ ሕጋዊ ወለዱ ካስመለሱ በኋላ) በሕግ መውረስና የሕዝብ ሀብት ማድረግ፤ በአገር ውስጥ በኤፈርት ድርጅቶችና በሕወሓት ባለሥልጣናት ስም በባንክ የሚገኝ ጥሬ ገንዘብና ከአገር ውጭ በሚገኙ ባንኮች በሕወሓት ባለሥልጣናት ወይም በቤተዘመዶቻቸው ስሞች በውጭ ምንዛሬ የሸሸው ገንዘብ (ከወዳጅ አገሮችና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር) ተገቢው ማጣራት ተደርጎ እንዳይንቀሳቀስ ከማድረግ ጀምሮ ለባለቤቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተመልሶ ለአገር ግንባታ እንዲውል ማድረግ፡፡

3ኛ/ ሕወሓት እንደ ድርጅት በጫካ ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያና ሕዝቧ ላይ የፈጸማቸው ወንጀሎች ተጣርቶ ባስተላለፋቸው ውሳኔዎች በጋራ፤ የድርጅቱ አመራር እና ተራ አባላት እንደ ግለሰብ የፈጸሟቸው ወንጀሎች ተጣርተው ለፍርድ ማቅረብ፤ በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ ረገድ ፍትሕ የሚጠይቀው ከደደቢት ጀምሮ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን በማዋረድ ተግባር ተሠማርተው የነበሩትን እነ አረጋዊ በርሄን፣ ግደይ ዘርዓጽዮንን፣ በወያኔ ክፍፍል ጊዜ በመለስ ቡድን ተሸንፈው ‹በተቃዋሚ› ስም በተለያዩ ድርጅቶች የተወሸቁትን ( እነ ስዬ፣ ገብሩ፣ ወዘተ.) ይመለከታል፡፡

ዘረኞቹ ወያኔዎች ቁርጡን ልንገራችሁ፤ ሰላማዊውን የለውጥ እንቅስቃሴ እያወክኹ እቀጥላለኹ ካላችሁ ምርጫው የናንተ ነው፡፡ እማዝነው ለመንግሥትነት ሳትበቁ ሱፍ የለበሰ ‹ሽፍታ› ሆናችሁ ወደ ደደቢት እንደተመለሳችሁ ኹሉ፤ ለ‹ሰውነት› ሳትበቁ ወደ ጥልቁ ልትወርዱ ነው፡፡ የትግራይን ሕዝብ እንዳዋረዳችሁት፣ ከወንድምና እህቶቹ ለማለያየት እንደሞከራችሁት ሳይሆን እናንተን በማባረር የወንበዶች ዋሻ አለመሆኑን ታሪክ በመሥራት ኢትዮጵያዊ ክብሩን እንደሚያስመልስ አልጠራጠርም፡፡

Filed in: Amharic