>

የአክሱሟ ጫፍ አቁማዳ ወዴት አለች? (ያሬድ ደምሴ መኮንን)

የአክሱሟ ጫፍ አቁማዳ ወዴት አለች?

ያሬድ ደምሴ መኮንን

< ስመ ጥሩ የኪነ ጥበብ ሠዉ ደበበ ሰይፉ ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ በሚለዉ የግጥም መድብሉ ዉስጥ ከአክሱም ጫፍ አቁማዳ የምትል ዉብ ግጥም አለችዉ፡፡ትግራይ እህል ቸግሮት የወሎ ወገኑ እህል ሰፍሮ እንዲልክለት ባዶ አቁማዳዉን ወደ ወሎ ላከ፡፡ወሎም ጎታዉ ባዶ ነበርና እህል ለትግራይ ወንድሙ ይልክለት ዘንድ ባዶዋን አቁማዳ ለሸዋ ዘመዱ ላከለት፡፡ሸዋም ጎተራዉን ሲፈትሽ ባዶ ሆነበትና የወገኑ ራብ አሳስቦት እህል ይሰፍርለት ዘንድ ለከፋዉ ዘመዱ ባዶ አቁማዳዋን ላከለት፡፡እንዲህ እንዲህ እያለች ያቺ የፈረደባት ባዶ አቁማዳ ሁሉንም ክፍለ ሃገራት ዞራ ዞራ ባዶ እንደሆነች ወደ እህል እንዲሰፈርባት ወደ ትግራይ ተመለሰች፡፡ትግራይም አቁማዳዋ የራሱ እንደሆነች ለይቶ ርሃብ የሁሉም ወንድሞቹ ዕጣ እንደሆነ አዉቆ በትካዜ እንዲህ አንጎራጎረ ይለናል ጋሽ ደበበ

            እኔና ወንድሞቼ ሁላችን ሁላችን

            ከባዶ አቁማዳ ነዉ የሚዛቅ ፍቅራችን!!

            ይህ ነዉ አንድነታችን

            ይህ ነዉ ባህላችን

            ዘመን ማዛጋቱ በየአንደበታችን፡፡

ትግራይ ይሄን ብቻ ብሎ አላበቃም፡፡ይህ የዚያ ዘመን ብካይ እሮሮ ለኋላ ትዉልድ ተረት እንዳይመስል ያቺን ባዶ አቁማዳ ከፍ ካለ ስፍራ ላይ ሊሰቅላት ይወስንና አክሱም ጫፍ ላይ ሰቅሎ አኖራት እንዲህ እያንጎራጎረ፡፡

             እንዳኖረዉ ያሻኛል ይህንን አቁማዳ ከፍ ካለ ስፍራ

             መጥቆ እንደባንዲራ

             ምንም ባዶ ቢሆን በዉስጡ አይጠፋምና የታሪክ አዝመራ፡

አዎ!!ትናንት የትግራይ ህዝብ ከሌላዉ ኢትየጵያዊ ወገኑ ጋር የሚቋደሰዉ ከባዶ አቁማዳ የሚዛቅ ፍቅር ነበረዉ፡፡ይህ ለማተቡ ያደረ ህዝብ ያካፍለዉ ቢያጣ ባዶነቱን ተካፍሎ በፍቅርና በመከባበር ዘመናትን አብሮ መሻገሩ የማይፋቅ ታሪኩ ነዉ፡፡

በዚህ ወቅት በዚች ሃገር ላይ እየሆነ ያለዉ ነገር፣ ትናንት ከትግራይ ዘመዶቻችን ጋር ያቆራኘችን ያቺ የአክሱሟ ጫፍ ባዶ አቁማዳ እዉነት ዛሬም አለችን ብለን እንድንጠቅ ያስገድደናል፡፡ይሄዉና በርካታ የችግር ጊዜያትን ያሻገረን ያ ከባዶ አቁማዳ የሚዛቀዉ ፍቅራችን ምን እንደሰለበዉ ሳናዉቅ በትግራይና በሌላዉ ኢትዮጵያዊ መሃል የጸብ ግድግዳ የቆሞ ይመስላል፡፡

ድሮ ድሮ ባብዛኛዉ ችግራችን አንድ ዓይነት፣ ህመማችንም የጋራ ነበር፡፡ቋንቋችን ቢለያይም መዝሙራችን ግን አንድ ነበር፡፡አንድ ታቦት እንስማለን፡፡ሃዘን ቢደርስብን ባንድ ድንኳን አብረን ሃዘን እንቀመጣለን፡፡ስንታመም እንጠያየቃለን፡፡እሳት እንጫጫራለን፡፡ዕቃ እንዋዋሳለን፡፡ኧረ ዕቃ ብቻ አይደለም ዙፋንና ዘዉድም ስንዋዋስና ስንወራረስ ኖረናል፡፡

ዛሬ ያቺ ለዘመናት ኢትዮጵያዉያን በሞላ እህል ተቃምሶ ለማደር ሲቀባበላት የነበረችዉ ባዶ አቁማዳ አክሱም ጫፍ ላይ የለችም፡፡በትግራይ ህዝብ እቅፍ ዉስጥ ያደገዉ ህወሃት የተባለ ድርጅት የትግራይን ህዝብ ከሌላዉ እትዮጵያዊ ወንድሞቹ ለመነጠል ሲል ያቺን ባዶ አቁማዳ ከአክሱም ጫፍ ላይ አዉርዶ ደብቋታል፡፡

በዚህም የተነሳ አንድ ማተብ አስረን፣ ባንድ ማህሌት ቀድሰን አብረን እየኖርን ስንክሳሮቻችን ግን ለየቅል እየሆኑብን ተቸግረናል፡፡ቁስላችን ቁስላቸዉ ህመማችን ህመማቸዉ ሊሆን አልቻለም፡፡ለኛ ወንጀለኛ የሆነዉ የእነሱ ጀግና ነዉ፡፡ የእኛ ጠላት የእነሱ ወዳጅ ነዉ፡፡ የእኛ ጭቆና ለነሱ ነጻነት፣የእኛ መታሰር የእነሱ መፈታት፣ የእኛ መሞት ለእነሱ ትንሳኤ የሆነ እስኪመስል ድረስ አንድም የጋራ መሻትና መግባባት በመሃከላችን ጠፍቷል፡፡

በአንድ ክራር ላይ የተወጠርን ክሮች ብንሆንም አንድ አይነት ጥዑመ ዜማ ማፍለቅ አቅቶን ዜማችን ሁሉ እንዳይሆን እንዳይሆን እየሆነ ነዉ፡፡እዚህ ስላንድነት ተወርቶ ሲጨበጨብ ተከዜ ማዶ ደግሞ ስለመበታተን ሲወራ ይደገም ይደገም እያለ የሚያጨበጭብ ትዉልድ ተፈጥሮ እያየን ነዉ፡፡ይሄኛዉ ጫፍ የህወሃትን የግፍ አገዛዝ በቃኝ አሻፈረኝ ሲል፣ የወዲያኛዉ ጫፍ ደግሞ ህወሃት ይግደለኝ እያለ ፍቅሩን ሲገልጽ ይደመጣል፡፡

ዛሬም እንደ ትናንት የትግራይ ህዝብ ጎተራ እንደ ሁሉም ኢትዮጵያዉያን ጎተራ ኦና ሆኖ ሸረሪት ያደራበት ቢሆንም፣ የትግራይ ህዝብ ግን በባዶ ሆዱም ቢሆን የአብራኬ ክፋይ ከሚለዉ ወያኔ ጋር በቁርባን ለመተሳሰር የቆረጠ ይመስላል፡፡ለዚህም ነዉ እስካሁን ድረስ የትግራይ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ ህወሃትን በድፍረት ተዉ ተሳስተሃል ብሎ ለመገሰጽ ያልደፈረዉ፡፡  

ለዘመናት አስተሳስራን የኖረችዉን የአክሱሟን ጫፍ አቁማዳ የማያዉቀዉ የወያኔ አዲሱ ትዉልድ ከባዶ አቁማዳ ሲዛቅ ስለነበረዉ ፍቅራችን የሚነግረዉ አጥቶ ራሱን በተንሸዋረረ መነጸር ለማየት ተገዷል፡፡ወይም ይሄ ታሪክ ተረት ተረት መስሎታል፡፡በዚህም የተነሳ ራሱን የወርቅ ፍልቃቂ ሌላዉን ደግሞ ዉዳቂ አድርጎ እንዲያይ እየተገፋ ነዉ፡፡ካንተ ወዲያ ጀግና ላሳር ነዉ ተብሎ እየተነገረዉ ከራሱ ወገን ላይ ኧረ ጎራዉ ብሎ እንዲፎክር እየተደረገ ነዉ፡፡  

ይህ ሁሉ እየሆነ ያለዉ ይህ ትዉልድ ያቺ የዘመናት ታሪካችን አሻራ ያረፈባትን፣ ከባዶ የተዛቀ ፍቅራችንን ቋጥረን ያስቀመጥንባትን የአክሱሟ ጫፍ አቁማዳን ለማየት ስላልታደለ ይሆን?

ለማንኛዉም አዲሱ ትዉልድ ያቺን የታሪክ አዝመራ ቋጥራ የያዘችዉን የአክሱም ጫፍ አቁማዳ ህወሃት ከደበቀበት ፈልጎ አዉጥቶ ታሪኩን መፈተሽና ማወቅ ቅድሚያ ሊሰጠዉ የሚገባ ተግባሩ ሊሆን ይገባል!!

ደበበ ሠይፉ ከ43 ዓመታት በፊት ዘመንን ተሻግሮ በዚች ሃገር ዛሬ የሚከሰተዉ ነገር የተገለጠለት የገጣሚነት ካባ የደረበ ነብይ ሳይሆን ይቀራል? ነብስ ይማር፡፡

Filed in: Amharic