>

ሀገር መገንባት እንደማፍረስ ቀላል አይደለም! (ሙሀመድ አሊ ሞሀመድ)

ሀገር መገንባት እንደማፍረስ ቀላል አይደለም!

ሙሀመድ አሊ ሞሀመድ

እምዬ ምኒልክ አገር ሠርተው ሰጥተውናል። አገር መሥራት ታሪኩን እንደማንበብ ቀላል አይደለም። አበው ሲተርቱ “ለተቀማጭ ሰማይ ቅርብ ነው” እንዲሉ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ሂደቱን መተቸትም ሆነ እምዬ ምኒልክን መክሰስ ቁልቁለት የመውረድ ያህል ቀላል ነው። ሀገርን ለማፍረስ መንደርደርም አፍራሽ አስተሳሰብን እንጅ የተለዬ ጥበብና አርቆ አስተዋይነትን አይጠይቅም። ጠባብ ብሔርተኝነትን ማቀንቀንና “እኛና እነሱ” መባባል ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል።

በምኒልካዊ መንፈስ ነገን አሻግሮ ማዬትና የሀገር አንድነትን ማጠናከር ግን ቁልቁለቱን እንደመውረድ ቀላል አይደለም። በልዩነቶች መሐል የህዝብን አንድነት መስበክና ጠንካራ ሀገር መገንባት አቀበቱን ከመውጣትም በላይ አድካሚና እልህ አስጨራሽ ነው። የአባቶቻችንን ልብ; ገንቢ አስተሳሰብና ሀገራዊ ራዕይ መውረስ; ክፍተቶችን መሙላትና የራሳችንን አሻራ መጨመር አስተዋይነት ነው። ገንቢ ሥራዎቻቸውን ሳንመዝን ከመሬት ተነስቶ አበውን መውቀስና መክሰስ ውለታቢስነት ነው። ከዚያም ባለፈ በአባቶች ደምና አጥንት የተገነባውን ለማፍረስ መቃጣት የለየለት እብደት ነው። ውጤቱም ለትውልድ የሚተላለፍ ፀፀት ነው። ስለሆነም ነገ እኛ በፀፀት የምንገረፍበትን; ልጆቻችንና የልጅ-ልጆቻችን ደግሞ በቁጭት የሚያዩትን ታሪክ እንዳንሠራ; ብሎም በታሪክ ተጠያቂ እንዳንሆን መጠንቀቅ አለብን።

ዘላለማዊ ክብር ለእምዬ ምኒልክና ለባለቤታቸው ለእቴጌ ጣይቱ!!!

ኢትዮጵያ በልጆቿ አንድነት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!!

Filed in: Amharic