>
5:13 pm - Saturday April 19, 9783

ሶማሊያን ማን በታተናት? (ዳግማዊ ኡመር ፋርዳ)

ሶማሊያን ማን በታተናት?
ዳግማዊ ኡመር ፋርዳ
ሠላም ክቡራትና ክቡራን ፤ሠላምታው ባንዳ የባንዳዎች ልጆችን አይመለከትም! ለ 27 ዓመታት እኛን እና የኤርትራን ሕዝብ አግልለውን ነበር፤ አሁን ደግሞ ለዘለዓለም እኛ እናገላቸዋለን! ብድር በምድር ይለዋል እንዲህ ነው!!! መቼም ዛሬ ሊቀሠይጣን መለስ ዘናዊ መሞቱ ይፋ የሆነበት 6ኛ ዓመታት መታሰቢያ ቀን ነው፤ እርግጥ ነው መለስ ዜናዊ የሞተው ክቡር ሰማዕት ፕሮፌሰር፣የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አባባ አስራት ወልደየስ ተሰቃይተው እንዲሞቱ ያደረገ ቀን ነው!! ብዙ ግፍ ሰርቶባቸው ነው የሞቱት አባታችን፤ ለመላው አማራ ሕዝብ ሰው የጠፋ እለት ሰው ሆነው የተገኙ አባታችን ናቸው!!! ዛሬ መለስ ዘናዊ መሞቱ ይፋ የሆነበት ታስቦ የሚውልበት ቀን ነው፤ እኛ ግን በእሱ ፈንታ፣ ክቡር ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም ከሰሯቸው እልፍ መልካም ሥራዎች መሀል፣ ለዛሬ አንድ ብዙዎች የዘነጉት ከባድ ሥራቸውን በጥቂት እናስታውሳለን።
ሶማሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ግዜ፣ ሕዝባዊ እና አብዮታዊ ሠራዊቱን ከሶሻሊስት ኩባ እና የመን ከተላኩት ወታደሮች ጋር በማቀናጀት የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ በመግባት ወረራ የፈጠመውን የሶማሊያ ግዙፍ እና ጠንካራ መከላከያ ሠራዊት ድባቅ ተመታ፤አብዛኛው በኦጋዴን ምድር ላይ ተደመሰሰ!  ከመማረክ የተረፈው ፈሱን እየፈሳ ሞቃዲሾ ሸሽቶ ገባ፤ ይህ አሳፋሪ ሽንፈት በሶማሊያ ፖለቲከኞች እና ባለሥልጣን መሀል ከባድ አለመግባባት እና አለመተማመን አመጣ፤ በርካታ መኮንኖች ዘብጥያ ወረዱ፤ ይህ ሁኔታ ለኢትዮጵያ መንግሥት ደርግ ሶማሊያ ዳግመኛ ኢትዮጵያን እንዳትወር እና እንዳትቸናኮል አድርጎ ለመበታተን ምቹ ሁኔታ አመጣ፤የደርግ ከፍተኛ ሹሞች ለስብሰባ ተቀመጡ፤ በሶማሊያ መንግሥት ላይ ተቃዋሚዎችን እንዴት እናደራጅበት በሚል ሀሳብ! በመጨረሻም አንድ ውሳኔ ላይ ደረሱ፤ በውጪ አገራት ለሚኖሩ የዚያድባሬ ተቃዋሚዎች “ኢትዮጵያ ማንኛውም ስንቅ እና ትጥቅ ታቀርባለች፤ ሙሉ ወታደራዊ ሥልጠና ትሰጣለች ” የሚል መልዕክተኛ በመላክ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ዚያድባሬን እንዲወጉ ይደረግ የሚል!!  በዚህ ላይ እንዳለ፣ የሶማሊያ ሠራዊት አዛዥ የነበሩትና፣ በባሌ ክፍለሀገር በኩል በባንዳው ዋቆ ጉቱ መሪነት ገብቶ በዜጎቻችን ላይ ከባድ ጭፍጨፋ አድርጎ የነበረው፣ በኋላም ሠራዊቱ እንዲደመሰስ አድርገዋል ተብለው ታስረው ከተለቀቁ በኋላ ወደ ኬንያ የተሰደዱት  ኮሎኔል ዐብዱላሂ ዩሱፍ ከ 7 ሌሎች ከፍተኛ መኮንኖች ጋር ናይሮቢ እንደሚገኙ ደርግ መረጃዎች ደረሱት፤ ደርግ በፍጥነት ናይሮቢ ለሚገኘው የደህንነት ክፍል ኮሎኔሉ ከጓዶቻቸው ጋር በፍጥነት ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ እንዲያደርግ መመሬያ ተሰጠው፤ በመመርያው መሠረት የደህንነት ክፍሉ ኮሎኔሉን ከጓዶቻቸው ጋር ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ አደረገ፤ ኮሎኔል ዐብዱላሂ ዩሱፍ እና ከጓዶቻቸው አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ ግዜ ሳይጠፋ ከፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም ጋር እንዲገናኙ ተደረገ፤ ሶማሊያን የመበታተን ከባዱ ሥራ ያኔ ሀ ብሎ ተጀመረ፤ ከብዙ ውይይት በኋላ ኮሎኔል ዐብዱላሂ ጠቅላላ የዚያድ ባሬን ተቃዋሚ አሰባስበው አንድ ጠንካራ ድርጅት እንዲመሠርቱ፣ መንግሥት ማንኛውም እገዛ እንደሚያደርግ አስረግጠው ነግረዋቸው ከሥምምነት ላይ ደረሱ።
ይህንን ተከትሎ ተቃዋሚዎችን የሚያሰባስ፣ የሚያስተባብር ኮሚቴ ተቋቋመ፤ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም ይህንን ኮሚቴ እንዲመሩ ተመረጡ፤ የደህንነት፣መከላከያ፣ ጤናጥበቃ እና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች የኮሚቴው አባላት ሆነው ተሰየሙ፤ ብዙ ቴክኒካል ኮሚቴዎች ተቋቋሙ፤ ኮሎኔል ዐብዱላሂ ድርጅት  የማደራጀት ሥራቸውን ጀመሩ፤ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚገኙ ተቃዋሚዎችን መልዕክት በመላላክ አሳምኖ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ አደረገ፤ 1971 አጋማሽ ላይ የድርጅቱ መሥራች ጉባኤ ተካሄደ፤ “የሶማሊያ አዳኝ ዴሞክራሲያዊ ግንባር” (SSDF,  Somalia Salvation Democratic Front) የሚል ስያሜ ተሰጠው፤ ድርጅት የነበረው ወደ ግንባር ተቀየረ፤ ኮሎኔል ዐብዱላሂ ዩሱፍ የድርጅቱ መሪ ሆኖ ተመረጠ፤ ወዲያውኑ ከኢትዮጵያ ወደ መላው ሶማሊያ የሚሰራጭ “ኩልሚስ” ነጻ አውጪ የሚባል ራድዮ ጣብያ ተቋቁሞ በሶማሊ ቋንቋ ፕሮፓጋንዳ መርጨት ጀመረ፤ በዚህ ሬድዮ ጣብያ የሚሰራጨው ፕሮፓጋንዳ የሶማሊያን ሕዝብ አነቃነቀው፤ ሕዝቡ ዚያድባሬ ላይ ጥላቻ ማሳደር ጀመረ፤ የሶማሊያ ሰደተኞች ድንበር አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ መጉረፍ ጀመሩ፤ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ መምሪያ ለሶማሊያ ስደተኞች የምግብ፣መጠለያ እና ምግብ ማቅረብ እስኪሳነው ድረስ ስደተኞች ኢትዮጵያን አጥለቀለቋት፤ ይህ የስደተኞች መጉረፍ ለግንባሩ ሠራዊት ለመልመል ምቹ ሁኔታን አመጣ፤ወጣቶችን አለምንም እክል መለመለ፤ የተመለመሉት አብዛኞቹ ወጣቶች የ “መሪሃን” ጎሳ አባት ነበሩ፤ የግንባሩ የፖለቲካ ክፍል በተለያዩ ውጪ አገሮች በመጓዝ እና ከዜጎች ጋር በመገናኘት ምድር አንቀጥቅጥ የተቃውሞ ሰልፍ በዚያድባሬ መንግሥት ላይ እንዲካሄድ አደረገ፤ ከፍተኛ የገንዘብ መዋጮም አሰባሰበ።
 በዚህ ደረጃ ላይ እያሉ፣ የተመለመሉ ወጣቶች ወታደራዊ ሥልጠናቸውን አጠናቀው ጥቃት ለማድረስ ዝግጁ መሆናቸው እንደተረጋገጠ፣ ዚያድባሬ በመሪሃን ክልል ውስጥ አስፍሮት በነበረው ሠራዊት ላይ የመጀመሪያው የሽምቅ ውጊያ ተደረገበት፤ ውጊያው ቀስበቀስ መላው ሶማሊያን አደረሰ፤ የሶማሊያ አዳኝ ዴሞክራሲያዊ ግንባርን እንቅስቃሴ በቅርበት ይከታተሉ የነበሩት የሰሜን ሶማሊያ ተወላጆች በአገረ እንግሊዝ “የሶማሊያ ብሔራዊ ንቅናቄ “(Somalia National Movement)  በመባል የሚታወቅ ድርጅት መመሥረታቸው ተሰማ፤ ንቅናቄው ከግንባሩ ጋር ኅብረት ሰርቶ የሶማሊያን መንግሥት ለመውጋት እንደሚፈልግ ለኢትዮጵያ መንግሥት አሳወቀ፤ በጉዳዩ ላይ ለመምከር የንቅናቄው ሁለት መሪዎች 1972 ላይ ከመንግሥት ጋር ለመምከር  አዲስ አበባ ገቡ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በሰፊው አነጋገራቸው፤ ስለሚያደርግላቸው ድጋፍ ገለጠላቸው፤ በኋላም ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲንቀሳቀሱ ፈቀደላቸው፤በዚህ ግንባሩ እና ንቅናቄው ተባብረው ቀንደኛ ጠላታቸው የሆነውን የሞቃዲሾ መንግሥትን ለመውጋት ውል አሰሩ።
ከዚያም አባሎቻቸውን ከየቦታው አስመጥተው፣ ከሴደተኞችም መልምለው በአነስተኛ ደረጃ በሰሜን ሶማሊያ መንግሥት ላይ የሽምቅ ውጊያ ማካሄድ ጀመሩ፤ በሁለቱ ድርጅቶች ከሊቢያው መሪ ሙአመር አልቃዛፊም ከፍተኛ ድጋፍ ተደረገላቸው፤ መሪዎቹንም ወደ ትሪፖሊ ጠርተው አነጋገሯቸው፤ በሚሊዮኖች ዶላሮች የሚያስወጡ ቀላል እና ከባባድ መሣርያዎችን ላኩላቸው፤ በኢትዮጵያ መንግሥት የሚደገፉት ተቃዋሚ ኃይሎች በየአቅጣጫው የዚያድባሬ ሠራዊት ላይ ከባድ ድልን ነሱ፤ በርካታ ከተሞችን፣ቁልፍ ቦታዎችን ተቆጣጠሩ፤ የተቃዋሚዎችን ድል የተመለከቱት የጎሳ መሪዎች ጦራቸውን ከተቃዋሚዎች ጋር ቀላቅለው ዚያድባሬ ላይ መዐት አወረዱበት፤ ዚያድባሬ እብድ ሆነ፤ ሰማይ ምድር ተደፉበት፤ የራሱ ጀነራሎች እየከዱት ወደ ተቃዋሚዎች ተቀላቀሉ፤ዚያድባሬ ተስፋ ቆረጠ፤ ቀኑ እንደጨለመበት ሲገነዘብ ቤተሰቡን ጠቅልሎ ስደት ወጣ።
 ኢትዮጵያን በሶስት ክፍላተሀገር በመውረር እና በማጥፋት ታላቋ ሶማሊያን ለመመሥረት የተነሳው ዚያድባሬ፣ 1983 እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ከሥልጣን ተወገደ፤ተሰደደ፤ ሶማሊያ ብትንትኗ ወጣ! የሶማሊያ ብሔራዊ ንቅናቄ  ሐርጌሳን ዋና ከተማው አድርጎ ሰሜን ሶማሊያን ገንጥሎ ሪፐብሊክ መንግሥት መሠረተ፤ ይህ አገር እንግሊዝ ቅኝ ስትገዛው”ሶማሊላንድ” ብላ ስትጠራው የነበረው ነው፤ ፑንትላንድ እየተባለ የሚጠራውን የቀንዱን ክፍል የታጠቁ የጎሳ መሪዎች ገንጥለው ቦሳሶን ዋና ከተማ በማድረግ ነጻ መንግሥት መመሥረታቸውን ይፋ አደረጉ፤በኮሎኔል አይዲድ የሚመራው ኃይል ደግሞ የመላው ሶማሊያ መንግሥት ብሎ ራሱን ሰይሞ ሞቃዲሾ ላይ መሠረተ፤ ከሥር ምስሎቹን የምንመለከተው የሶማሊላንድ መከላከያ ሠራዊት ነው፤ ከአየር ኃይል ውጪ ዘመናዊ ሠራዊት አለው፤ እጅግ ዘመናዊ ባህር ኃይልም አለው፤ ለዛሬዎቹ ሶማሌላንድ እና የፑንትላንድ መንግሥታት እንዲመሰረት የደርግ መንግሥት ትልቅ ሥራ ሰርቷል፤ የደርግ መንግሥት የዚያድባሬን መንግሥት በመፈንገል፣ ሶማሊያን ለዘለዓለም በመበታተን ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ወንበዴዎች ወረራ ለዘለዓለም ሠላም እንድትሆን ዘመን አይሽሬ ሥራውን በታሪክ መዝገብ ላይ በደማቁ አስፍሯል፤ አጅሬው የክፋት ባለ ራዕዩ መሪ መለስ ዜናዊ ሞቃዲሾ መሽጎ ኢትዮጵያን በሶማሊያ ማስወጋቱ ሳያንሰው፣አሰብ ወደብን እና ኤርትራን ከኢትዮጵያ በማስገንጠል ለዘለዓለም በክፉ ሲታወስ ይኖራል፤ደርግ ደቡብ ሱዳንን እንዴት አድርጎ ከሱዳን እንደገነጠላት በሌላ ግዜ እንመለከታለን ኢንሻአላህ።
Filed in: Amharic