>

ዝክረ መለስ እና የተ.ሓ.ህ.ት. ያረጁ ያፈጁ ራዕዮች ! (አሰፋ ሃይሉ)

ዝክረ መለስ እና የተ.ሓ.ህ.ት. ያረጁ ያፈጁ ራዕዮች !
አሰፋ ሃይሉ
 – ፅዮናዊነት እና አንዳንድ ሀገርኛ ኮንስፓይረሲ-ነክ ትወራዎች!
«More often than not, it appears that history of the past may be the only available choice we have at hand to explain history of the present.»
                       – Ralph Waldo Emers
«ተ.ሓ.ህ.ት. ፅዮናውያንና ኢምፐርያሊስቶችን በተለይም የአሜሪካ ኢምፐርያሊስቶችን በመቃወም ላይ ከሚገኙት ፍልስጤማዊያንና የዐረብ ህዝቦች ጋር ግንኙነቱን ያጠናክራል!»
 (– የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ድርጅት መግለጫ
(የህወሓት ማኒፌስቶ)፣ የመጀመሪያ እተም፣ 
  በየካቲት ወር 1968 ዓ.ም.፣ ገጽ ተሓህት 38፡፡)
ከላይ የቀረበው – የዛሬ 42 ዓመት – በተ.ሓ.ህ.ት. የወጣ – የፍልስጥዔም-ዐረብ አጋርነት ማኒፌስቶ ነው፡፡ ያ የሆነው በየካቲት ወር 1968 ዓመተ ምህረት ነበር፡፡ አሁን ግን እነሆ በወርሃ ነሐሴ 2010 ዓመተ ምህረት ላይ እንገኛለን፡፡ አንባቢዎች ሆይ – እንኳን ወደ ትዕግስት አስጨራሹ ታሪካዊ ጽሑፌ ጅማሮ – በሠላም መጣችሁ!
ትክክለኛው ህልፈተ ጊዜያቸው «ወርሃ ነሐሴ ነው!» በሚሉ እና የለም ትክክለኛ ህልፈተ-ወቅታቸው «ወርሃ ሐምሌ ነው!» በሚሉት መካከል ሰሞኑን የሰፈነውን አተካሮ ለጊዜው ወደጎን አቆይተነው – ሰሞኑን ግን – የቀድሞው የህወሓት ሊቀመንበርና የሀገሪቱ ጠ/ሚ የአቶ መለስ ምውት ዓመት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ሲዘከር ነው የሰነበተው፡፡
«ሲዘከር» ወይም ሲታወስ ስል ግን – የዝክሩ ዓይነት- በሁለት ተቃራኒ ስለቶች በኩል የተሞረደ መሆኑ ልብ ይባልልኝ፡፡ በአንድ በኩል አክባሪዎቻቸው – እንደወትሮው በብሔራዊ ደረጃና በሀገሪቱ መሪዎች የአቶ መለስ ስም ከፍ ከፍ እየተደረገና በታላቅ ብሔራዊ ደረጃ ባይሆንም – ስማቸውን በክብር ሲዘክሩላቸው ነበር፡፡ የአቶ መለስ ራዕዮችም – ከመጽሐፍ ቅዱሱ የዮሐንስ ራዕይ ባልተናነሰ – ሲዘከሩላቸው፣ ሲወደሱላቸውና ህያውነታቸው ሲመሠከርላቸው ነበር፡፡ ይሄ አንደኛው – ከአቶ መለስ ህልፈት ጀምሮ ላለፉት ዓመታት ካንድ ወገን ሲሰማ የነበረው «ኦፊሺሴላዊ ቨርዥን» ነው፡፡ ሌላኛውስ «ሪቮኬቲቭ ቨርዥን»ስ?
ሌላኛው ቨርዥን ደግሞ – ያን የህወሓታውያን (ወይም «ኢህአዴጋዊ») የራዕይ ትርክትና የምስጋና ዝክር የማይቀበለው – በተቃራኒው የዝክሩ ስለት በኩል ቆሞ የምናገኘው – በተለይ ይሄንኑ የምፅፍበትን መድረክ ጨምሮ የተለያዩ ዓለማቀፍ ማኅበራዊ ድረገጾች ሲንፀባረቅ የነበረው – ውጉዝ-ወ-መለስ ዝክር ነው፡፡ በዚህኛው ጎራ – የአቶ መለስ ሙውት ዓመት የተዘከረው – ባጭሩ – በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ላይ – ከፍተኛ የውግዘት መዓት በማውረድ ነው፡፡
«መለስ መሪ ሣይሆን መሠሪ ነው!» ይል ነበር አንድ በብዙዎች ዘንድ የናኘ ማህበራዊ «ፖስት»፡፡ አንዳንዱም «መለስ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መልካምን ነገር ያደረገው መሞቱ ብቻ ነው!» ይላል ደግሞ ሌላው ፅንፍ፡፡ አጃኢብ ነው ብቻ – ሁለት ሶስት ቦታ የተከፈለ ሀገር – የጋራ ጀግና፣ የጋራ ጠላት የሌለው ሀገር ሆነን እንዲህ እስከመቼ በተቃራኒ ፅንፎች እንደነጎድን እንደምንኖር – ሳስበው ግርም፣ ግን ደሞ ጭንቅም ይለኛል!! ምን ያለው ንግርት ይሆን የያዘብን?
እና እንዲህና እንዲህ የመሳሰሉ – በጥልቅ ከታዩ ደግሞ – የውርጅብኝ ቃላቱና የውጉዝ-ከመአርዮሶቹ አሰነዛዘር – የሞተውን መሪ ለማውገዝ ያለሙ ከሆኑት በላይ – ወይም ቀጥተኛ ዒላማቸው ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ሣይሆን – መልዕክቱና ውግዘቱ ሁሉ – አሁን ያሉትን የእርሱን «ሌጋሲ» እናስቀጥላለን የሚሉትን እና ለእርሱ አምልኮታዊ ክብር የሚሰጡትን – በነገር ለመሸንቆር፣ ጀግናችን ይለያያል የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ፣ ለመበሻሸቅ፣ እና ብሎም አሁን ላሉት የአቶ መለስ «ሌጋሲ» ተከታዮች የተላለፈ የተቃውሞ መልዕክት ይመስላል! አሊያም – አሁን – የእርሱ ጊዜ – አክትሟል – የሚልን መልዕክት ለማስተላለፍ – በቀደመው መልኩ ከዚህ በኋላ ልንጓዝ አንፈቅድም የሚልን ጠንካራ መፈክር ለማስተላለፍ የሚሞክሩ ዓይነት ይመስላሉ፡፡
እንግዲህ እኔም እንዳቅሚቲ ደግሞ «እኔስ በምን ልገንባ? ምንስ ቅርስ ላኑር?» የሚል የመዘከር ስሜት ነሸጠኝ፡፡ የድርሻዬን ለመዘከር፡፡ በእርግጥ «መዘከር» ማስተወስ፣ ማሰብ፣ እና ምናልባትም ደግሞ ስሙን እያነሱ ማወደስም የሚል ትርጉም ሊኖረው ይችላል፡፡ እኔ ደግሞ ከመዘከር ይልቅ ማማትን መረጥኩ፡፡ ማማት፡፡ «አማ» ማለት «ሰውን በሌለበት ስሙን አነሣ» ማለት ነው አይደል የሚሉት አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ ባማርኛ መዝገበ-ቃላታቸው?! ስለዚህ እኔም ልማቸው አቶ መለስን፡፡ ማለትም – በክፉም ሆነ በበጎ – ስማቸውን በሌሉበት ላንሣ – እንደማለት፡፡
ተጠቃሹ በሌሉበት ቢሆንም ቅሉ ስማቸውን የምናነሳው – ከእርሳቸው ጋር የነበሩ ብዙ ሰዎችም – በአንድ ላይ በወል ‹‹መለስ›› በሚለው ስም ሥር ሊካተቱ እንደሚችሉ እያሰብን ነው ታዲያ – ጉዞ ማማታችንን የምንጀምረው፡፡ ሀሜቴን የምጀምረው በአቶ መለስ ‹‹ራዕይ›› ላይ ነው፡፡ እና እርሳቸው እርግጥ የሆነ ራዕይ አላቸው ወይ ለመሆኑ የሚል መንደርደሪያ ጥያቄን በመጠየቅ፡፡
አቶ መለስ የህወሓትን ምሥረታን ተከትሎ ያሳደሩት “ብሔራዊ” ሊባል የሚችል ሀገራዊ «ራዕይ» ግን ምንድን ነበር ሊባል ይችላል? በበኩሌ – እርሳቸው (እና ጓዶቻቸው) – አንድ ተለይቶ የሚታወቅ ሀገራዊ ራዕይ ነበራቸው – ወይም አላቸው ከተባለ – በቃ እርሱ – ያ ለረዥም ዘመን ሲያቀነቅኑት የቆዩት – ሶሻሊስታዊ ራዕይ ነው!! ያ እና ያ ብቻ!!!! ያን ሳስብ – እና በጊዜ ሂደት የተለወጠውን ሁሉ ሳስብ ደግሞ – እርሱስ ቢሆን አለ በእውን ወይስ የለም? ብዙዎች ተጠያቂዎች ግራ ይጋባሉ፡፡
ብዙዎች ‹‹አብዮታዊ ዲሞክራሲ›› የሚባለው ነገር እኮ ያን ግራ የተጋባ – የቀድሞ እና የአሁን ራዕይ ባንድ አጣምሮ ለመግለጽ – በባለራዕዮቹ በእነ አቶ መለስ በሥራ ላይ የዋለ ቃል ነው – ይላሉ፡፡ የምር ግን – ለረዥም ዓመታት ሰዎችን ነፍጥ አስነግቦ ያጫረሰውን ያን ነባር ራዕይ ጠለቅ ብሎ ላየው – ከ83 በኋላ የተከሰተው – እና አሁንም – እና ወደፊትም የሚኖረው ‹‹ራዕይ›› የምር – ግርርም ሊለው ይችላል፡፡ በበኩሌ ግርርርርርም ብሎኝ አላባራም – ሁልጊዜ፡፡
አሁን ወደ ‹‹አቶ መለስ ራዕይ›› አለ ወይስ የለም? ወደሚለው – ታማልዳለች ወይስ አታማልድም? እንደሚለው – አይሁንብንና – እስቲ ወደ ራዕዮች ጉዳይ በጥቂቱ እንጫወት፡፡ በእርግጥም በብዙዎች ሲባል እንደሚሰማው – አቶ መለስ ዜናዊ – ሥር የሰደደ እና ለብዙ ጊዜ እንደ ዓይነተኛ ሀገራዊ ራዕይ ያገለገለ – አንድ የሚታወቁበት ራዕይ ነበራቸው ከተባለ – በእርግጠኝነት ያ – በያኔው ተ.ሓ.ህ.ት – ወይም ህወሓት – ጅማሮ ላይ – ያነገቡት – እና ሊሞቱ-ሊገድሉ የተነሱለት – ያ ራዕይ – የዓለም ተራማጆች – ወይም የዓለማቀፋዊ ሶሻሊስቶች – ሦሻሊስታዊ ራዕይ ነበር – ብንል ከእውነቱ ብዙም ፈቀቅ አያደርገንም፡፡
ማለትም የጭቁኑን ወዛደራዊ መደብ አሸናፊነት፣ እና የከበርቴውንና ሪአክሽነሪውን ኢምፔሪያሊስት መደብ መቃብር መግባት – እነዚህን ራዕዮች አንግበው ነበር – ወደ ትጥቅ ትግላቸው – ከጓዶቻቸው ጋራ – የተቀላቀሉት – አቶ መለስ፡፡ እና ራዕይ ካለ – ያለው አንድ ራዕይ – ያ ራዕይ ነው – ብለን ብናምንስ?! – መብታችን!!
ምናልባት የሚከተሉትን የተ.ሓ.ህ.ት መፈክሮች – በእርግጠኝነት – በእሣትና አረር መሐል ሆነው የ«ደርግ»ን ሥርዓት በተፋለሙባቸው ዓመታት ሁሉ – ራሳቸውም ደጋግመው ፎክረዋቸዋል – ሌሎችንም እንዲፎክሩባቸው አስተጋብተዋል – እና  የአቶ መለስ ራዕዮችም ነበሩ ብንል – ከእውነታው ብዙ መራቅ አይሆንብንም፡፡ ለ17 እና ከዚያም ለበለጡ ዓመታት – ምናልባት – የአቶ መለስ – እና ተከታዮቻቸው – ታላላቅ ራዕዮች የነበሩትን እስቲ የ1968 ዓመተ ምህረቱ የህወሓት ማኒፌስቶ መደምደሚያ ቃሎች እንዲህ ለታሪክ ተከትበው እናገኛቸዋለን፡-
«5- ለዲሞክራሲና ለህብተሰብዓዊ ዕድገት በመታገል ላይ ለሚገኙት የላቲን አሜሪካና የኢስያ ህዝቦች ያልተቆጠበቀ የሞራል ድጋፉን ይሰጣል፡፡
«ፋሽሽታዊ ደርግ ይውደም!
«ኢምፐርያሊዝም ይንኮታኮት!
ድምቀት ለዓለም ተራማጅ ሃይሎች!
የትግራይ ህዝብ ትግል ያሸንፋል!!»
(– የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ድርጅት መግለጫ (የህወሓት ማኒፌስቶ)፣ የመጀመሪያ እተም፣ በየካቲት ወር 1968 ዓ.ም.፣ ገጽ ተሓህት 39)
እንግዲህ የአቶ መለስ ታላቁ ራዕይ ያ የዘመኑ ሶሻሊስቶች ታላቅ የጭቁኖች መፈክር ሆኖ – ነገር ግን ያም «ሎካላይዝ» ተደርጎ ወደ ትግራይ ጭቁኖች ወርዶ እናገኘዋለን፡፡ ያንንም የሌሎች ጭቁን ብሔሮችም ጭምር መፈክር እንዲሆን ነበረ – ታላቁ – ምናልባትም በአመዛኙ የተሣካላቸው – የአቶ መለስ ታላቁ ራዕይ፡፡
ይሄን የአቶ መለስ ራዕይ – ምን ያህል ከትግራውያን «ጭቁን» ሕዝቦች አልፎ – ለሌላውም የተረፈ ሶሻሊስታዊ ራዕያቸውን የምንገነዘበው – በአንድ ወቅት – የህወሓትን «አንጃ» ቡድን ተቀላቅለዋል በሚል ጥርጣሬ የአቶ መለስን ውግዘት ማስተናገድ የከበዳቸው የቀድሞው ፕሬዚደንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ – «ሦስተኛውን አማራጭ ተቀብያለሁ!» ብለው – ምክር ቤቱን ረግጠው ለመውጣታቸው ዋነኛ ምክንያት አድርገው የሚያቀርቡት «እኔ ኢህአዴግ ከሦሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም ማፈንገጡን አላውቅም ነበር፣ እና ከዚያ ርዕዮተ ዓለም ማፈንገጡን ማወቄ ለእኔ የመጀመሪያው ግንባሩንና ሥልጣኔን እንድለቅ ያስገደደኝ ምክንያት ነው!» ሲሉ መደመጣቸውን ስንሰማ ነው!! ወቸ ጉድ?!!
እና አሁን ይህን የማንሳቴ ፋይዳ ምንድን ነው? – ፋይዳውማ – ያ የአቶ መለስ ሶሻሊስታዊ – እና ፀረ-ኢምፔሪያሊስታዊ – ራዕይ – እሳቸው ከተነሱለት ብሔር አልፎ – ከሌሎችም ብሔሮች አንጋፋ ምሁራንን ጭምር ተከታያቸው እስከማድረግ የበቃ ራዕይ እንደነበር – ዓይነተኛ ማሳያ ይሆነናል በሚል ነው፡፡ «እንደነበር» ስልስ? ለምን «እንደሆነው» አልልም? – የማልለውማ –  በነበር ያስቀረሁትማ፤ አቶ መለስ ዜናዊ – ያን ብዙ ተከታይ ያፈሩበትንና – ለበርካታ ዓመታት ነፍጥ አንስተው የታገሉለትን ያን ብቸኛ መለያቸው ሊሆን የሚችለውን – ፅኑ ራዕያቸውን – በጊዜ ሂደት – ከናካቴው ቀይረውታል! – የሚል አመለካከት – ከላይ እንዳየነው ባሉት ምስክርነቶችና – በሌሎችም እማኞች – እና በተግባር ተሞክሮ – በገሃድ ስለተገለጸልን ነዋ!!!!!
እና የአቶ መለስ – የቀረ – ይህ ነው የሚባል – ቁርጥ እና የነጠረ ትክክለኛ ራዕይ – የትኛው ነው? ወይም የትኛው ነን ብለን እንያዘው?! — መልሴ፡- «የዚህ ሠፈር ልጅ አይደለሁም!»
እንዲያውም በቃ – አሁን ያን እንተወውና ሌላ ነገር እንጫወት – ወይም ሃሜታችንን እንቀጥል – ወደ ተረኛው ርዕሰ-ራዕይ ጉዳይ፡፡ ቀጠልኩ፡፡ ሌላው – እና ሁሌም ባየሁት ቁጥር ግርም የሚለኝ – የአቶ መለስ (ወይም የድርጅታቸው) ያፈጀ (የኖረ) ራዕይ – የዛሬ 42 ዓመት በተነደፈውና በተሰራጨው – በህወሓት የውጭ ጉዳይ ማኒፌስቶ ቁጥር-3 ላይ የሰፈረው – እና ላስተዋለው – የወቅቱን የእነ አቶ መለስን – የዓለም አተያይ አበክሮ የሚያስገነዝብ ራዕይ ነው፡፡ ያ የእነ አቶ መለስ ራዕይ – ከትውልደ እስራኤላውያኑና አሜሪካውያኑ ኢምፔሪያሊስት መዳፍ ነፃ ለመውጣት ለሚታገሉት – ለፍልስጥዔማውያን እና ለአረብ እስላማውያን ሀገራት አጋርነታቸውን የገለፁበትን መግለጫ ስመለከት… እንዲህ ነው የሚለው፡-
«3- ስለዚህ ተ.ሓ.ህ.ት. ፅዮናውያንና ኢምፐርያሊስቶችን በተለይም የአሜሪካ ኢምፐርያሊስቶችን በመቃወም ላይ ከሚገኙት ፍልስጤማዊያንና የዐረብ ህዝቦች ጋር ግንኙነቱን ያጠናክራል»
(– የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ድርጅት መግለጫ (የህወሓት ማኒፌስቶ)፣ የመጀመሪያ እተም፣ በየካቲት ወር 1968 ዓ.ም.፣ ገጽ ተሓህት 38፡፡)
እንዴ?! ግን ግን – አቶ መለስ ግን – በዓለም ላይ ያሉ ሌሎች ሕዝቦችን በምሥጢራዊ የተደራጀ ተንኮል እና በክፋት ዕቅዶች ሁሉ ሸብቦ – ለሁልጊዜም ጭቁን ሆነው ተንኮታኩተው እንዲቀሩ ሌት ተቀን ጥፋትን እያሴሩብን ነው የሚለውን – ያን የ«ሲክሬት ሶሳይቲስ ኤንድ ዘ ዛየኒስት ግሎባል ኮንስፓይረሲ» ብለው ባሳተሟቸው በእስራኤላውያኑና በኢምፔሪያሊስቶቹ የተቀናበረ – ሌላውን የዓለም ሕዝብ ለማንበርከክ የተሸረበ – ሌት ተቀን በላያችን ላይ በግልጽና በሥውር የሚቃጣብን ዓለማቀፋዊ ሤራ አለ – ብሎ የሚሰብከውን – የእነ ጃን ቫን ሔልሲንግን – ፀረ-ፅዮናዊነት አስተሳሰብ – ይጋሩት ይሆን እንዴ – እኚህ አቶ መለስ (እና የትግል ጓዶቻቸው)???!!
ካልሆነ ታዲያ – አጋርነታቸውን ለፍልስጥዔማውያንና አረቦች እንደትግል ማኒፌስቶ አድርጎ መደንገግ – እና ፅዮናውያንን ከኢምፔሪያሊስቶች ጋር ማገናኘት – ለምን አስፈለገ? – ምናልባት – በትግላቸው ወቅት እንደልባቸው ሊደጉሟቸው- እና ሊያስጠልሏቸው – የሚችሉት ኢትዮጵያን የከበቡ ጎረቤት ሀገራት ጫናና ግፊት የተፈጠረ – ወቅታዊ ፋይዳ ያለው ራዕይ ይሆንን? ወይስ ምን? – እንጃባቴ!!! በምን አውቄው?!!
ነገሩን ካነሣን ላይቀር ግን – ምናልባት – አቶ መለስ በሥልጣን በቆዩባቸው ተከታታይ ዓመታት – እና ከዚያም ወዲህ በቅርቡ – ቀንደኛ አቃፊ-ደጋፊ አጋራቸውን ዩ ኤስ አሜሪካንን እና እስራኤላውያኑን ሸሪኮቻቸውን ወደ ጎን በማለት – ወጥ በሆነ መልኩ – ለፍልስጥዔማውያን ‹‹ኮዝ›› በመወገን – ለምሳሌ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚነሱት ባሉ ወሣኝ ዐለማቀፋዊ ድምፅ አሰጣጦች ላይ – ‹‹ፕሮ››-ፍልስጥኤም ድምጾችን እና ድጋፎችን ሲሰጡ የኖሩት – ምናልባት ከተመሣሣይ ,- ከዚያ ነባሩ መለሳዊ ፍልስጥዔማዊ ወንድማማችነት ራዕይና – ነባር መለሳዊ ሌጋሲ ላይ ተመሥርቶ ነበር ማለት ነው??? – ወይስ…..?? – የሚል ሃሳብ ደጋግሞ በዓዕምሯችን ሊመላለስብን ይችላል – በሁለተኛው ርዕሰ-ሃሜታችን – አቶ መለስን ስንዘክር – ወይም “ራዕያቸውን” ስናማ!!!
/ይሄኔ እኮ “ወሬኛም ያውራ ሃሜት ይጠንክር፤ እኛስ ሆነናል ፍቅር በፍቅር!” የሚል አይታጣ ይሆናል! …አያድርስ ነው እንጂ ምን ይባላል?!/
ወደሌላው – እና ወደ መጨረሻው – የአቶ መለስ ‹‹የብሔር ራዕይ›› ደግሞ እንሸጋገር፡፡ ምናልባት ሌላው ‹‹ራዕያቸው›› ወይም ‹‹ሌጋሲያቸው›› ተብሎ ሊጠራ የሚችለው – እና ሲጠራም የምንሰማው – ከአቶ መለስ ራዕዮች አንዱ – በራዕያቸው ላይ ተመሥርቶ ተዋቀረ የሚባልለት – የብሔሮች (እና ብሔር-ብሔረሰቦች) እኩልነት ጉዳይ ነው፡፡ (ያው እኩልነት ስንል እኩልነቱ ‹‹ጨቋኝ›› ከተባለው ከአማራው ብሔር ጋር መሆኑን ልብ እንበል፡፡) እና ሌላኛው የአቶ መለስ ራዕይ እንግዲህ – ያን የአማራን ብሔራዊ ጭቆና መሠረቱ አድርጎ የተቀመረው – እና ነፍጥ ያስነሣው – እና አሁን ለምንኖርበት ሥርዓት መፈጠር መሠረቱ – በብሔሮች ላይ የተመሠረተ ፌዴራላዊ ሥርዓት ነው፡፡
ምናልባት ይህንንም ‹‹ራዕይ›› – ከላይ በቀረበው – ማለትም አንድ ሕዝብ – ሌላን ሕዝብ – ሆነ ብሎ ሊያራቁትና በጭቆና ሥር አንኮታኩቶ እንዲቀር ለማድረግ – ሆነ ብሎ – በሌላ ሕዝብ (ወይም ሕዝቦች) ላይ – እንደ ሕዝብ – «ሆነ ተብሎ» የተቀናበረ ምሥጢራዊና ይፋዊ ፋሺስታዊ ሤራዎችና ተግባራትን ይፈጽማል – ወይም ፈጽሟል – ወይም አለ ብለው ያምኑ ይሆን ወይ – እኚህ ዛሬ ስማቸውን የምናማው – የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር – እና የሕወሓት የቀድሞ ሊቀመንበሩ – ጓድ መለስ ዜናዊ?!!!
በእርግጥ – ምላሹን በእርግጠኝነት መደምደም አይቻል ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ያን ራዕይ ሆነ ብለው አምነውበት የተገለጠላቸው ራዕይ ነው – ወይስ – ህዝቦችን ከእርሳቸው (እና ድርጅታቸው) ጋር ለማሰለፍ የተጠቀሙበት ዓይነተኛ የተከፋ-ሰው-የማሰባሰብ እስትራቴጂ?? ብሎ ጥልቅ ጥናት ማድረግ አስፈላጊ ስለሚሆን ነው፡፡ ግን እስቲ ለማንኛውም ይህን የሚከተለውን የህወሓት ማኒፌስቶ በትኩረት እንመርምር፡፡ አተኩረን ስንመረምር – የመደብ ጭቆና አለ ከሚለው ሶሻሊስታዊ ራዕይ በላይ – አንዱ ህዝብ – እንደ ህዝብ – በሌላው ህዝብ ላይ – ሆነ ብሎ – ሸርንና ሤራን እየጎነጎነ ነው የሚል ፋሺስታዊ ራዕይን ያነገበ ሃሳብስ እናገኝ ይሆን?? ወይስ ማኒፌስቶውን ስናየው ምን የሚል ሃሳብ ይመጣብን ይሆን? እንዲህ ይላል የእነ አቶ መለስ ትግል መሠረቱን የጣለበት ዋነኛ ራዕይ ቁጥር አንድ!!!
«3 – ሕብረተሰባዊ ሁኔታዎች፡-
 
«ራስን መጣል (ዲ-ሁማይዜሽን)
«የትግራይ ህዝብ ለረጅም ዘመን ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቱ ተነፍጎ ሲጠላና ሲናቅ እንዲሁም አድልዎ ሲረደምበት ቆይቷል፡፡ ይህም በደል ጨቋኝዋ የአማራ ብሔር ሆነ ብላ እንደመንግሥት መመሪያዋ አድርጋ ስትሰራበት የቆየች ሲሆን ፋሽስታዊ ደርግም በባሰና በመረረ መንገድ ቀጥሎበታል፡፡ በዚህም የተነሳ ሰፊው የትግራይ ሕዝብ ኑሮው እንዲቆረቁዝ ተደርጓል፡፡… ስለሆነም ሕዝቡ ተጠርጣሪና የተጠላ እንዲሆን በመደረጉ በህብረት መኖር የማይቻል ሆኖ ይገኛል፡፡ … ሰፊው የትግራይ ህዝብ ሥራ አጥቶ በ….. በስደት ወ.ዘ.ተ. ብቻ ሳይሆን በረኃብ፣ በድንቁርናና በበሽታ እየተሰቃየ ይኖራል፡፡ እነዚህም ችግሮች ወንጀል እንዲፈጽም ይገፋፉታል፡፡ ለችግሩ መሠረታዊ ምክንያት ኢምፐርያሊዝምና ባላባታዊ ሥርዓት ይሀኑ እንጂ ጨቋኝዋ የአማራ ብሄር የምታደርገው የኢኮኖሚ ብዝበዛና የፖለቲካ ጭቆና ታክሎበት ነው፡፡»
(– የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ድርጅት መግለጫ (የህወሓት ማኒፌስቶ)፣ የመጀመሪያ እተም፣ በየካቲት ወር 1968 ዓ.ም.፣ ገጽ ተሓህት 14-15፣ 15-16)
ምናልባት ምናልባት ታዲያ – ከላይ ያለውን አስተውለን ስናይ – ምናልባት ከ100 ዓመታት በፊት በሩሲያኑ ሶሻሊስቶች በእነ ቭላዲሚር ሌኒን፣ እና በእነ ጆዜፍ ስታሊን – ብሎም በጀርመናውያኑ ብሔርተኛ ሶሻሊስቶች በእነ አዶልፍ ሒትለርና በእነ ፍሬድሪክ ጎብልስ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት አስቀድሞ – «ፅዮናውያን ከምዕራብ አውሮፓና አሜሪካ ኢምፔሪያሊስቶች ጋር በማበር – ሆነ ብለው – እኛን ለማጥፋትና ለማቆርቆዝ –  የሸረቡብን ታላቅ ዓለማቀፋዊ ሤራ አለ!» – የሚል የኮንስፓይረሲ ራዕይን እንዳራመዱት – እና አንግበው ለመረረ ሕዝብ-ብሕዝብ ላይ የትግል ራዕይ አንግበው እንደተነሱት – ሕዝባቸውንም እንዳሳመኑት – እና አሲረውብናል ያሏቸውን ጠላቶቻቸውን ሕዝቦቻቸው እንዲፋለሟቸው ለማድረግ እንደበቁት – እና እንደተሸነፉት – ነገር ግን እስካሁንም ድረስ ያንን የህዝብ-በህዝብ-ላይ ተንኮል ሌጋሲ አምነው ተቀብለው እየኖሩ እንዳሉት በርካታ «ኮንስፓይረሲ ቲዎረቲስትስ» ሁሉ – እኛስ ራሳችን? የእኛስ የራሳችን ነገር – ምን እንበለው ይሆን? – አንድዬ ይወቅ!!
ምናልባት – ምናልባት – እዚህስ እኛ ሠፈር – እንዲያ ያለውን ታላቅ ዘመን-ተሻጋሪ የኮንስፓይረሲ ራዕይ – በዘመኑ ተጽፎ እንደምናገኘው – ስማቸውን በምናነሳቸው አብዮታውያን ዘንድ ስለመኖሩም ሆነ ስላለመኖሩ – እና ሌጋሲውስ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ – በሌሎች ዘንድ – ዛሬ እንደታላቅ ራዕይ ተነግቦ እንደሆነስ – ወይም በዚያው በራሱ ቀድሞ በተቃኘበት አቅጣጫም ይሁን – ወይም በፍፁም ተቃራኒ አቅጣጫ ተቃኝቶ – ያንኑ ዓይነት ትርክት – ያንኑ ዓይነት መነሳሳት – እና ያንኑ ዓይነት ኮንስፓይረሲ ቲዎሪ – ወይም ትወራዎች – ቀጥለው እንደሆነስ? – ወይም አሁንም በይፋም ሆነ በስውር – በአንዱ ወይም በሌላኛው ህዝብ ላይ ተነጣጥረው – እየቀጠሉ ስላለመሆኑስ? ወይም – ዛሬ ላይ – አሁንስ – ያ የእነ አቶ መለስ ‹‹ፒፕል ኧጌይንስት-ፒፕል ኮንስፓይረሲ›› ራዕይ ወይም ሌጋሲው – በአንዱ ወይም በሌላው ዘንድ እንደ ዓይነተኛ መሣሪያ ሆኖ ስላለመቀጠሉስ- ምን ያህል እርግጠኞች መሆን እንችላለን???!
— ትቀልዳለህ?! ለምንድነው ግን ስለ ነገሮች ‹‹እርግጠኝነት!›› ማወቅ እና መማማል የሚቀናን??! ሃበሻነታችን ይሆን?! እስቲ ተወው እርግጠኝነቱን ወዳጄ – እና ፀልይ እንዳይደገም ዛሬ – ያ እኩይ ራዕይ!!!
በበኩሌ – እንዳይኖር ከመጸለይ በቀር – ስለእንዲያ ዓይነት ራዕዮችና ሌጋሲዎች መኖርና ያለመነኖር – በቂ ማረጋገጫ መስጠት የሚችል የማሰብም ሆነ የመዳሰስ አሊያም የመገመት አንዳች አቅም የለኝም፡፡ ነሲብም የሚያዋጣ አይመስለኝም፡፡ ሁላችንም ስለትናንቱ እንጂ – ስለወደፊቱ እርግጠኞች መሆን አንችልም፡፡ ስላለፉት ራሱ በስንት ነገሮች ላይ ተቃራኒ እምነቶች እያሉን – እንዴት ነው ስለወደፊቱ ባንድ ላይ እርግጠኞች ልንሆን የምንችለው??
I guess we can’t! We can only mention and question that vision, but could not conclude whatsoever. Because no one knows the truth, except the fortunate dead!
በመጨረሻ – «ጠባብ ብሔርተኞችን» እና «ትምክህተኞችን» በሚያወግዘው ይኸው የህወሓት በየካቲት ወር 1968 ዓ.ም. ማኒፌስቶ ላይ በሠፈረው የአቶ መለስ ዜናዊ (እና የትግል ጓዶቻቸው) አስገራሚ (ምፀታዊም!) የትግል ራዕይ ማማቴን ወይም ዝክሬን ባሣርግስ? ይኸው፡-
«.ስለሆነም [ተ.ሓ.ህ.ት.] ለዓለም አቀፍ ኢምፐርያሊዝም ያለው ጠንካራ ተቃውሞና ለተራማጅ እንቅስቃሴዎች ያለው ድጋፍና ተባባሪነት ይገልጻል፡፡ በውጭ ጉዳይ አመራሩ የወዝ-አደር ዓለም አቀፍነት ይከተላል፡፡ ጠባብ ብሄርተኝነትና ትምክህተኝነት በጥብቅ ይቃወማል!»
(– የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ድርጅት መግለጫ (የህወሓት ማኒፌስቶ)፣ የመጀመሪያ እተም፣ በየካቲት ወር 1968 ዓ.ም.፣ ገጽ ተሓህት 38)
ወይ ጊዜ!!! ጠባብ ብሔርተኝነትንም የሚያወግዝ ራዕይ ነበራቸው ማለት ነው – ባለራዕዩ መሪ??!!! አይ ጊዜ!!! ጉድ እኮ ነው!!! ለነገሩ ይህ የሶሻሊስቶች ሁሉ ዓለማቀፋዊ መሐላ ነበር፡፡ ሁሉም ሶሻሊስት ዓለማቀፋዊ የወዛደሮች ወንድማማችነትን ሰባኪ ነበር በጊዜው፡፡ ‹‹የዓለም ጭቁኖች ተባበሩ!›› የሚለውን የማርክስን መፈክር በማንገብ ማለት ነው፡፡ የሚገርመው ግን – እንደ ሶሻሊስቶች ያለ – ጠባብ ሀገራዊ ብሔርተኝነትን በዓለም ያሰፈነ የለም!!! አይ መቃጠል!!! በስንቱ በኩል እንቃጠል?!!! — አሉ ገበርምጣዶች!!!
ለማጠቃለል ያህል – እነዚህን ሁሉ አሁን ላይ ሆነን – የምንዘክረው – ወይም የምናማው – ጣቶቻችንን በእነዚያ ታሪኮችና ባለታሪኮች ላይ እየጠቆምን – ከዚያው የታሪክ ዳራ አንዳችም እንኳ ጋት ፈቅ ሳንል – በእነዚያ ትውልዶች ጥልቅ የታሪክ አዙሪት ውስጥ ተዘፍቀን – ከነትውልዶቻችን ወደማንወጣበት የጥላቻና የጥርጣሬ ፅልመት ውስጥ ሰጥመን እንድንቀር – ወይም – በዚያው በድሮው የኋልዮሹ ሌጋሲ ልክፍት እኛም ተይዘን – ዳግም በእነዚያ ጠንቀኛ ራዕዮች እንድንዳክር – አስበን – ያን ፈልገን አይደለም – ዛሬ እነዚያን የምንዘክረው፡፡
ይልቁንስ – የቀድሞዎቹ ባለታሪኮች – (እና ባለራዕዮች) – በሌሎች ላይ ያራመዱትን ያን የታሪክ ሥህተት – ዛሬ ላይ ያለን እኛ – ወይም ወደፊት የሚኖሩት የኛ ትውልዶች – አንደኛው በሌላኛው ላይ ያንኑ እንዳንደግመው ዘንድ ነው – ከልብ በመነጨ መቃተት – ያለፈውን ታሪካችንን – አብረን – በጥልቅ እንመርምር – ብለን – በተቻለ መጠን በርበሬውን ደቁሰን (ቃጠሎውን አለዝበን፣ ጣዕም ሰጥተን) – ያለንን ለማዋጣት – እና ሃሳብ ለመካፈል የተነሣሣነው፡፡
ለማንኛውም ግን ሃሳቤ ረዥም ነው፡፡ እንዲህ ረዝሞ ራሱ ገና አልተቋጨም፡፡ በሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ – ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ‹‹የበላኸው ይመለስ!›› የሚለኝ ከሌለ ማለት ነው!!! ወቸ ጉድ!! አያድርስ ነዋ!! እና በሕግ አምላክ!!
ያለፉትን ነፍስ ይማር፡፡ ያለነውን ቸር ያሰንብተን፡፡ የሚመጡትን ብሩህ፣ ቀና፣ ዘመን-ተሻጋሪ ራዕይን በልባቸው ያኑር፡፡ አምላክ ኢትዮጵውያንን ሁሉ ከትውልድ እስከ ትውልድ አብዝቶ ይባርክ፡፡ የብዙሃን እናት ኢትዮጵያ – ለዘለዓለም ትኑር፡፡ አነሣሥቶ ላስጀመረን – አስጀምሮ ላስጨረሰን አንድዬ አምላክ – ክብር ምስጋና ይድረሰው፡፡ አበቃሁ፡፡
Filed in: Amharic