>
5:30 pm - Wednesday November 2, 2259

ዛሬም ስለአስተሳሰብ አንድነት!! (ኢ/ር ይልቃል ጌትነት)

ዛሬም ስለአስተሳሰብ አንድነት!!
ኢ/ር ይልቃል ጌትነት
የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ እንደሆነና የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል የአስተሳሰብ አንድነት ለመፍጠር በሚያስችል ሁኔታ እየተካሄደ እንደሆነ ኢቲቪ ነግሮናል።አህአዴግ ማርጀቱና ሊድን በማይችል ሁኔታ መታመሙን ለመገንዘብ የሩቁን ትተን የቅርቡን የአራት ወር ጉዞ ማየት በቂ ነው።
በኢህአዴግ ሊቀመንበርና በህወሃት መካከል የነበረው የቃላት ጦርነት፣በደኢህዴን ውስጥ የነበረው ሽኩቻ በህወሃትና በብአዴን መካከል የሚታየው ፍጥጫ፣ የለውጥ ሀይል ተብሎ የሚታወቀውና ወደ ህዝብ የቀረበው የጠቅላይ ምንስትሩ ቡድን የቀደሙ ስህተቶችን በተለይም የህወሃትን የበላይነት ከመታገልና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ ከሞመከር ባለፈ ግልፅ የሆነ የለውጥ አጀንዳና የድርጊት መርሀ ግብር ቀርፆ ኢህአዴግን አሳምኖ ባለመውጣቱ ምክንያት ድርጅቱ በውስጥ ሽኩቻ እየታመሰ ነው።
በኔ እምነት ሁሉም የግንባሩ አባል ድርጅቶች በተፈጥሮ በህሪያቸው አንዱ ያለአንዱ ሌኖር ስለማይችልና የለውጥ ሃይል የተባለውም  ቡድን በእውቀት ላይ የተመሰረት ግልፅ ፍኖተ ካርታ አቅርቦ አሳምኖ መውጣት የሚችልበት ቁመና ላይ ባለመሆኑ ኢህአዴግ ህመሙ እንደጠናበት ያለህክምና ስብሰባው ይጠናቀቃል።
በኢህአዴግ መበስበስ የሚመጣውን ሃገራዊ ቀውስ ለመመከትና የኢትዮጵያን የለውጥ ምጥ ወደ ዴሞክራሲ ለማሸጋገር ከኢህአዴግ ውጭ ያለው የለውጥ ሃይል የራሱን አጀንዳ ቀርፆ ሀላፊነት በተሞላበት መልኩ ትግሉን መምራት ያለበት ደረጃ ላይ የደረስን ይመስለኛል።የኢትዮጵያን መፃኢ እድል በኢህአዴግ የውስጥ ሽኩቻ አሸንፎ ሊወጣ የሚችል ሀይልን ተስፋ አድርጎ ለእድል መስጠት አደገኛ ቁማር ስለሆነ በጥንቃቄ መታየት ያለበት ጉዳይ ይመስለኛል።
Filed in: Amharic