>
4:57 pm - Sunday August 7, 2022

ዐብንና የአሜሪካ መንግሥት  በነገው ዕለት በሸራተን ሊወያዩ ቀጠሮ ይዘዋል! (ዘመድኩን በቀለ)

ዐብንና የአሜሪካ መንግሥት 
በነገው ዕለት በሸራተን ሊወያዩ ቀጠሮ ይዘዋል!
 ዘመድኩን በቀለ
~ ማነህ እንትና ይኸው መረጫጨት ተጀመረ፣ የገመትነውም ተፈጸመ በልልኝማ ! ንሥሮቹ ታድሰው ከተፍ አሉ ማለት ይኼም አይደል ?  ኢንዴዢያ ነው። አከተመ።
~ ጩኸቴን የሰማኸኝ አምላኬ ሆይ ክበርልኝ። ዐማራን በዐማራነቱ ኃያላኑ ሀገራት ከእርሱ ጋር ተቀምጠው ሊነጋገሩ፣ ሊመካከሩና ሊወያዩ ተራ ገብተው ያሳየኸኝ አምላክ አሁንም ክበር ተመስገንልኝ። አሜን።
 እነሆ ይኼ የመደራጀት ውጤት ነው። ነገር ግን ይኼ ኢምንቱ ጉዳይ ነው። ገና የራስደጀን ተራራን የሚያህል ፈታኝ ሥራ ከፊታችሁ ይጠብቃችኋልና ከአሜሪካ ጋር መወያየት በመጀመራችሁ እንዳትዘናጉ። ተናግሬያለሁ።
ከአሁኑ ጨቅላውን #ዐብን አያያዙን በማየት እናናግርህ ባዩ እየበዛ መጥቷል። ለዚሁም ምስክሩ ዐብን በማናገሩ በኩል አሜሪካ ቀዳሚውን ስፍራ መያዟ ነው። ይህን ዜና ያሰራጨው ሀገር መጋዶ ፈጅቶ ገና በቅርቡ ከእንቅልፉ ነቅቶ በመንጠራራት ላይ የሚገኘው በድኑ ብአዴን የሚመራው የዐማራ መገናኛ ብዙኃን ድርጅት የተባለው የወሬ ማሰራጫ ድርጅት ነው። ወሬ ማደራጫው ድርጅት የዐማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (ዐብን) ሊቀመንበር የሆኑትን ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ ነገ ነሐሴ 17/ 2010ዓ.ም የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት #ከዐብን ከፍተኛ አመራሮች ጋር በአዲስ አበባ ከተማ በሸራተን ሆቴል ውይይት ያደርጋሉ፡፡
በውይይቱ የአፍሪካ ዓለማቀፍ ጤና፣ ሰባዊ መብት እና ዓለማቀፍ ተቋም ሊቀመንበር ክሪስ ስሚዝ እና በአሜሪካ የዐብን ብሔራዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ ቴዎድሮስ ትርፌም ይገኛሉ ተብሏል፡፡ አቶ ቴዎድሮስ ትርፌ ማለት HR128 ን አጡዞ በኢትዮጵያ አሁን የሚታየውን ለውጥ ያመጣና ዐማራ በመሆኑ ብቻ ገድሉ የተደበቀበት ወንድ እናቱ የወለደችው የዐማራ ጀግና ነው። አቶ ቴዎድሮስ እነ ዶክተር ዐቢይ አህመድን የስልጣን ርካብ ያስረገጠና ያፈናጠጠ፣ ህውሓት የሚመጣባትን አደጋ አይታ ወደ ጓዳ እንድትደበቅ የደረገም ምርጥ ኢትዮጵያዊ አሜሪካዊ የዐማራ ልጅ ነው። እናም ቴዲ ዛሬ ከአሜሪካ ተነስቷል። ነገ አዱ ገነት ይገባል። አከተመ።
የዐብን የወቅቱ የንቅናቄው ሊቀመንበር የሆኑት ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ እንደተናገሩት ከሆነ በውይይቱ ወቅታዊ የዐማራ ፖለቲካና የኢትዮጵያ ሁኔታ፣ ዐማራ ባለፉት ዓመታት ስለአሳለፋቸው የፖለቲካ ሂደቶች፣ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲና የፖለቲካ ሥርዓቱ እንዴት መሻሻል እንዳለበት እንዲሁም የአሜሪካ መንግሥት የፖለቲካ ሂደቱን እንዴት ይደግፋል የሚሉ ነጥቦች በውይይቱ ይነሳሉ ተብሎ ይጠበቃል በማለት መናገራቸው ተዘግቧል፡፡
ዐብን የተሰኘውን ዐማራዊ ድርጅት የፈጠረው ጥጋብ አይደለም። አናሳነትም አይደለም። ዘረኝነትም አይደለም። ዐማራ ሲጀመር ዘረኛ ሆኖ አያውቅም። ዘረኛም አይደለም። ዐማራን በዐማራነቱ እንዲደራጅ የግድ ያለው የህውሓት ለከት ያጣ ዐማራውን መግፋት ነው። እናም ዐብን ጭቆና፣ መረገጥ፣ መገለል፣ መሰደድ፣ መራብ፣ መጠማት፣ መሰደብ፣ መገፋት፣ መናቅ፣ መታሰር፣ መደብደብ፣ መኮላሸት፣ መሰለብ፣ መታረድ፣ ገደል መጣል፣ በእሳት መቃጠል፣ የዘር ማጥፋት የወለደው የዐማራ እንባ አባሽ ድርጅት ነው።
#ምክር_ቢጤ_ለዐማራዎቹ | ~ እርግጥ ነው ኢትዮጵያ !  ኢትዮጵያ!  ኢትዮጵያ ብቻ በማለታችሁ ባለፉት 44 ዓመታት ነገዳችሁ በማንም ፀረ ኢትዮጵያ ቡድን ከምድረ ገጽ እንዲጠፋ ተደርጓል። መጀመሪያ በፋሽስት ኢጣልያ፣ ከዚያም በሸአቢያና በህውሓት አሳራችሁን በልታችኋል። አሁንም ቢሆን በዐማራነት መደራጀቱ ምቾት እንደማይሰጣችሁ ይታወቃል። ሆኖም ግን ሌላ ምርጫ የላችሁም። ነገዳችሁን ለማዳን ያለ ዐማራ ተሳትፎ በሸአቢያ፣ በህውሓትና በኦነግ አማካኝነት የተዘጋጀው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በሚፈቅደው መሠረት መደራጀት ብቸኛው መፍትሄ ነው። እናም ትክክል ናችሁ።
ዐማራ በዐማራነቱ ቢደራጅ ለኢትዮጵያ ስጋቷ እንዳልሆነም እሙን ነው። እንደ ህውሓት ወይም እንደ ኦነግ የውጭ ኢንቨስትመን የሌለበት ድርጅትም ነገድም ነው ዐማራ። ዐማራን እንደ ፈጣን ሎቶሪ ብትፍቀው ውስጡ ኢትዮጵያዊ መሆኑን እነ ህውሓትም ምስክሮች ናቸው። እናም በመደራጀታችሁ ቅንጣት ታህል ቅሽሽ እንዳይላችሁ። እደግመዋለሁ ቅንጣት ታህል አልኳችሁ።
ነገር ግን እንዳትዘናጉ። ዙሪያችሁን የተከበባችሁት ዐማራ የሚባል ነገድ ከምድረገጽ መጥፋት አለበት በሚሉ አካላት መሆኑን ማወቅ አለባችሁ። እንደ ዐማራ ማሰብ ከጀመራችሁ ገና ዓመት እንኳ ያልሞላችሁ ጨቅላዎች መሆናችሁንንም እንዳትረሱ። ከ50 ዓመቱ ኦነግ፣ ከ44 ዓመቱ ህውሓት ጋርም ስትነጻጸሩ እናንተ ገና አራስ ጨቅላ ህጻን መሆናችሁን አትዘንጉ። በሴራ ፖለቲካ በተካኑ አውሬዎች መሃል መሆናችሁንም ልብ በሉ።
የዐማራን መበደል ጣሊያን ታውቀዋለች፣ ጀርመን ምስክር ናት፣ እንጊሊዝ አይታለች፣ አሜሪካ፣ ካናዳና ፈረንሳይም ምስክሮች ናቸው። የተባበሩት መንግሥታት ድብን አድርጎ ያውቃል፣ እነ ቢቢሲ፣ ሲኤንኤን አልጀዚራም በደንብ ያውቃሉ። እናም አያውቁ መስሏችሁ እነሱን ለማስረዳት ስትሉ ልባችሁ አይውለቅ። ዕድሉን ስላገኛችሁ ተጠቀሙበት። በደንብ ተጠቀሙበት። ቢያውቁትም ዶክመንት ያህል አስረግጣችሁ ንገሯቸው።  እንደ ህውሓት እግር አትላሱ። ጫማም ላይ አትውደቁ። እንደ አባታችሁ እንደሚኒልክ፣ እንደእናታችሁ እንደጣይቱ እንደ እርግብ የዋህ እንደ እባብ ብልህ ሁኑ። እንደ ንሥር በግርማ ሞገስ ቅረቡና እኩል ተቀምጣችሁ ሞግቷቸው። እንጂ አትቅለስለሱ፣ አትተብቱ፣ አትጎርሩም። የዐማራው መደራጀት የህልውና ጉዳይ መሆኑን። የሞት ሽረት ጉዳይ መሆኑንም አስረግጣችሁ ንገሯቸው። ይኸው ነው።
ስሙኝማ ልንገራችሁ የዐማራው አደረጃጀት፣ መሰብሰብ ልክ እንደ ማዕበል ነው። እንደ ሱናሚ ያለ። በቃ የሞላ ፣ የገነፈለ ብሶት የወለደው፣ የፈጠረውም ማዕበል ነው። አሁን እንደ ድሮው ስለ ዐማራ ሞት ብቻ መዘገብ ቀንሷል። ይኽን የፈጠረው የዐማራው መደራጀት ብቻ ነው። እናም አሁንም መደራጀቱ ተጠናክሮ ይቀጥል። በገጠር በከተማ በክልሎችም በአዲስ አበባና ዐማራ ባለበት ቦታ ሁሉ ዐማራው ልክ እንደ ኦሮሞው፣ እንደትግሬው፣ እንደሱማሌው እንደአፋሩና እንደ ሌሎቹም ይሰባሰብ፣ ይደራጅ፣ ይነጋገር።
የተደራጀን ህዝብ እንኳን ህውሓት ሰይጣንም ይፈራዋል። የተደራጀ ህዝብ ይከበራል። የተደራጀ ህዝብ ፈላጊው ይበዛል። ጓደኛ ሁነኝ ባዩም ይበዛል። መጠንቀቅ ግን አስፈላጊ ነው። የፖለቲካ ጨዋታ ብዙ የዋሕነትን አይፈቅድ። በፖለቲካ ጨዋታ እንደመንፈሳዊ ሰው ጿሚ ጸላይ መስሎ መቅለስለስም ደግም አይደል። አጉል መንጠራራትም ጠላት ያበዛል። መልመጥመጥም ባሪያ፣ አሽከር፣ አቅመ ቢስ ያስመስላል። የሚሻለው ኢትዮጵያዊነቱን ሳይለቁ በዐማራነት መንፈስ ደርባባ ሆኖ መቅረቡ ነው።
ዐማራው በኢትዮጵያዊነቱ መደራጀት ለሚፈልግ አካልም እንቅፋት መፍጠር የለበትም። በነገዱ መደራጀት ለሚፈልገውም ክብር መስጠት አለበት። የአንድነት ኃይሉም በዐማራው መደራጀት ማለቃቀስ የለበትም። መነጫነጭም የለበትም። ግፍያ፣ ስም ማጥፋት፣ ነቆራውም አይጠቅምም። በዚያን ጊዜ ልቅሶ ይሆናል የማይጠቅም ልቅሶ ነው። በዚያን ጊዜ እየዬ ይሆናል የማይጠቅም እየዬ ነው። በዚያን ጊዜ ብስጭት ይሆናል የማይጠቅም ብስጭት ነው እንዲል መጽሐፍ ዐማራውን ላታስቆሙት ነገር  ከፊቱ አትገተሩበት። በቃ ዐማራው ነቅቷል። የሚበጀውንም ይዟል። ከነቃ ደግሞ ነቃ ነው። አይገደድም። ኻላስ !
ይኸውልህ ማነህ እንትና ዐማራው ለዘመናት ከመታወቂያዬ ላይ ዐማራ የሚለውን አንስታችሁ ኢትዮጵያዊ በሉኝ ብሎ በማለቱ መከራውን አይቷል፣ ፍዳውንም በልቷል። አሁን ግን ቀበሌ ሄዶ መታወቂያዬ ላይ በወፍራሙ #ዐማራ ብለህ ጻፍልኝ ሲል ጊዜ አይ ቆይ እስቲ መታወቂያውን ኢትዮጵያዊ እናድርግልህ ተብሏል። እናም ይኼ ለውጥ የመጣው ዐማራው ዐማራ ነኝ ማለት በመጀመሩ፣ ደረቱን ነፍቶ ድምጹንም ሞቅ አድርጎ ዐማራ ነኝ በመለቱ ምክንያት ነው።
እናም የዐማራው መደራጀት ኢትዮጵያን ዳግም ይሠራታል። ነገርኩህ ዳግም ይሠራታል። ቢመርህም ዋጠው። ኢንዴዢያ ነው።
ሁሉም ዐማራ እስላም ክርስቲያኑ የዐብን መታወቂያ መያዝ አለበት። ዐብን የዐማራ ትንሣኤ ምልክት መሆኑን ማሳየት የዐማራው ሁሉ ኃላፊነት ነው።
ዐማራው የራሱ የሆነ የመገናኛ ብዙኃን የግድ ያስፈልገዋል። ራዲዮ ለገጠሩ ዐማራ፣ ቴሌቭዢንና ጋዜጣ ለከተሜውና በመላው ዓለም ለሚገው ዐማራ ያስፈልጉታል። ዐማራው የደቀቀውን ክልሉን መልሶ ማልማት ይገባዋል። የዐማራ ባንኮች፣ የብድር መስጫ ተቋማት፣ ኢንሹራንሶች፣ የልዩ ክህሎት መስጫ የትምህርት ተቋማት፣ ወዘተ መቋቋም ያስፈልጉታል። ገዳማቱ፣ ጥንታውያን ታሪካዊ ሥፍራዎቹን መልሶ መገንባት የግድ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው።
የዐማራው መደራጀት በጊዜ ካልተከወነ ልክ ሀገር አልባ እንደሆኑት ያዚዲዎች ክፉ ዕጣ ይገጥመዋል። ዐማራው እንደ ፍልስጤም ሽባ፣ አቅመቢስ ሆኖ የሰው እጅ ከማየቱ በፊት መሰባሰብ፣ መደራጀቱ ይበጀዋል ባይ ነኝ። ይኼ ወንድማዊ ምክሬ ነው።
ሻሎም !  ሰላም !
Filed in: Amharic