>
4:44 pm - Wednesday January 26, 2022

መሀሉ ዳር ሲሆን ዳሩ መሀል ይሆናል የወቅቱ የሶማሌ ክልል መልእክት (መሀመድ ኤ እድሪስ)

መሀሉ ዳር ሲሆን ዳሩ መሀል ይሆናል
የወቅቱ የሶማሌ ክልል መልእክት
መሀመድ ኤ እድሪስ
የሶማሌ ክልላዊ መንግስት አዲስ ርዕሰ መስተዳደር መርጧል። አዲሱ ፕሬዝዳንት ሙስጠፋ ኦመር በዋነኛነት በሁለት ምክንያቶች ሰፊ ተቀባይነት አግኝተዋል። የመጀመሪያው እርሳቸው በተኳቸው ክልሉን የቡድን ጥቅም ማስከበሪያ የፉክክር አውድማ አድርጎ ካቆየውና ህዝቡን የማያፈናፍን ክልሉንም ከሎሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች በነጠለው በአብዲ ኢሌ እግር መተካታቸው ነው። ሁለተኛው የአቶ ሙስጠፋ ኦመር የግል ብቃት ጋር የተያያዘው ነው። በሰብአዊ መብት ትግል ተሞክሯቸው በብዙሀኑ ዘንድ ያተረፉት መልካም ስም እና የአለምአቀፉን ማህበረሰብ ባህሪ መረዳት የሚያስችላቸው ልምዳቸው ተጠቃሽ ነው። የክልሉ ስያሜና ባንዲራ ላይ ለውጥ እንዲያደርግ የገፋቸው ስለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ያላቸው ሚዛናዊ ምልከታ አዲስ ሀይል እንደሚሆናቸውም ይጠበቃል።
ዛሬ የሶማሌ ክልል የሚሰኘው በንጉሱ ዘመን ሳይቀር በሀገር ፍቅር ክበብ ኢትዮጵያዊነትን እንዲማር ሲፌዝበት ስለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ታግለው የንጉሱን ስርአት የገረሰሱ የተማሪዎች ንቅናቄ አመራር እና አባላትን ያፈራ ነገር ግን ውለታው ተዘንግቶ ከፖለቲካው ዲስኮርስ በፖለቲከኞች የተረሳ ክልል ነው። ጭቆናን እምቢ የሚሉ የነፃነት ትግሎችም አዲስ አይደሉም። እንደወቅቱ ፖለቲካ የሚሰጣቸው ስምና የሚከተሉት ስልት ቢለያይም የተካሄዱ የነፃነት ትግሎችም የክልሉን ህዝብ ለጭቆና አጎንብሶ እንደማያውቅ መስካሪዎች ናቸው።
ይህም ሆኖ ግን አስቀድሞ ከክልሉ ህዝብ ይልቅ የክልሉን ሀብት እና መሬት የሚያስቀድሙ መንግስታት ምክንያት የሶማሌ ክልል ህዝብ ለኢትዮጵያ የድንበር አጥርነት ሚና ብቻ እንዳለውና እንዲኖረው ተደርጓል። በኢህአዴግ አገዛዝ ዘመን ደግሞ ክልሉን ለተመሳሳይ አላማ በተለየ ስልት ዳር ሆኖ እንዲቀጥል አድርጎታል። የመሀል ሀገር ፖለቲካን ደህንነት ማስጠበቂያ፣ በቅርብ ግዜ ደግሞ የፖለቲካ ሀይሎች ለሚያደርጉት ፉክክክር የእጃዙር የፍልሚያ አውድማ ( Proxy War) ማካሄጃ ሆኗል።
“መሀሉ ሲነካ ዳሩ መሀል ይሆናል” እንዲል ያገራችን ሰው ክልሉ በስተመጨረሻ የመሀል ሀገሩ ፖለቲካ ፉክክር የመጨረሻ አሸናፊ የሚለይበት አንጋሽ ( King Maker) ወደመሆን መጥቷል። የመሀል ሀገሩ ፖለቲካ ፖለቲካዊ አቅሙ የሚመሰከረው አዲስ አበባ ላይ የመሆን እድሉ እየቀነሰ ነው። እርግጥ ነው ይሄንን በሙሉ አፍ ለመመስከር ተጨማሪ ግዜዎች መጠበቅ ያሻናል።
የአቶ ሙስጠፋ ኦመር ጅምር እና የክልሉ ነፃነት ናፋቂዎች ያሳዩት ትልቅ አቀባበል በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ አዲስ ዲስኮርስ ከሶማሌ ክልል እና ፖለቲከኞች የመነሳቱን አይቀሬነት ያሳያል። እራሱን የመሀል ሀገር ፖለቲከኛ ብሎ የሚሰይመው ሀይልም የፖለቲካ ማእከልነት በታሪክ ውርስ የሚመጣ ሳይሆን ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ እና ለአዲሱ ትውልድ በሚመጥን ፖለቲካዊ ጥበብ ብቻ እንደሚገኝ የሚገነዘብበት ወቅት እንደመጣ አስረጅ ነው። የአዲስ አበባ የፖለቲካ ማእከልነት አዳዲስ ተዋንያን እስካልጨመረ ድረስም ብቻውን የፖለቲካ ሚዛን የማስጠበቅ አቅሙ ላይመለስ እየሄደ ነው። በተለምዶ ዳር (Periphery) ተብለው የሚታወቁ አካባቢዎችን ከስጋት፣ ከድንበር እና ከሀብት አንፃር ብቻ የሚተነትኑ ፖለቲከኞች ቅኝታቸውን ካላስተካከሉ ጡረታቸውን በግዜ ማመቻቸት ይጠበቅባቸዋል። ለአብዲ ኢሌ አስተዳደር ጥብቅና ሲቆሙ የቆዩ አካላት ክልሉ ከአቻ ክልሎች አንፃር ያለበት ፖለቲካዊና ተቋማዊ ሁዋላ ቀርነት ሳያሳስባቸው በሁዋላ ቀርነቱ ለመጠቀም የመረጡት ስልት ነበርና በፍትሀዊ ተጠቃሚነት ቀመር አብሮ ወደመስራት ጉዞ እንዲገቡ አዲስ ግብዣ እንደቀረበላቸው ቢረዱ መልካም ነው። በኢህአዴግ ውስጥ ያለው የውስጥ ድርጅት ፉክክር መጨረሻው ምንም ይሁን ምን የሶማሌ ክልል የፖለቲካ ድምፁ እየጎላ የሚመጣ ሁላችንም ቆመን ልንቀበለው የሚገባ አይቀሬ የፖለቲካችን ወሳኝ ባለድርሻ መሆኑ አይቀርም።
በስተመጨረሻም የዶክተር አብይ መንግስት እስካሁን ካካሄዳቸው መሰረታዊ ለውጦች የሶማሌ ክልል ላይ የታየው ጅምር ትርጉሙም ተፅእኖውም ትልቅ ነው። ይሄንን ጅምር በመሀል ፒለቲካው ላይ የክልሉን ሚና ታሳቢ በማድረግ የሀገራችንን ፓለቲካ አዲስ ገፅታ እንደሚያሳየንም ተስፋ እናደርጋለን።
Filed in: Amharic