>

"...የምታስተዳድረው "ዳቦውን በእንባ አርሶ የሚበላ" ምስኪን ህዝብ መሆኑን አትዘንጋ...

“…የምታስተዳድረው “ዳቦውን በእንባ አርሶ የሚበላ” ምስኪን ህዝብ መሆኑን አትዘንጋ…
ቅዱስ ፓትርያርኩ ለዶ/ር አብይ የለገሱት ምክር
ዘላለም
* …ታድያ ልጄ 80 ልጆች እንዳሉህ ቆጥረህ በትእግስት አስተዳድራቸው…ሁሉም ሆደ ባሻ ፣ሁሉም ቶሎ አኩራፊ፣ ሁሉም ቁስለኛ  ስለሆነ ቆዳህን አወፍረህ በትእግስት አስተዳድራቸው..
 
አየህ ልጄ “ላናግርህ ስፈልግ መጣህ”…በቅጡ ካወራሁ አንድ 4 አመት ይሆነኛል። ዛሬ ግን ካንተ ጋር ማውራት እሻለሁ…አሉት ልስልስ ባለ የአዛውንት ድምጽ…ብዙ ሰው አትናገርም ወይ ይለኛል? ምን ብየ ልናገር? ስለምንስ ልናገር?…እኔ ንግግሬ ከሰማያዊው አምላክ ብቻ ነው…ምድርንማ ይሄው ከተወለድኩባት ደብረታቦር አውራጃ ድርበብ ከምትባል ትንሽ የገጠር መንደር አስከ አማሪካ ኖሬ አየሁት…ይሄንን አድካሚ ከንቱ አለም አይቼ መልካም ነገር ባጣበት በልጅነቴ የተማርኩትን ሰዓታት፣ድጓ፣ጾመ ድጓ፣ዚቅ፣ምልጣን ሌላውንም በልቤ እያዜምኩ በአርምሞ መኖርን መረጥኩ…
ዛሬ ግን አንተን ላወራህ ወሰንኩ…ይሄውልህ እኔ ወደ ስደት ከመውጣቴ ትንሽ ቀደም ብሎ የአለም ታላላቅ ሰዎች የተሳተፉበት አንድ ስብሰባ ነበር እዛ ላይ ታድያ ነፍሱን ይማረው እና ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የኤርትራው መሪም ተገኝተው ነበር…ስብሰባው አልቆ እረፍት ላይ እንዲህ ወደ ምሳ እየሄድን…ካወራሁ ስለሰነበትሁ ጉሮሮዬ እምቢ አለኝ ልጄ…አይዞዎት አባታችን ውሀ ላምጣ…እይ ይሻለኛል ግድ የለም…እናልህ ከደጃፉ ስንደርስ የቀድሞው የሮማ ካቶሊክ አባት (ጆን ፓል 2ኛ) መለስን እና ኢሳያስን ጠሩ እና እንዲህ አሏቸው…”እናንተ ወጣት መሪዎች እጅግ እድለኞች ናችሁ…ከዚህ በኋላም  እናንተ የታገላችሁለትን ህዝብ ትክሱታላችሁ…የቀድሙት መሪዎች የሰሩትንም ስህተት እናንተ አትደግሙትም” ብለዋቸው ቅጭም ያለች ፈገግታ ትተውላቸው ሄዱ…እንግዲህ ከዛ በኋላ የሆነውን ላንተ አልነግርህም…ግን ልጄ አደራህን የኛን ሽማግሌ ምክር ወዳንተ ላስተላልፈው እና እባክህ “የቀደሙት መሪዎች የሰሩትን ስህተት አንተ እንዳትደግመው” ዓለምሰ ኃላፊ ውእቱ ከመጽላሎት”አለም እንደ ጥላ ሀላፊ ጠፊ ናት” ብለው በእርጅና የሞጨሞጩ አይኖቻቸው እንባ አቀረሩ…. ልጅ ሲወለድ በእግሩ የመጣ እንደሆን ለእናቱም ለልጁም ጤንነት አደጋ ነው በጭንቅላቱ የመጣ እንደሁ ግን ለሁለቱም ሰላም ነው…መልካም መሪም እንደዛው የሀገር መድሀኒት ነው…ታድያ ልጄ 80 ልጆች እንዳሉህ ቆጥረህ በትእግስት አስተዳድራቸው…ሁሉም ሆደ ባሻ ፣ሁሉም ቶሎ አኩራፊ፣ሁሉም ቁስለኛ  ስለሆነ ቆዳህን አወፍረህ በትእግስት አስተዳድራቸው…አንዱን ለማስደሰት አንዱን እንዳትኮንን አደራ…ዘመን፣ ግዜ እና ፓለቲካ አቃቃራቸው እንጂ ኢትዮጵያውያን የአንድ እናት ልጆች ናቸው…አደራህን ልጄ አደራህን ይህችን አገር ስታስተዳድር እኔ ሸክላ ነኝ ድንገት ተሰባሪ…መልካም ሰርቼ ስሜ ከመቃብር በላይ ይዋል ብለህ ስራ…የንጹሀን እንባ እና ደም በከንቱ አይፍሰስብህ አዙሮ ይጥላል እና….የምታስተዳድረው “ዳቦውን በእንባ አርሶ የሚበላ” ምስኪን ህዝብ መሆኑን አትዘንጋ…በል በርታ ልኡል እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ይሁን…እኔም ወደ አርምሞዬ ልመለስ አሉ ቅዝዝ ባሉ አይኖቻቸው ወደጎን ትኩር ብለው እያዩ…ሆደ ቡቡው ጠቅላይ ሚኒስትር በተራው እንባ ተናነቀው…መሬት መሬቱን እያየ በሀሳብ ጭልጥ ብሎ ሄደ…በዚህ መሀል ፕሮቶኮሉ ጠጋ ብሎ እንግዶቹ ኤርፖርት ደርሰዋል ሲለው ከእንቅልፉ እንደነቃ ሰው ብንን አለ…።
Filed in: Amharic