>

የአውራ ፓርቲው መሪነትና የ ''አጋሮች'' እጣ ፈንታ (ዩሱፍ ያሲን - ኦስሎ)

የአውራ ፓርቲው መሪነትና አጋሮችእጣ ፈንታ

ዩሱፍ ያሲን – ኦስሎ

በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እረፍት ማግስት የህልፈታቸው እንደምታዎችን አስመልክቶ ኢሳት ለአንጋፋው ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌና ለእኔ ቃለ መጠይቅ አድርጎ ነበር። የዛሬ 6 ዓመት መሆኑ ነው። በእሳቸው ሞት አባት አልባ (Orphan የእሳቸው ቃል ነው) እጓለ መውታ ይሆናሉ ያሏቸው ቅርበት የነበራቸው የሁለት ሰው ስም ጠቅሷል። ወይዘሮ አዜብ መስፍንንና አቶ በረከት ስምዖን። ትንበያው የያዘላቸው ይመስላል። ሁለቱን የፖለቲካ ስዎች የመለስ ዜናዊ ሞግዚትነት ማጣት የፖለቲካ ኮከባቸው እያዘቀዘቀ መጥቶ ኮስምነው፣ ኮስምነው ለጥቃት አመቻችቶ አጋለጣቸው። የፖለቲካ እጓለ ሙታን ቢባሉ አያስገርምም ለማለት ነው።

በታዳጊ ክልሎች የስልጣን ተጋሪ ባይሆኑም ቅሉ የኢሕኣዲግ አጋር ተብለው 5 ክሎሎች ማለትም በሶማሌ፣ በአፋር፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ፣ በጋምበላና በሓራሪ በስልጣን የተፈናጠጡት ገዢ ፓርቲዎችና የብሔረሰቦችና የሕዝቦች የስልጣን ኤሊቶችአጋርነታቸውለፈጣሪያቸው ለአውራው ፖርቲ ኢሕዴአግ ነበር። ልክ እንደ መጽሓፍ ቅዱሱ (ፍጥረት ወይም መቅድመ ወንጌል?) እግዚኣብሔር የፈጠራቸው መላዕክትን ፈጥሮ ለተወሰነ አጭር ጊዜ የተሰወረባቸው ፍጡራን ተጠፍጣፊ አስመስሏቸዋል። ግራ እየተጋቡ ናቸው። ምክንያቱ የኢሕአዲግ አራቱን ብሔራዊ ድርጅቶች ከግንባር ወደ ውሁድ ፖርቲ በሚለወጥበት ወቅት በታዳጊ ክልሎች ያሉትአጋርዲሞክራሲያዊ ድርጅቶችም ወደ አዲሱ አንድወጥ ፓርቲ እንደሚቀላቀሉ ነበር እቅዱም፣ ፍላጎቱም ሕልሙም። ዓረቦች እንደሚሉት ንፋሱ ለጀልባዎቹ የጉዞ አቅጣጫ በተጻራሪ አቅጣጫ መንፈስ ተያያዘው ሆነና ኩነቶቹ ፊታቸውን አዞሩባቸው። ነገር ዓለሙ ተገለባበጠባቸው። እንኳን የእነሱ እጣ ፈንታ የፈጣሪያቸው ጠፍጣፊያቸው እጣ ፋንታ አነጋጋሪ ሆነና አረፈው። እሱም ድርጅቶቹ በጥቅምት ያደርጉታል በሚባለው ጉባያቸው እልባት ያገኝ ይሆናል። ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ የመዋሃዱ እቅድ እንዳለ ነው ቢሉም ውህደቱ በቅርብ ይጠናቀቃል ተብሎ አይታሰብም። አጋሮችን የመጠርነፉ እቅድ እየራቀ ይሄዳል ማለት ነው። የኢሕዴኣግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መግለጫም ሆነ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋዜጣዊ መግለጫ ሁሉም ነገር በታቀደው አኳኋን በመከናወን ላይ እንደሆነ ቢያረጋግጡም ቅሉ። እንደውም ቃል በቃል ለመጥቀስም መግለጫው የተጀመረውን የለውጥ ሂደት እንደሚቀጥል ካረጋገጠ በኋላ ኢሕኣዲግ በተለመደው ድርጅታዊ ባህል፣ ዲሞክራሲያዊነትን በተላበሰና በሰከነ አግባብ ሂደቶችን በጥልቀት ገምግሟል ብሎ ያሰርጋል። እነዚህ ሁሉ ያልተለመዱ አባባሎች አይደሉም። እንዲያውም ለሰሚው ያሰለቹ ናቸው ቢባል ምንም ማጋነን የለበትም። ታዛቢዎቹ የሕወሓት መሪዎች ከስብሰባው መለስ መቕሌ  ከተመለሱ በኋላ የሚሉትን ነው የናፈቃቸው። ለምን ቢባል  በሁለት ቀን ስብሰባ ሁሉ ቅሬታ መልስ ማግኘቱን ስለሚጠራጠሩ። ከሁሉ በላይ ግን ድርጅቶቹ በውስጠ ደንባቸው ላይ ለማከል የሚዘጋጁት ማሻሻያ ሓሳቦች ላንድወጥ ፓርቲነት የሚያዘጋጃቸው ሳይሆን ለየራስ ድርጅታዊ ሕልውናቸውን የሚያጠናክሩ ናቸው። የሚዋሃዱ ከሆነ ስሞቻቸው መቀየሩ ምን አመጣው ሌላ ጥያቄ። በተግባር የሚገለጽ የዓላማ አንድነት የኢሕዴኣግ የዘውታሪ ቃል ዓላማ ነው። እሱም ቢሆን በቀላሉም በቅርቡ የሚተገበር መፈክር አይሆንም።

ስለ መፈክሮች ካወራን ዘንድ ኢሕዴኣግም ሆነ ሕወሕት በርካታ የመፈክር ጋጋታ ነበረው። ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ማጠፊያ ሲያጥራቸው የሚያደናግሩበትና ስሚ የሚያደነባቡርበት የትዮሪ አረፋ ያስነሱ ነበር። ገና ደደቢት በረሓ እሱና ሰዬ አብርሃ ከተጻራሪ ግንባሮች ጋር ለመከራከር በኮሞኒስት ቲዮሪ ልቀው እንዲገኙ ድርጅቱ ካሰማራቸው ጊዜ ጀመሮ የተካኑት አካሄድ ነው። በኋላ ላይ አረጋዊ በርሔናና ግደይ ዘረጽዮን ከሜዳ ያባረሩት በዚሁ የቃላት ጋጋታ ነበር። ቦርዡዋ፣ ቦናበርቲዝም፣ አብዮታዊ ዲሞክራሲ፣ልማታዊ መንግስት በእዚህ ትጥቅ የሚደመሩ ወንጭፎች ነበሩ። ዛሬ ቀለሃው በየቦታው ተበትኖ ቀርቶዋል፣ እንጂ። 

አጋርድርጅቶችም ከሲቪል ኮሌጅ በተመረቁ ጥቂት መሪዎቹ ጧት ማታ ኪራይ ሰብሳቢ፣ ጥልቅ ተሃድሶ፣ ብለው የሚደሰኩሩት እምበለ ምክንያት አይደለም። እነ አብዲ ኤሊ የመፈክር ጋጋታ አላስፈለጋቸውም። ልዩ ኃይል በማሰማራት በሕወሓት የተሰጣቸውን ግዳጅ በሚገባ ተወጡት። ከጦር ሜዳ አብረው የመጡት እንደ አፋር ክልል መንጁሶች (የልጅ ወታደሮች) የሲቪል ኮሌጅ ካድሬነት ኮርስ አላስፈለጋቸውም። በክልላቸው ላይ በላይ መመሪያ ይዥጎዶጎድላቸው። ትናንትም፣ ዛሬም። ምክንያቱ ከሕወሕት ጋር የነበራቸው እትብት አልተቆረጠምና። አንዳንድ ካድሬዎች ታማኝነታቸው ወደ አዲሱ አመራርና ባለተራው ብሔራዊ ድርጅት ለማሸጋገር እየሞከሩ ነው።ገሚሶቹ እየተንገላቱ ናቸው። እንደከላይ የተጠቀሰው ፈጣሪያቸው የተሰወረባቸው አመልዕክት ፈጣሪያቸውን ለመክዳት እያኮበኮቡ ነው። መቼም ከእነሱ መሓልምንቁም በባህላዊነ እስከ ንረክቦ ለፈጣሪነ (አምላካችን እስከምንገናኝ በእምነታችን ጸንተን እንኑር)ብሎ የቅዱስ ገብርኤል ሚና የሚጫወት እምነት ጠንካራ አይጠፋም። ሕወሕት አሁንም አፈር ልሶ ይነሳል ብሎ ትንሴውን የሚጠባበቅ። በእዚህ ግንባር የአፋር ክልል መሪዎች አቋም ጠንካራነታቸውን ሳያሳዩ አይቀሩም ተብሎ ይተነበያል። 

አጋሮችየሚመሯቸው ክልሎች በኋላ ቀርነታቸው (ታዳጊነታቸው) የዳር ሃገር ከመሆናቸው ውጭ ከሚያመሳስላቸው ይልቅ የሚያለያያቸው ባሕሪያት ያመዝናሉ። በሕዝብ ብዛት፣ የማሕበረሰብ ስብስቦች ጥንቅር፣ የፖለቲካ ሃይሎች አሰላለፍ ወዘተ አይመሳሰሉም። ያለ ሞግዚት ለጋራ ዓላማ የሚያስተባብራቸው ሃይል ሳያስፈጋቸው መቼም አይቀርም። ድሮ መገናኛቸው የኢሕዴኣግ ጉባኤ ነበር ማለት ያስደፍራል። የብሔረሰቦች ቀን ሲያከብሩም አብረው መጨፈሩ እንደተጠበቀ ሆኖ ማለቴ ነው። የጋምቤላ ዲሞክራሲያዊ ድርጅትና የሶማሌ ፓርቲ፣ የሓራሪና ቤንሻንጎል ጉሙዝ ገዢ ፓርቲ ከእዚ ውጭ ጥረቶቻቸውን የሚያስተባብሩበት መድረክ አልታይ ብሎኝ ነው። 

በኢሕዴኣግ ግንባር ውስጥ ስለተፈጠረ መመሰቃቀል በአጋሮች ዘንድ ያስከተለው ግራ አጋቢና አስቸጋሪ ሁኔታ አወሳሁ እንጂ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ማህበረሰቡና ያማገሩት ተቋማት ሁሉ ጤናቸው የተሟላ አይደለም። ሥርዓቱ እየተናወጠ ነው። ምን ይገርማል ታዲያ በአብዮታዊ ሽግ ግር ላይ መሆናችን ከታመነ ሊባል ይችል ይሆናል። አብዮት ደግሞ የሕብረተሰቡ ሹም ሽር ነው ይላል 68 ካድሬው። / ዓብይ አህመድ ኢትዮጵያን ከእርስ በእርሱ ብጥብጥ አፋፍ፣ እፍፍ አደረጋት ተባለ እንጂ ባለፉት 27 ዓመታት ከሚያገናኙ መግለጫዎቻችን ይልቅ በሚያለያዩን ጉዳዮች ላይ ሆን ተብሎ ስለተተኮረ ሕብረተሰቡ የገባበትን ቀዛቃዛ እርስ በእርስ ጦርነት አላበረደውም። እንደ ጓደኞቹ ያንዣበበው ስጋት በፍቅር አስወጋጅ ዝማሪን አብሬ ብዘምርለትም በወደፊቱ አብሮነታችን ቀመር ላይ እንኳን የሁሉ ስምምነት  አልተበጀም። ገና በርካታ ውይይት፣ መግባባትና ስምምነት ሊደረስባቸው የሚገባ ዓበይት ጉዳዮች አሉ። በቅርቡና የመጀመሪያው ጋዜጣዊ መግለጫ በርካታ ጉዳዮች ተብራርቷል። የለውጡ አስተማማኝነትን የሚያረጋግጡ መተማመኛዎች ተሰጠዋል። እስከ 2012 (2020) ምርጭ ድረስ ግን በእርግጠኝነት መነጋገር አዳጋች ነው። ለምን ወደዚያ እንሄዳለን። የጥቅምቱ የኢሕዴአግ ጉባኤ የሻዕቢያ ካድሬዎች እንደሚያዘወተሩት  በዓወት ተዛዝሙ  በድል ተጠናቀቀ) ካልተባለ። ካልታዘልኩ አላምንም እንዳለችው የገጠር ሙሽራ ጥርጣሬ እያንገላታን ነው!

Filed in: Amharic