>
11:22 pm - Tuesday August 16, 2022

የተንታው ፊታውራሪ አመዴ ለማ ማን ናቸው? (አዲስ አድማስ ጋዜጣ)

የተንታው ፊታውራሪ አመዴ ለማ ማን ናቸው?
 
አዲስ አድማስ ጋዜጣ
 
* ለሀዘን ጥቁር የምንለብሰው ከጣሊያኖች ኮርጀን ነው… ይላሉ
* በህገመንግስቱ ውስጥ የሰፈረውን የመገንጠል መብት ይቃወማሉ…
* በ36 ዓመታቸው 300 መፃሕፍት አንብበዋል…
ፊታውራሪ አመዴ ለማ፤ በ2001 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ከመለየታቸው ጥቂት ዓመታት ቀደም ብሎ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የ”ዓውደ ሰብ” ፕሮግራም ላይ እንግዳ ሆነው በቀረቡበት ወቅት፣ ጋዜጠኛው ከባህል ተከታይነታቸው ጋር በተያያዘ በተለይ ነጠላ የማዘወትራቸውን ጉዳይ አንስቶላቸው ነበረ፡፡ እሳቸውም ሲመልሱ፤ “ጀለቢያ ለአረብ አገራት የባህል ልብስ እንደሆነው ሁሉ ነጠላም ለኢትዮጵያዊያን ባህላዊ እንጂ ሃይማኖት ገላጭ አይደለም” ማለታቸው ይታወሳል፡፡
የፊታውራሪ አመዴ ለማ ታሪኮች፣ እውነታዎች፣ ትዝታዎች፣ የቤተሰብና የሥራ ታሪካቸውን የያዘው “የሕይወቴ ታሪኬ” የተሰኘ መጽሐፍ ለአንባቢያን የቀረበው በቅርቡ ነው፡፡ “የሕይወት ታሪኬ” የሚለውን መጽሐፍ፤ በማቀነባበርና በማረም የረዷቸው አቶ በቀለ አበባውን ያመሰገኑበት ጥራዝ በ320 ገፆች የተቀነበበ ሲሆን በ60 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ተዘጋጅተው እየቀረቡ እንዳሉት መፃሕፍት ሁሉ ይህም መጽሐፍ ማመሳከሪያ ሰነድ ሆኖ የሚጠቀስለት ብዙ መረጃ ይዟል፡፡ ለሀዘን ጥቁር የምንለብሰው ከጣሊያኖች አይተን ነው ።
በአማራ ብሔረሰብ የቀድሞ ባህል መሠረት በሀዘን ወቅት አንገት ላይ ነጭ ክር ይታሰራል፡፡ ጥቁር የበርኖስ ካባ ተገልብጦ ቀይ ገበር ባለው በኩል ይለበሳል፡፡ ነጣ ያሉ ልብሶች ቀይ ቀለም በሚያወጣ የተክል ዓይነት ተቀቅለው “ከል” እንዲሆኑ ይደረጋል የሚለው መጽሐፉ፤ ኢትዮጵያዊያን በሀዘን ወቅት ጥቁር መልበስ የጀመሩት ከጣሊያን ወረራ በኋላ ጣሊያኖች በሀዘን ወቅት የሚያደርጉትን አይተው በመኮረጅ ነው ይላል – መጽሐፉ፡፡
የሴተኛ አዳሪነት ጅማሬ በደሴ (ሰቆጣ) 
አመንዝራነት ከዓለምና ከሰው ልጅ መፈጠር ጀምሮ እንደነበር ታሪክ ይመሰክራል የሚሉት ፊታውራሪ አመዴ ለማ፤ በእኛም አገር “መለኮን” በሚል መጠሪያ ብዙም በአደባባይ ሳይታወቅ ይተገበር እንደነበር አመልክተው፣ ከፋሽስቱ ጣሊያን ወረራ በኋላ ቆንጆና ልጅ እግር ሴቶች ተመርጠው ፎቶግራፍ ተነስተው በካምፕ እንዲቀመጡ ከተደረገ በኋላ፣ ወታደሮች ከፎቶግራፉ እየመረጡ ወስደው ይስተናገዱባቸው ጀመር፡፡ በዕድሜ ጠና ያሉና ካምፕ መግባት ያልቻሉ ሴቶች ቤት እየተከራዩ በምሽት ቀይ መብራት እያበሩ በመቆም፣ ሴተኛ አዳሪነት በአደባባይ እንዲታወቅ አደረጉ፡፡
የሁለቱ ዘመን ግጥም መመሳሰል
የጣሊያን ወታደሮችን ስሜት እንዲያረኩ ተመልምለው በየካምፑ እንዲቀመጡ የተደረጉ ሴቶችን ተግባር ተከትለው በሴተኛ አዳሪነት የተሰማሩ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር መበራከቱ ያስገረማቸው የዘመኑ ሰዎች:-
በአሪቲ በአሽኩቲ የታሸውን ገላ
ሰጠችው ለፈረንጅ ለፈረንካ ብላ
በሚል መገረማቸውን በግጥም አቅርበው እንደነበር የሚያስታውሰው መጽሐፍ፤ “አሽኩቲ” ግሩም ሽታ ያለው የተክል ዓይነት እንደሆነም ያብራራል፡፡
ይህ ግጥም ከተቋጠረ ከ60 ዓመት በኋላ “አልመሸም” በሚል ርዕስ በገጣሚ ዓለምፀሐይ ደሳለኝ ተዘጋጅቶ በ1993 ዓ.ም በታተመው የግጥም መጽሐፍ ውስጥ ከቀረቡት 70 ግጥሞች አንዱ በጣሊያን ዘመን ከተገጠመው ሕዝባዊ ግጥም ጋር በሀሳብ የሚገናኝ ሲሆን ቁጭታዊ ስሜትን የሚያስተላልፍ ነው፡፡
መኖር ሆኖ የሌት ትልሟ
መብላት ሆኖ የቀን ሕልሟ
ነገደችው፤ ለወጠችው ተደራድራ
ያንን ገላ፣ ያን ብርቅ …”ቃ
ባንዲት ቅጠል “በወረቃ”…
በ36 ዓመት 300 መፃሕፍት አንባቢው 
የገበሬ ልጅ ነኝ የሚሉት ፊታውራሪ አመዴ ለማ፤ የገበሬ ልጆች የሚያልፏቸውን ብዙ ውጣ ውረዶች አልፈዋል፡፡ በጣሊያን ዘመን እስከ 4ኛ ክፍል የመማር ዕድል አግኝተዋል፡፡ በኋላ ላይ የሕግ ትምህርታቸውን ተከታትለው በዲፕሎም ተመርቀዋል፡፡
ከዚያም የራሳቸውን ሥራ ፈጥረው በመምራት ላይ እያሉ በ1948 ዓ.ም የፓርላማ አባል እንዲሆኑ በሕዝቡ ተጠቁመው በመወዳደር ያሸነፉ ሲሆን ስለዚሁ ጉዳይ ሲናገሩ:-
“እኔ በዚያን ጊዜ ከ300 የማያንሱ ልዩ ልዩ መጽሐፍትን አንብቢያለሁ፡፡ የውጭውን አስተዳደርና የእኛን አስተዳደር ኋላ ቀርነት ተገንዝቤያለሁ፡፡ ይህንን አስመልክቶ አንዳንድ ጥያቄዎች ቢነሱ ለመመለስ ተዘጋጀሁ፡፡ የነጋዴውን፣ የገበሬውን፣ የወታደሩን፣ ችግሮች አስመልክቶ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች መልሴን አዘጋጀሁ” ዝግጅታቸው ጠቅሞአቸዋል፡፡ በተካሄደው ጠንካራ ውድድር ለፓርላማ አባልነት በማሸነፍ የደሴን ሕዝብ ከወከሉት ሁለት እጩዎች አንዱ ሆነው አዲስ አበባ መጡ፡፡
ተቃውሞን ከፓርላማ በመውጣት መግለጽ 
በነጋሪት ጋዜጣ ቁጥር 62 ለቃዲ ፍርድ የተሰጠ ስልጣን ነበር፡፡ በ1951 ዓ.ም የፍትሐ ብሔር ሕግ ሲወጣ ከዚያ በፊት በልማድ ወይም በጽሑፍ የወጡ ሕጐች በሙሉ መሻራቸው ይገለፃል፡፡ ፓርላማው ከነበሩት 210 አባላት 35ቱ ሙስሊሞች ነበሩ፡፡ ለቃዲ ፍርድ ቤት የተሰጠው መብት እንዳይሻር ፊታውራሪ አመዴ ለማ ለምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ያመለክታሉ፡፡
ፕሬዚዳንቱ ድምጽ ይሰጥበት ይላሉ፡፡ በድምጽ እንደሚሸነፉ የተረዱት ፊታውራሪ አመዴ 35ቱም ሙስሊሞች ፓርላማውን ለቀው እንዲወጡ ያደርጋሉ፡ ከዚያ በኋላ ጉዳዩ እስከ ንጉሠ ነገሥቱ ይደርስና ለቃዲዎች የተሰጠው ስልጣን እንዳይነካ ተደረገ፡፡
ከጣሊያን በተገኘ ብድር የተሰራው የለገዳዲ ግድብ 
የቆቃ ግድብ ፋሽስቱ ጣሊያን በኢትዮጵያ ላይ ላደረሰው ጉዳት በሰጠው የካሳ ገንዘብ መገንባቱ ይታወቃል፡፡ ጣሊያኖች ግን በኋላ ላይም ኢትዮጵያን መፈታተናቸው እንደቀጠሉ የፊታውራሪ አመዴ ለማ መጽሐፍ አንድ ታሪክ ያሳያል፡፡ በንጉሡ ዘመን ጣሊያን 35 ሚሊዮን ብር ለኢትዮጵያ ብድር ለመስጠት ፈቃደኛ ስለነበረች በጉዳዩ ላይ ፓርላማው ሲወያይበት “በአከፋፈሉ ክርክር ቢነሳ ዳኝነቱ ሮም ላይ በጣሊያን ሕግ መሠረት ይታያል” የሚለውን አንቀጽ ያዩት ፊታውራሪ አመዴ ለማ፤ ጉዳዩን ይቃወማሉ፡ምክንያታቸውና መከራከሪያቸው ታሪካዊ እውነታን ያጣቀሰ ነበር፡፡ “ጣሊያን በአፄ ምኒልክ ጊዜ ሁለት ሚሊዮን ሊሬ አበድራ ብድሩን በማስታከክ የአገሩን ሉአላዊነት ለመዳፈር ስታደባ አፄ ምኒልክ ይነቁና ሕዝባቸውን አስተባብረው ብር እንዲያዋጣ ካደረጉ በኋላ ብድሩን በመክፈል የመጣባቸውን አደጋ መከላከል” መቻላቸውን ያብራራሉ፡፡
ከሦስት ዓመት በኋላ ያከራከረው አንቀጽ ተቀይሮ ጣሊያን 35 ሚሊዮን ብር ለኢትዮጵያ ብድር የሰጠች ሲሆን አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ብሩን ተቀብሎ የለገዳዲ ግድብ ተሰርቶበታል፡፡ ፊታውራሪ አመዴ ለማ፤ ከንጉሡ እስከ ኢሕአዴግ ባሉት መንግስታት ውስጥ የተመለከቷቸውን ጥሩ ነገሮች ማድነቅ እንደሚችሉት ሁሉ ያላመኑበትንም ትህትና በታከለበት ግልጽነትና ድፍረት ይናገራሉ፡፡ ለዚህ እውነታ በንጉሡ ዘመን ለተለያዩ አካላት የፃፏቸው ደብዳቤዎች ማሳያ ናቸው፡፡ አገሪቱንና ህዝቡን ከአምባገነኑ የደርግ መንግስት የገላገላቸው ኢሕአዴግ፤ የመሰብሰብ፣ የመናገርና የመፃፍ መብት መፍቀዱን የሚያደንቁት ፊታውራሪ አመዴ ለማ፤ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ስለመገንጠል መብት የተቀመጠውን አንቀጽ ግን ይተቻሉ፡፡
አገሪቷ ወደብ አልባ እንድትሆን መደረጉንም ይቃወማሉ፡፡ “የአክሱም ሐውልት ለደቡብ ሕዝብ ምኑ ነው” ያሉት የኢሕአዴግ መሪዎች፤ በኋላ ላይ የአክሱም ሐውልት ወደ አገሩ እንዲመጣ ጥረት እንዳደረጉት ሁሉ በሂደት ስህተታቸውን ያርማሉ ብለውም እንደሚያምኑም በመጽሐፋቸው ውስጥ ገልፀዋል፡፡
Filed in: Amharic