>
5:14 pm - Monday April 20, 6691

ዳግማዌ ምኒሊክ, አኖሌ እና ለማ መገርሳ (ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ)

ዳግማዌ ምኒሊክ, አኖሌ እና ለማ መገርሳ

ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ

(ኮተቤ  ሜትሮፖሊታን  ዩኒቨርስቲ)

ህወኃት በፈጠራ ወሬ፡ መረጃን በማሳከር፡ በሃሰት ውንጀላ፡ እና ዜጎችን በመከፋፈል የተዋጣለት የማፊያ ቡድን ነው፡፡ህወኃት ካዛባዉ የታሪክ ድርሳን መካከል የአጼ ምኒሊክን እና የአኖሌን ኃዉልት በዚህ አጭር ጽሁፍ እንቃኛለን፡፡በአርሲ ዘመቻ የምኒሊክ ወታደሮቸ የኦሮሞ ሴት ጡት ቆርጠዋል ለሚለዉ ዉንጀላ ህወኃት ያሰራዉ ኃዉልት አኖሌ ተብሎ ይጠራል፡፡

ዘመናዊነት በኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረው በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመን ሲሆን በባቡር፣ ስልክ ፣ ፖስታ፣ ኤሌክትሪክ፣ አውቶሞቢል፣ የውሃ ቧንቧ፣ ህክምና፣ ሆሰፒታል/ ፋርማሲ፣ ባንክ፣ ገንዘብ ማተሚያ ቤት፣ ጋዜጣ፣ ሆቴልና ፖሊስ አገልግሎት መኪና፣ ወፍጮ፣ ቀይ መስቀል፣ የሚኒስተሮች ሹመት፣ የሙዚቃ ሸክላ እና የመሳሰሉትን ስራዎች የተጀመሩት ከ1982-1901 ባሉት ጊዜያት ውስጥ ነው፡፡ ሃያ አመት ባልሞላው ጊዜ ውስጥ እነዚህ ሁሉ የዘመናዊነት ማሳያዎች የተከናወኑት በእኝህ ታላቅ አንጋፋ መሪ ነበር፡፡

አፄ ሚኒሊክ በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ ያላቸው ለኢትዮጵያ አንድነት አብዝተው የሰሩ፣ ህዝባቸውን አስተባብረው በውጭ ወራሪ ላይ ድል የተጎናፀፉ ታላቁ የአፍሪካ የድል ኮከብ ሆነው አያለ የህወኃት ልሂቃን የአፄ ምኒለክን ታሪክ ጥላሸት ለምን ቀቡት?  የህወኃት ካድሬዎች በአጼ ምኒሊክ ላይ ተገቢ ያልሆነ የታሪክ ሸክም ለመጫን ለምን ፈለጉ? ስሜትን በሚኮረኩሩ የፖለቲካ ቃላት ታሪክን ማጠልሸት ለምን አስፈለገ? የአፄ ምኒልክን እኩሪ ገድል የሚዘክረውን ታሪክ በፖለቲካ የፕሮፓጋንዳ ነውጥ መወዝወዙ ለምን ተፈለገ? የኦሮሞ ሴትን ጡት የምኒሊክ ወታደሮቸ እንደቆረጡት ተደርጎ ኃዉልት መቆሙ ለህወሃት የሚከተሉትን ፋይዳ እንዲያስገኝለት ታስቦ የተሰራ ነው፡፡

  1. ዜጎቸን ከሚለያየው የፖለቲካ ፖሊሲ እና ፕሮፖጋዳ በተጨማሪ ህዝባችንን ለመለያየት ታሪካዊ ዳራ ለማንተራስ  የቂም ኃዉልት ማቆም ስለፈለገ፤
  2. በዘመናዊ የኢትዮጵያ  ታሪክ አፄ ምኒልክ ሀገርን አንድ በማድረግ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ መሪ ስለነበሩ እሳቸው የፈጠሩትን አንድነት ህወኃት ከሚከተለው  ፖለቲካ ጋር ስለሚፃረር የአጼ ሚኒልክን የድል ታሪክ በተደራጀ መልኩ ማጨለም ለህወሃት ህልውና አስፈላጊ ነው ተብሎ ስለታሰበ፤
  3. አናሳ ቁጥር ያለው ኃይል ስልጣን ላይ ለመቆየት የመለያየትን ታሪክ መስበኩ ለህወኃት አማራጭ የሌለው መንገድ ስለነበረ ነው፡፡

የኢትዮጵያን ንጉሠ ነገሥቶች ግዛታቸውን ለማስጠበቅና ለማስፋፋት አብዝተው ኃይል ይጠቀሙ እንደነበር በርካታ የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ፡፡ ለምሳሌ፣  አፄ ቴዎድሮስና አፄ ዮሐንስ የዚሁ ታሪክ ተጋሪዎች ናቸው፡፡ የአፄ ቴዎድሮስ ቅጣት እጅና እግርን የሚየስቆርጥ እንደሆነ የተመለከተች አልቃሽ የሚከተሉትን ስንኞች ደርድራለች፡፡

 አጼ ቴዎድሮስ ምነው ተዋረዱ፣

 የሸዋን ሰው ሁሉ እጅ ነስተው ሔዱ ፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ አጼ ዮሐንስ በርካታ የጭካኔ ድርጊቶችን ይወስዱ እንደነበረ የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ አጼዎች የሚወስዷቸው የጭካኔ ቅጣቶች በዘመናዊ አስተሳሰብ ተቀባይነት ባይኖረውም የሚወስዷቸው ቅጣቶች ግን ለሀገር እና ለሐይማኖት ካላቸው ቀናኢነት እንደሆነ ለመረዳት ይቻላል፡፡ አብዛኛዎቹ አጼዎች (ኃ/ስላሴ ፣ ቴዎድሮስ ፣ ዮሀንስ እና ሌሎችም) በዜጎቻቸው ላይ የጫኑት የጭካኔ በትር ቢኖርም አፄ ሚኒልክ ግን በአስተዋይነታቸው እና በሩህሩህነታቸው የተለዩ እንደነበሩ የተለያዩ ፅሁፎች ያስረዳሉ፡፡ይህ ሲባል ግን  አፄ ምኒሊክ ሰው ናቸውና ምንም ስህተት የማይፈጽሙ ብጹዕ ናቸው ለማለት የተሰነዘረ መላምት አይደለም፡፡ ሆኖም ከሌሎች አጼዎች ጋር ሲነጻጸሩ የላቀ አመራርና ሰብአዊነት እንደነበራቸው ለማሳየት ነው፡፡

አንጋፋው ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ አጤ ምኒልክ በሀገር ውስጥ የተጻጻፏቸውን ደብዳቤዎች በመመርመር ማጠቃለያ  ሀሳቡን ሲያስቀምጥ ሁሉም ደብዳቤዎች የንጉሠ ነገሥቱን ትሁት ግለ-ባህርያት ያንጸባርቃሉ ብሏል፡፡ ሌላው ቀርቶ ይላል ጳውሎስ ኞኞ ምኒልክ የማይስማሙበት ነገር እንኳን ቢገጥማቸው አሉታዊ መልሳቸው ተቀባዩን ቅር እንዳያሰኝባቸው ተጨንቀውና ተጠብበው ነበር ደብዳቤውን የሚጽፉት(ጳውሎስ ኞኞ፡2003)፡፡ አጤ ምኒልክ አምዬ በሚል ሙገሳ ህዝቡ የሚጠራቸው ያለ ምክንያት አልነበረም፡፡  ፀኃፊ ትእዛዝ ገብረስላሴም የጳውሎስ ኛኞን ሀሳብ ይጋሩታል፤ ጸኃፊ ትእዛዙ አጤ ምኒልክ አስተዋይና ሩህሩህ እንደነበሩ ጽፈዋል(ጸኃፊ ትእዛዙ፡2008)፡፡

አንጋፋው ተመራማሪ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ (2008) ስለ አፄ ምኒልክ እንደ ጻፈዉ ሚንሊክ የቆሰለውን ምርኮኛ ገድሎ በመጨረስ ፋንታ ቁስላቸውን ራሳቸው አክመው አጠገባቸው አስቀምጠው አብረዋቸው እንዲመገቡ በማድረግ ፍቅር ያሳዩአቸው ነበር፡፡ አገራቸውን ለመውረር የመጡ ምርኮኞች ጣሊያኖችን እንኳን በርህራሄና በደግነት ነበር የያዟቸው ፡፡ ሩህሩህ እንደነበሩ የዳግማዊ ምኒልክ ታሪክ ምሁሩ በተረኩበት ጽሁፎች ይታያሉ፡፡

የአማራው ገዢው መደብ የኦሮሞን ሴት ጡት እንደቆረጠ የሚያሳየው የአኖሌ ሀውልት ሁለቱን ታላላቅ ህዝቦች ለማራራቅ የተቀነባበረው የህወኃት የፖለቲካ ሊሂቃን ሴራ እንደሆነ በርካታ የጥናት ጽሁፎችም ያሳያሉ (በቃሉ፣ 2010፤ ቪስታስ፣ 1991) ፡፡ በተጨማሪም ታዋቂው የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስተር በጠሩት ስብሰባ ላይ እንደገለጹት ህዝባችን የሚያቃቅሩ መሰረተ-ቢስ ክንውኖች እንዳሉ በጥያቄ መልክ አቅርበው ነበር፡፡ እንዲሁም ተዋቂው ጸኃፊ ተውኔት እና የታሪክ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ስለ አጼ ምኒሊክ እና ስለ አኖሌው ሀውልት እንደጻፉት አፄ ምኒሊክ ምክንያታዊ አስተሳሰብ የነበራቸው እና እራሳቸውን እንደጥሩ ክርስቲያን የሚያዩ ሰው ነበሩ፡፡ በጦርነት ላይ የሴት ልጅ ጡት መቁረጥ ፍጹም ከባህሪያቸው ውጭ ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ ውንጀላ መሰረተ-ቢስ እና ከተንኮለኞች የመነጨ ነው፡፡ እኚህን ሰው ጡት ቆርጠዋል/ አስቆርጠዋል ብሎ መፈረጁ አግባብነት የሌለው ትንሽ የፖለቲካ ጠቀሜታ ለማግኘት ታስቦ የተሰነዘረ ፕሮፖጋንዳ  ነው በማለት ገልጸዋል(ፍቅሬ ቶሎሳ፡2008)፡፡

አጤ ምኒልክ እንኳን ለወገናቸው ለኦሮሞው ይቅርና ለወራሪው የፋሽሽት ምርኮኛ እንኳን ሩህሩህ እንደነበሩ ታሪክ ይዘክራቸዋል፡፡ ሁኖም ግን ህወኋት የሀሰት መሰረተ ቢስ ተረቱ ቁመና እንዲኖረዉ በሀሰት የተቀነባበሩ ልብ-ወለዶችን በመፍጠር በሁለቱ ትልልቅ ህዝቦች መካከል የስልጣን ህልውናውን ለማስጠበቅ የሚለያዩ ጉዳዮችን ማራገብ ነበረበት፡፡ ይህን ለማሳካት ሀሰትን የሚያቀነባብሩ እንደ ተስፋየ ገ/አብ የመሳሰሉ በገንዘብ እና በስልጣን የሚገዙ ፀሀፊዎችን በመፍጠር የቡርቃ ዝምታን በማፃፍ ታሪክን ማጠልሸት ፈለገ፡፡ በተመሳሳይ  ሁኔታ በአርሲ ኦሮሞዎች እና በሚኒሊክ መካከል የነበረውን የጦርነት ሁኔታ ሩሲያዊው ፀሐፊ እልቂት ብሎ የጠራውን አሰፋ ጃለታ ምኒሊክ አምስት ሚሊዮን ኦሮሞዎችን ጨፍጭፏል በማለቱ ለህወኃቶች ጥሩ መደላደል ፈጠረላቸው (በዕውቀቱ ስዩም፣ 2008)፡፡ ያልተፃፈውን ጭብጥ በመሰለኝ መተርጎም ትልቅ የታሪክ መዛባትን ያስከትላል፡፡ ምንም እንኳን አሰፋ ጃለታ እልቂት የሚለውን ቃል አምስት ሚሊዮን ብሎ ቢተረጉመውም፣ በጊዜው የነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ ከጠቀሰው ቁጥር ብዙም የማይሻገር እንደነበረ እና ጉዳዩ የሀሰት እንደሆነ የዘርፉ ተመራማሪዎች ያስረዳሉ (ፍቅሬ ቶሎሳ, 2008)፡፡

በአጠቃላይ ምኒሊክ በኦሮሞ ህዝብ ላይ ፈፅመውታል የተባለው የሀሰት ትረካ በህወሀት ቅጥረኞች የተቀነባበረ እና ታሪክን በቅጡ ማገናዘብ ባልቻሉ አክራሪ ብሔርተኞች የተሰነዘረ ሃሳብ እንጂ እነዚህ ወንጀሎች በተግባር ስለመፈፀማቸው የሚያስረዱ የታሪክ ሰነዶች አልተገኙም፡፡ ስለ አርሲ ጦርነት መረጃ የሰበሰቡት የኦሮሞ ወዳጅና የሚኒልክ ነቃፊ  የነበሩ የአውሮፓ ፀሀፊዎች ስለ ጉዳዩ ያሉት ነገር የለም (በዕውቀቱ ስዩም፣ 2008) ሌሎችም የታሪክ ተመራማሪዎች እና የነገስታት ፀሐፊዎችም በጉዳዩ ላይ ምንም ነገር አልመዘገቡም ፡፡

እውነታው ይህ ሆኖ እያለ ከእውቀት ይልቅ በብልጠትና በመሰሪነት ህዝቡን ሊመሩ የሞከሩት የጎሳ ስርዓቱ ባለሟሎች ህዝቡን በአሉባልታ ወሬ በመከፋፈል ህይወታቸውን ስርዓቱ፤ ክብራቸውን ሆዳቸው፤ አክራሪ ብሔረተኝነትን የህልውናቸው ምሰሶ ያደረጉትን ካድሬዎች ከየብሄሩ በመመልመል ብዙ ጥፋት ተሰርቷል፡፡ በኦሮሞና በአማራ ህዝቦች መካከል አንድነትን ለማዳከም ብዙ የሀሰት ታሪኮች ተፈልፍለዋል፡፡ የጥፋት መስመርን ለመክፈት በርካታ የቅጥፈት ስራዎች ተሰርተዋል፡፡በጋብቻ፣በታሪክና በባህል አብረው የተገመዱትን የሁለቱን ህዝቦች ወንድማማችነት ለመለየት ሲባል ከሚቻለው በላይ ብዙ ተሰርቷል፡፡  

ይህን የሀሰት ታሪክ ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ የለብንም፡፡ አክሱምን፤ ላሊበላን፤ ፋሲልን የመሳሰሉ የኪነ-ጥበብ ስራዎችን ከበፊቱ ትውልድ ወርሰናል፡፡ እንዲሁም የአድዋን ድል የመሰለ አኩሪ የጥቁር ህዝብ ታሪክ ከአባቶቻችን ተረክበናል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ታሪክ፣ ስነ-ፅሁፍ፣ ባህልን ከአባቶቻችን ታድለናል፡፡ እኛ የሚያኮራ ታሪክና ቅርስ ተረክበን እንዴት የጥላቻን ትርክት ለቀጣይ ትውልድ እናስተላልፋለን?  እንዴት ቀጣይ ትውልድ የሚያፍርብንን የሀሰት ታሪክ እናሻግራለን? እኛ እንደነሱ መሆን ባንችል እንዴት መሰረተ-ቢስ በሆነ ትርክት ቂምን እናሻግራለን? የጎሳ ብሔር አቀንቃኞች ለሀያ ሰባት ዓመታት ሲያራግቡት የነበረውን ዓለማቸውን ለምን ለመጭው ትውልድ እናቆየዋለን? የህወኃት የመሰሪነት ባህሪ መረዳት ለምን ተሳነን፤ እግዚአብሔር የሚጠላዉን የቂምን ሐዉልት ለምን የታሪካችን አካል ይሆናል፡፡

በመጸሀፍ ቅዱስ መጽሀፈ ምሳሌ 6፡16-19 እንዲህ ይላል እግዚአብሔሄር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች ናቸው ሰባትንም ነፍሱ አጥብቃ ትጸየፈዋለች እርሷም በወንድማማችን መካከል ጠብን የሚዘራ ይላል፡፡ የተዘራዉ የሀሰት ትርክት ፍሬ አፍርቶ ቂምን እንዲቋጥር እና ሀዉልት ሁኖ ለመጭዉ ትዉልድ እንዲተላለፍ  የተፈለገበትን ምክንያት ከተረዳን ይህን እግዚአብሔር የሚጸልየውን ጠብን የሚዘራ ኃውልት መፍረስ አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ በባለጌ መዳፍ እጅ የገባችውን ኢትዮጵያን ፈልቅቆ ያወጣው፣ አይበገሬ ለማ መገርሳ ይህን ማድረግ ይሳነዋል ብዬ አላምንም፡፡

ዋቢ መጽሀፍት

Vestal, Theodore 1999. Ethiopia: A post-cold war African State. Westport, Greenwood

         Publishing Group.

Bekalu Atnafu Taye (2018). Ethnic Cleansing in Ethiopia: The Canadian Journal of Peace and Conflict Studies Volume 50, Number 1 (2018): 77-104 ©2018 Peace Research

ፍቅሬ ቆሎሳ (2008) የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛ የዘር ምንጭ

በእውቀቱ ስዩም (2008) ከአሜን ባሻገር

ጳውሎስ ኛኞ (2003) አጤ ሚኒሊክ በሀገር ውስጥ የተጻጻፏቸው ደብዳቤዎች

ትዕዛዝ ገ/ስላሴ (2008) ታሪክ ዘመን ዳግማዊ ሚኒሊክ

Filed in: Amharic