>

ባለውለታዋን የምትረሳ ከተማ ባለ ተስፋዎቿን አታገኝም!!! (ዳንኤል ክብረት)

ባለውለታዋን የምትረሳ ከተማ ባለ ተስፋዎቿን አታገኝም!!!

ዳንኤል ክብረት

* እቴጌ ጣይቱ ለሀገርዋ የሠራቺው ሥራ ለዐቅመ ሐውልት እንዳልደረሰ የሚያስረዳን ማነው? ሁሉንም ነገር በወገንተኛነት ለማየት መሞከር ዋጋ የሚያስከፍል ስሕተት ነው!!

መቼም አዲስ አበባ የምትባለውን ከተማ ዛሬ ባለቺበት ቦታ ላይ የቆረቀረቺው እቴጌ ጣይቱ ናት፡፡

ይህ እውነታ ነው፡፡ የእቴጌ ሐሳብ ባይደፋ ኖሮ አዲስ አበባ ወይ እንጦጦ ላይ ወይ አዲስ ዓለም ላይ ትቀር ነበር፡፡

እቴጌ ጣይቱ የአድዋን ዘመቻ የመራች፣ ጥበብ በተሞላበት ሁኔታ የእንዳ ኢየሱስን ውኃ አስይዛ ጣልያንን ያንበረከከች፣ ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ መሠረት ከጣሉ ሴት መሪዎች አንዷ ናት፡፡

ለዚች ታላቅ ጀግና አዲስ አበባ ላይ ሐውልት እንዳይቆምላት የሚከለክላት የትኛው የሞራል፣ የሕግ ወይም የታሪክ መሠረት ነው?

እቴጌ ጣይቱ ለሀገርዋ የሠራቺው ሥራ ለዐቅመ ሐውልት እንዳልደረሰ የሚያስረዳን ማነው? ሁሉንም ነገር በወገንተኛነት ለማየት መሞከር ዋጋ የሚያስከፍል ስሕተት ነው፡፡

የአንድ ሰው መመዘኛው ‹ለሀገሩና ለወገኑ ምን ሠራ?› እንጂ የምን አካባቢ ሰው ነው? የሚለው አይደለም፡፡

እዚህ ሀገርኮ ዊንስተን ቼርቺል ጎዳና፣ ቻርልስ ደጎል አደባባይ አላቸው፡፡

ፑሽኪንና ካርል ሄንዝ ሐውልት ተሠርቶላቸዋል፡፡

የአፍሪካ ሀገሮች በሙሉ አዲ አበባ ውስጥ በስማቸው የተሰየመ መንገድ አላቸው፡፡

የከተማዋ መሥራችና ከተማዋ በነጻነት እንድትኖር ዋጋ የከፈለችው ጣይቱ ግን ቁራሽ ቦታ ተነፈጋት፡፡

ከተማ ከገጠር የሚለይበት አንዱ መሠረታዊ ጠባዩ ሁለገብነቱ ነው፡፡

የከተማ ሥልጣኔ የሰው ልጅ ሥልጣኔ መገለጫ ነው፡፡ የእገሌ ወገን የሚባል ሥልጣኔ አይደለም፡፡

ያ ወገን የሚመሰገነው የከተማ ሥልጣኔ መርሕ ገብቶት ለሚሠራ ሁሉ በሩን ክፍት አድርጎ የከተማ ሥልጣኔን ማምጣቱ ነው፡፡

ከተማ በሰው ልጅ የዕውቀት ጭማቂ እንደምታድግና እንደምትደምቅ ገብቶት ይህንን ለመፈጸም በመቻሉ ነው፡፡

በባቢሎን ሥልጣኔ አፍሪካውያን የነበራቸው ቦታ ለማወቅ የፈለገ ሰው ‹From Babylon to Timbuktu: A History of the Ancient Black Races Including the Black Hebrews› የተሰኘውን መጽሐፍ ያንብብ፡፡

የአኩስም፣ የላሊበላ፣ የጎንደርና የአዲስ አበባ ሥልጣኔዎች ከየአቅጣጫው ጥበብና ዕውቀት ፍለጋ የመጡ፣

ለንግድና ለጥቅም የተሰባሰቡ፣ በመንግሥታዊ መዋቅር ሚና የነበራቸው ኢትዮጵያውያንና የውጭ ሀገር ዜጎች የጋራ ሥልጣኔ ማሳያ ናቸው፡፡

ለመሆኑ እነ ሐጂ ቀዋስን የመሰለ የግሪክ መሐንዲስ ለአዲስ አበባ የኪነ ሕንጻ ሥልጣኔ የዋሉትን ውለታ ልንረሳው ነውን?

አርመኖች፣ ግሪኮች፣ የመኖች፣ እንግሊዞች፣ ጣልያኖች፣ ኦስትሪያዎች ለአዲስ አበባ ሥልጣኔ የከፈሉትን ዋጋ ልንረሳው ነውን?

ከተማ ነበረን ብለን የምንከራከር ከሆነ የከተሜ ጠባይ ነበረን ማለታችን ነው፡፡

የከተሜ ጠባይ ደግሞ ውጥንቅጥነትና ውጥንቅጥነትን መቀበል ነው፡፡

የከተማ ሥልጣኔም ከውጥንቅጥነት የሚመነጭ ነው፡፡ ዛሬም ለማደግ የቻሉት የዓለም ከተሞች ውጥንቅጥነትን በሥርዓት ለማስተናገድ የቻሉት ከተሞች ናቸው፡፡

ለአሜሪካዋ የፍሎሪዳ ከተማ ለሚያሚ በዋናነት ሕይወት የዘሩባት ከኩባ ተሰድደው የመጡት ኩባውያን ናቸው፡፡

በዚህ ረገድ ‹The Triple Package: How Three Unlikely Traits Explain the Rise and Fall of Cultural Groups in America› የተሰኘውን መጽሐፍ ማንበብ የሚጠቅም ይመስለኛል፡፡

የምዕራብ አሜሪካ የካሊፎርንያ ከተሞች ያለ እስያውያንና ያለ ሜክሲኮአውያን ሕይወት አይኖራቸውም ነበር፡፡ ከተሜነት እንዲህ ነው፡፡

ውጥንቅጥነትና ውጥንቅጥነትን በሥርዓቱ ለማስተናገድ መቻል፡፡

ከተሜነት ዘውገኛነትን ብቻ ለማቀንቀን የሚችል መርሕ የለውም፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ሐውልት ሊቆምላቸው ወይም መታሰቢያ ሊኖራቸው የሚገቡ ሌሎችም አሉ ብሎ መከራከር አንድ ጉዳይ ነው፡፡እቴጌ ጣይቱ ከእነዚህ ወገን አይደለችም ብሎ መከራከር ግን ከእውነት ጋር መጣላት ነው፡፡ ከተሜነትንም መጣል ነው፡፡ ባለውለታዋን የምትረሳ ከተማ ባለ ተስፋዎቿን አታገኝም፡

Filed in: Amharic