>
6:11 pm - Wednesday November 30, 2022

“ጥሩ መሪ በድል ጊዜ ወደ ሁዋላ በትግል ጊዜ ፊት የሚሰለፍ ነው!!!”

“ጥሩ መሪ በድል ጊዜ ወደ ሁዋላ በትግል ጊዜ ፊት የሚሰለፍ ነው!!!” ዚኖፎን

ፋሲል የኔአለም

የአንዳንድ ሰዎች ጉራ ያጥወለውላል። ጉራና ከልክ ያለፈ “እኔነት” በሽታ ነው። ኢጎ ያሸነፈው ሰው ጽንፈኛ ነው፤ ጽንፈኝነት አውዳሚ ነው፤ በጽንፈኝነት የሚመራ አገር ሲወድም እንጅ ሲገነባ አላየንም። አገር በወጉ የሚመራው በ “Golden mean” መርህ ነው፤ በዚህ መርህ የሚመራ ሰው “ኢጎ” ናላውን አያዞረውም ፤ “ኢጎ” የሌለው ሰው  ጽንፈኛ አይሆንም፣ አገርም አይጎዳም። በሁለት ሲኦሎች መሃል ገነት አለ እንዲል ኦሾ፣ ጽንፈኝነት ሲኦል ነው። በዚህ ጉዳይ መሟገት የሚፈግል ሰው የኦሾን The Hidden Harmony: Discourses on the Fragments of Heraclitus ያንብብ፤ ስለ ኢጎ መዘዝ ብዙ የሚናገረው አለው።
እና አንዳንዶች “የትግል ስትራቴጂ ነድፈን ቄሮን ለድል አበቃነው ” እያሉ አየሩን በውሸት ሲበክሉትና ራሳቸውን ፊት መሪ አድርገው ሲያቀርቡ ሳይ ውስጤ ይናደዳል። ለእነዚህ ሰዎች መልስ መስጠቱ ለአገር የሚያስገኘው ትርፍ ባይኖርም፣ ዝም መባሉ ደግሞ በአገር ላይ ኪሳራ ሊያደርስ ይችላል። እነዚህ የለውጥ መሃንዲስ ነን የሚሉትን ሰዎች በአካል አግኝቼ ባላናግራቸው ኖሮ ለመጻፍም አልደፍርም ነበር። ዛሬ ሁሉም “  ትግሉን የመራሁት እኔ ነኝ ባይ ነው።” ሁሉም ፊት ሆኖ ለመታዬት ሩጫ ላይ ነው፤ ብዙ ሰዎች መረጃ ስለሌላቸው የሚረጨው ውሸት እውነት እየመሰላቸው ያጨበጭባሉ፤  ዛሬ ያጨበጨበ ሰው ነገ እውነቱን ሲያውቅ ጭብጨባውን ወደ ጡጫ ለመለወጥ ፈጣን መሆኑ በበዙ አገር ታሪኮች ታይቷል። በተለይ ጫፍ ላይ ቆመው ህዝብን በውሸት እያታለሉ ኢጎዋቸውንና ቁሳዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት የሚፈልጉ ሰዎች መጨረሻቸው ምንጊዜም እንደማያምር ከሂትለር፣ ሙስሎኒ፣ ሚሎሶቮችንና ሌሎችንም ታሪኮች መማር ይቻላል። ለነገሩ ጥሩ ጄኔራል እኮ በድል ጊዜ የድሉን ዋጋ ለተከታዮቹ እንጅ ለራሱ አይሰጥም። ዚኖፎን የተባለው ፈላስፋ “ጥሩ መሪ በድል ጊዜ ወደ ሁዋላ በትግል ጊዜ ፊት የሚሰለፍ ነው” ይላል፤  መሪ ነን የሚሉት የእኛዎቹ ሰዎች ግን ድል ሲገኝ ራሳቸውን ለማስተዋወቅ የሚቀድማቸው የለም፤ እነዚህ ሰዎች በዚኖፎንና ሰን ቱዙ አይን ዋጋ የሌላቸው ናቸው።
የለውጡ መሃንዲስ ነን የሚሉት ሰዎች፣ ለውጡ እነሱ በሚፈልጉት መልኩ አለመምጣቱን እንኳን ተገንዝበው ለውሸታቸው ልጓም ለማበጀት ፍላጎት የሌላቸው ናቸው። ኢጎ የእዕምሮ ሚዛናቸውን አዛብቶታል። ይህ ለውጥ ሁላችንም በምንፈልገው መንገድ አልመጣም። መሃንዲስ ነን የሚሉት ሰዎች አላማቸው ኢህአዴግ ወድቆ እነሱ የመረጡት ጽንፈኛ ሰው እንዲሾም ነበር፤ እነዚህ ሰዎች ትናንት በእነ አብይ ላይ የስድብ ናዳ ሲያወርዱ የነበሩትም የእነ አብይን ወደ መሃል መምጣ ስለጠሉት ነበር። ድሮውም ጽንፍ የማይመቸን ሰዎች አብይንና ለማን ወደን የደገፍናቸው ወደ መሃል ስለመጡልን ነው። ጽንፈኞች የሚጠሉት ነገር ቢኖር ደግሞ መሃል’ን ነው፤ መሃል ላይ ኢጎ የለም፤ መሃል ጤና ነው።
 ይህ ለውጥ የመጣው “እኔ ነኝ” ባዮቹ እንደሚሉት ሳይሆን፣ ኢህአዴግ ውስጥ በተፈጠረ ስንጥቅ ነው፤ ኢህአዴግን ማን እንደሰነጠቀው ደግሞ ይታወቃል። የ8 አመታት ዘገባዎች ቢፈተሹ የሚመሰክሩት ነው። ኢህአዴግን በውስጡ ሆነው ፣ እሱ የለበሰውን እየለበሱ፣ እሱ የሚናገረውን እየተናገሩ፣ የገዘገዙት ሰዎች ደግሞ መሃላችን አሉ። በኢጎ አረም ስላልተዋጡ ራሳቸውን ለማስተዋወቅ አልፈለጉም፤ ታሪክ ግን አንድ ቀን ይዘክራቸዋል።  እነ ለማ የኢህአዴግን ኔትወርክ ተጠቅመው ትግሉን ባያቀጣጥሉ፣ የለውጡ መሃንዲስ ነን ባዮች የሚለጥፉትን መረጃ እንኳ አያገኙም ነበር። ፌስ ቡክ ሲዘጋ፣  “ይህን መረጃ አጣሩ” ብለን ስንጠይቃቸው እኮ  ውሃ ውሃ ሲሉ አይተናቸዋል። ብቻ ለጊዜው ተከድኖ ይብሰል።
አንድ መራር ሃቅ ላንሳ። ለውጡ የረጅም ጊዜ የስራ ውጤት ቢሆንም፣ የኦሮሞ ህዝብ ከጫፍ እስከ ጫፍ እንዲነሳሳ ያደረገው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጉዳይ መሆኑ አይካድም፤ ክብሪቱ እሱ ነው። ይህ መረጃ መጀመሪያ የደረሰው ለኢሳት ነው፤ ስሙን መጥቀስ የማልፈልገው አንድ ሰው ማስተር ፕላኑን ከሚያዘጋጁት መካከል ስለነበር፣ አንድ ቀን ኢሜል ላከልኝ። “የምሰጥህ መረጃ እጅግ አደገኛ ነው፤  ከፍተኛ ሚስጢር ነው፣ እኔ እንዳወጣሁት ቢያውቁ ይገድሉኛል፤ የምልክበትን ኢሜል ወዲያውኑ አጠፋዋለሁ። ይህ መረጃ የኦሮሞን ህዝብ ከጫፍ ጫፍ ያስነሳሳዋል፤ እርግጠኛ ነኝ በአዲስ አበባ ዙሪያ ትግሉን ለመጀመር ወሳኝ ስለሆነ ደጋግማችሁ ተጠቀሙበት” አለኝ። መጀመሪያ አላመንኩትም ነበር፤ ሰነዱን እንዲልክልኝ ወተወትኩት፤ “ተው ታስገድለኛልህ” አለ፤ እኔ ደግሞ ዳኛ ይመስልን ሰነድ እወዳለሁ፤ ያ ቆራጥ ሰውም፣ ህይወቱን ሸጦ ሰነዱን ላከው።  መረጃውን አወጣነው።  ልክ እሱ እንደገመተው መረጃው ሲወጣ የኦሮሞ ወገኖቻችንን ከእያቅጣጫው ተነሱ፣ ትግሉም መቀጣጠል ጀመረ።  የለውጡ መሃንዲስ ነን የሚሉት ቀርቶ ኦህዴዶች እንኳ መረጃው አልነበራቸውም። እቅዱን በሚስጢር እንዲሰሩ የታዘዙት በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች ናቸው፤ መረጃው እንዲወጣ የፈለገው ሰው ደግሞ ኦሮሞ አይደለም። ትግሉን መሃል አገር ማቀጣጠል እንደሚጠቅም ስለተረዳ ብቻ ነው ሃላፊነቱን የተወጣው፤ መረጃውን አለማውጣት እንችል ነበር፤ እንዲታፈን ማድረግ እንችል ነበር። ግን ትግሉን ስለሚጠቅም ወጣ። ኦህዴድ መግቢያ ያገኘው ያኔ ነው። ትግሉ አብዛኛው ከሰሜን ጎንደርና ከደቡብ ክልል አልወጣ ብሎ አስቸግሮ ስለነበር፣  አልፎ አልፎ አፋርና ጋምቤላ ትግል ቢካሄድም፣ ይህ መረጃ የኦሮሞን ህዝብ ለመብቱ ለማስነሳት መጥቀሙን የተረዳሁት ዘግይቶ ነው።  የኦሮሞ ህዝብ ላደረገው ተጋድሎ ከፍተኛ አክብሮት አለኝ፤ የወደቁት ሰማዕታትም  ሆነ በእስር ቤት የተንገላቱን ሁሉ አላማቸውም ምንም ይሁን ምን ክብር ይገባቸዋል። ይህ ማለት ግን ሌሎች መስዋትነት አልከፈሉም ማለት አይደለም፤ ከቁጫ እስከ አዳማይቱ፣ ከወልቃይት እስከ አሶሳ አሁን ለተገኘው ለውጥ ከፍተኛ ዋጋ የከፈሉ ሺዎች አሉ። ክብር ለሁሉም ይሁን።
ሁሉንም ለጊዜ ልተወው እንጅ፣ በኢህአዴግ ውስጥ አለመተማመን እንዲፈጠር አስቦ በኢሳት የሚወጡትን አብዛኛዎችን የድርጅት ሚስጢሮች ያወጣ የነበረው ሰው  አንገቱን ደፍቶ መሃላችን አለ።  ማንም አያውቀውም።  የማስተር ፕላኑን ሚስጢር እንዲወጣ ካደረገው ሰው እኩል፣ በኢህአዴግ ውስጥ አለመተማመን እንዲፈጠር፣ ህይወቱን አሳልፎ በመስጠት ትልቅ ስራ በመስራት እኩል ዋጋ የምሰጠው ለዚህ ሰው ነው። 8 ዓመታት ሙሉ የህወሃትን የስለላ መረብ አሸንፎ፣ አንዳንዴም ራሱ ደህንነት እየሆነ፣ ሌላም ጊዜ ስሙን እየለዋወጠ፣ የኢህአዴግን ሰነዶች ያወጣ ለነበረው ለዚህ ሰው ትልቅ ዋጋ እሰጠዋለሁ። የሚስጢሮች መውጣት ኢህአዴጎችን እርስ በርስ እንዳይተማመኑ እንዴት እንዳደረጋቸው እነ በረከትን እነ አለምነውን፣ አባዱላንና ሌሎችንም ጠይቋቸው።  በአጭሩ ይህ ለውጥ፣ በምንፈልገው መልኩ ባይመጣም፣ አሁን ያለውም ቢሆን ብዙዎችን ባሳተፈ፣ የረጅም ጊዜ ትግል የተገኘ መሆኑን መርሳት የለብንም።  ለውጡ በጋራ ትግል የመጣ እንደመሆኑ “እኔነትን” አስወግደን አገራችንን ወደ ተሻለ ጎዳና ለመውሰድ የሁላችንም ተሳትፎ ያስፈልጋል። በዚህ ትግል ማን ምን ተሳትፎ ነበረው የሚለውን፣ ታሪክ መስራት አቁመን ታሪክ  መጻፍ ስንጀምር ሁላችንም የምናውቀውን እንጽፋለን። ለአሁኑ ግን ገና ያልተጠናቀቀ ስራ አለና ሃሰትን ለሃሳታውያን ትተን ስራችን ላይ እናትኩር።
Filed in: Amharic