>

አቶ ለማ መገርሳን ብሆን ጃዋርን እንዲህ እለው ነበረ!!! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው) 

አቶ ለማ መገርሳን ብሆን ጃዋርን እንዲህ እለው ነበረ!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው 
አቶ ለማን ሆኘ መናገርና ሐሳቤን በቀጥታ መናገር ያልፈለኩበት ምክንያት ሁለት ምክንያቶች አሉ፡፡ አንደኛው እንደምታውቁት የለውጥ ኃይልና የለውጥ እንቅስቃሴ በሚባለው ነገር ከፍተኛ ጥርጣሬ ስላለኝ ሲሆን ሌላው ደግሞ ጃዋር ሞሐመድ እራሱን አንቱ ብሎ እብሪቱን ፈጽሞ በማይጠበቅ ደረጃ አለቅጥ ወደላይ ማጎኑና የሌላን ሰው ዋጋ ለመውሰድ መጣሩ በእጅጉ ስለገረመኝ ትክክልም ስላልሆነ ነው፡፡
ጃዋር ታማኝ ላቀረበለት ጥሪ የሰጠውን አጭር ምላሽ አነበብኩት፡፡ እዚያ ላይ ነው ጃዋር ለራሱ በእጅጉ የተሳሳተ ግምት እንዳለውና አሁን አለ የሚባለውን ለውጥ በማምጣቱ ትግል ከፍተኛውን ዋጋ ለራሱ እንደሚሰጥ ያየሁት፡፡ እርግጥ ከዚህ በፊትም ሀገርን ያህል ነገር እጁ ላይ እንዳለ ቂጣ መቆራረስ የሚችል ሰው አድርጎ ራሱን በገለጠበት ንግግሩም ይሄ ሰው ለራሱ ያለው ግምት ምን ያህል የተጋነነና የተሳሳተ እንደሆነ ተገንዝቤ ነበረ፡፡
እርግጥ ነው አንድ የማይካድ ነገር አለ፡፡ ቅስቀሳው በሞራል (በቅስም) ድንጋጌ ሲታይ፣ በሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ ሲለካ፣ በሐቅና እውነትን ላይ መመሥረት አለመመሥረቱ ሲፈተሽ፣ በዲሞክራሲያዊነት (በመስፍነ ሕዝባዊነት) መመዘኛ መስፈርት ሲመዘን በእጅጉ ቀሎ የሚገኝ፣ የሚነቀፍና የሚወገዝ ነው ወይስ ሚዛን የሚደፋና የሚበረታታ??? የሚለውን እንተወውና ጃዋር በተለይ መገናኛ ብዙኃንን ካቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ ቅስቀሳ ሲያደርግ የቆየ ሰው መሆኑ ግልጽና በማገባ የሚታወቅ ነገር ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ጃዋር በኦሮሞ ወጣቶች ዘንድ ከፍተኛ ዕውቅና ለማግኘት በቅቷል፡፡
ይሁንና ግን ለውጡ ጃዋር እንደሚያስበውና እንደሚመስለው የሱ ውጤት ነው ወይ? ብለን ብንጠይቅ መልሱን አቶ ለማን ሆኘ ልመልሰውና “ዋናው ድርሻ የሕዝቡ ዐመፅ መሆኑ እንዳለ ሆኖ በግለሰብ ደረጃ ሰው እንጥቀስ ከተባለ ግን ለዚህ ለውጥ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው የእኔ፣ የደመቀ፣ የዐቢይና የገዱ እንጅ ፈጽሞ የአንተ የጃዋር አይደለም!” የሚለው ነው ትክክለኛ መልሱ፡፡
ለአሁኑ ወይም ለጊዜው የእነኝህ የእነ አቶ ለማ ቡድን አደረጉት የሚባለው ተጋድሎ እውነት እንደሆነ እንቁጠርና የቄሮን ዐመፅ የአማራ ማንነት ተጋድሎም ወይም ፋኖም ባይቀላቀልና እነ አቶ ለማ እነ አቶ ገዱን ጨምረው በወያኔ ላይ አድመው ፊታቸውን አዙረው ወያኔን ባይፈነግሉት ወይም ባያገሉት ኖሮ የቄሮ ዐመፅ ብቻውን ምን ሊፈጥር ይችል ነበር??? ብለን ብንጠይቅ በእርግጠኝነት ነው የምነግራቹህ ምንም ነገር መፍጠር አይችልም ነበር፡፡
ደርግ ቀይሽብርን አውጆ ያመፁ ወጣቶችን ከመላ ሀገሪቱ በመፍጀት ለ17 ዓመት አገዛዙን ማስቀጠል እንደቻለ ሁሉ ወያኔም ያመፀው ቄሮ ብቻ በመሆኑና ትኩረቱን የሚሻማ፣ ኃይሉን የሚከፍልና የሚያሳስብ ችግር በሌላ የሀገሪቱ ክፍል ስለሌለ ሙሉ ትኩረቱን ቄሮ ላይ ብቻ በማድረግ በቄሮ ላይ እንደ ደርግ ቀይሽብርን አፋፉሞ አስፋልቱን ባመፀው ወጣት ደም ጎርፍ አጥቦ የቄሮን ዐመፁ ፀጥ ረጭ በማድረግ ተደላድሎ መግዛቱን ይቀጥል ነበር እንጅ የቄሮ ዐመፅ ብቻውን አንድም የሚለውጠው ወይም ጠብ የሚያደርገው ነገር አይኖርም ነበር፡፡
የዛሬ አራት ዓመት ዐመፁ ሀ ብሎ በጅማ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ሲቀሰቀስም ዐመፁ ለመቀስቀሱ ጃዋር ምንም ሚና አልነበረውም፡፡ ዐመፁ የተቀሰቀሰው እኔ ዕንቁ መጽሔት ላይ የጻፍኩትን ጽሑፍ በመቃወምና በማውገዝ ተማሪዎች እኔና የመጽሔቱ አዘጋጅ ለፍርድ እንድንቀርብ ጠይቀው በዚያ ሰዓት ጥያቄያቸው ተፈጻሚ ሆኖ ስላልነበረ ነው ዐመፁ የተቀሰቀሰው፡፡
ዐመፁ ከተቀሰቀሰ በኋላም ተማሪዎች ኦሮሚያ በሚሉት የሀገራችን ክፍል ባሉ ዩኒቨርስቲዎች (መካናተ ትምህርት) እና የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች እየተደዋወሉ ዐመፁን እንዲቀጣጠል ሲያደርጉት የኦሕዴድ ካድሬዎች (ወስዋሾች) ይሄንን መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም በመፈለግ እኔን ምክንያት ማድረጉን ትተው የአዲስ አበባን የማስፋፊያ አቅድ ወደመቃወም እንዲዞር አደረጉትና ዐመፁ በታየው መልኩ ሊቀጥል ቻለ፡፡
እነ ጃዋር ዐመፁ ከተቀሰቀሰ በኋላ ነው ዐመፁ እንዳይበርድ እፍ እያሉ በማንደድ የተሳተፉት፡፡ ወደ መጨረሻ ላይ በነበረበረው የመቋጫ ከበድ ያለ ዐመፅ እንዲያውም እነ ጃዋር የዐመፁ ተቃዋሚ ሆነው ዐመፁ እንዲቆም ጥሪ በማቅረብ ተጠምደው ነው የነበረው ሰሚ አላገኙም እንጅ፡፡ ከዚያ በፊትም ቢሆን ዐመፁ በወጣቶች ዝም ብሎ ይደረጋል እንጅ ባለቤት አልነበረውም፡፡ ጃዋርና ኦነግ በአሜሪካ ድምፅ ከዐመፁ ጀርባ ስለመኖራቸው ወይም የዐመፁ ባለቤት ማን እንደሆነ ሲጠየቁም ወጣቱ በወያኔ አገዛዝ በመማረሩ ማመፁን እንደሚያውቁ ተናገሩ እንጅ እኛ ነን አላሉም ነበረ፡፡ ወደኋላ ግን ዐመፁ ባለቤት አልባ መሆኑ ተመቻቸውና ኦነግ እና እነ ጃዋር “እኔ ነኝ እኔ ነኝ!” በማለት ለመሻማት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል፡፡
ጃዋር ዐመፁ ከተቀሰቀሰ በኋላ እሳቱ እንዳይጠፋ እፍ በማለት አስተዋጽኦ ነበረው ስልም ጃዋር አሁን ሠለጠነና ከልቡ ይሁን አይሁን እግዚአብሔር ይወቅለትና ከጎሳ ተኮር አስተሳሰቡ አለመላቀቁ እንዳለ ሆኖ አሁን አሁን አንጻራዊ በሆነ መልኩ ደረጃውን የጠበቀ አስተሳሰብ ለማንጸባረቅ በቃ እንጅ ቀደም ሲል በነበረው ጊዜ ግን ቅስቀሳው ሁሉ ሜንጫን ያካተተ አደገኛ፣ ጠባብ፣ እጅግ ኋላቀር፣ ያልሠለጠነና ጽንፈኛ፣ ሐሰትና ሕዝብን አሕዛብ ጋር የሚያባላ የፈጠራ ወሬ፣ ፀረ ሀገርና ፀረ ሕዝብ መርዘኛ ስብከት ነበረ ቅስቀሳው የተሞላው የነበረው፡፡
ጃዋር ከጽንፈኝነት በፀዳ፣ በትክክለኛና ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ፣ ትክክለኛ መረጃንና ታሪካዊ እውነታን በጠበቀ መንገድ፣ የሀገርን ህልውና ባልተገዳደረ መልኩ ቅስቀሳውን አድርጎ የኦሮሞ ወጣቶችን አነሣሥቶና ቀስቅሶ ቢሆን አሁን እየተሰማው ያለው ኩራትና እብሪት ቢያንሰው እንጅ የሚበዛበት ባልነበረ፡፡ የሆነው ግን ይሄ አይደለም፡፡
ጃዋር “ከመለወጡ በፊት” የሰበከው ጽንፈኛ ስብከት እነኝህ በእሱ የተሰበኩ የተቀሰቀሱ ወጣቶችን ሻሸመኔ ላይ እንደታየው ንጹሕ ሰው ገለው አስከሬን በአደባባይ ላይ እንዲሰቅሉ በማድረግ እጅግ ነውረኛና ኢሞራላዊ ተግባር አስፈጸማቸው እንጅ የማመዛዘን፣ የማስተዋል፣ ኃላፊነት የመሸከም ክህሎትን አጎናጽፎ ከእንዲህ ዓይነት አረመኔያዊ አጸያፊና ነውረኛ ተግባር አላቀባቸውም፡፡ ይሄ ደግሞ የሚያሳፍር የሚያሸማቅቅ እንጅ የሚያኮራ የሚያንጠራራ ጉዳይ አይደለም፡፡ ጃዋር እንዴት እንደሚያስብና ምን ዓይነት ሰብእና እንዳለው ባላውቅም፡፡
እናም ጃዋር የነበረውን ሚና ከላይ ከገለጽኩት በግልጽ ማየትና መረዳት እንደሚቻለው ለዚህ ለውጥ ጃዋር ፈጽሞ ምንም ዓይነት ሚና አልነበረውም ባይባልም መጠነኛ ድርሻ ያለው መሆኑን ግን በግልጽ ማየትና መረዳት ይቻላል፡፡
ስለሆነም የጃዋር እብሪትና ኩራት ፈጽሞ መሬት ላይ ከነበረው ነባራዊው ሁኔታ ጋር የማይገናኝ፣ የማይዛመድ፣ የማይመሳከር በመሆኑ ትክክል አይደለምና ጃዋርን በሌለና ባልነበረ አበርክቶህ ልክ የሌለው ኩራትና እብሪት “እኔ ነኝ!” እያልክ እራስህን አታስታብይ፣ አታንጠራራ፣ አታንግሥ፣ ጭንቅላትህን አሠራውና አስብ ሰከን በልም፡፡ መኩራራት መንጠራራት መታበይ ከፈለክ ያቅምህንና የነበረህን አበርክቶ ያህል ብቻ ተኩራራ፣ ተንጠራራራ፣ ቃዥ በሉልኝ እባካቹህ???
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
Filed in: Amharic