>

አማራ ሲበደል ያልጨነቀው፣ አማራ ሲደራጅ ለምን ይጨነቃል??? (ጌታቸው ሺፈራው) 

አማራ ሲበደል ያልጨነቀው፣ አማራ ሲደራጅ ለምን ይጨነቃል???
ጌታቸው ሺፈራው
~በኢትዮጵያ ፖለቲካ ያልተተነበየ ደርሷል። ኢህአዴግ ሊቀየር ይችላል ብለው የገመቱ ቢኖሩ እንኳ በኦህዴድ ፊት አውራሪነት፣ ያውም ትህነግ/ህወሓትን በሚቃረን መልኩ፣ ያውም የኦሮሞ የፖለቲካ ልሂቃን ኢትዮጵያ ሱሴ ነች እያሉ በአንድ አፍታ ተቃዋሚውን ሁሉ አሸሸ ገዳሜ ያስመቱታል ብሎ የጠበቀ አልነበረም።  የዚህ ቀመር መነሻና ዘዋሪ ማን ነው የሚለው ሌላ ነገር ሆኖ ለፕሮጀክቱ ቅምጥ ደጋፊ ተደርጎ ከተወሰዱት መከካል ግን አማራው ቀዳሚው ነው። የኦሮሞ ድርጅት ገፊነት፣ በኦሮሞ ልሂቃን ፊት አውራሪነት የተዘመረለት ይህ ፕሮጀክት ኦሮማራ በሚል አማላይ ሙዚቃ እየታጀበ መጥቷል። ደመቅ እያለ የታየው ደግሞ አማራውን በጊዜያዊነትም ቢሆን ያንቀሳቀሰውን የጣናን እንቦጭ ለመንቀል በነበረው ዘመቻ ወቅት ነው። ኦህዴድ እምቦጭ የሚነቅሉ የኦሮሞ ወጣቶችን ወደጣና በላከበት ወቅት ይህ ኦሮማራ ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ደርሷል። ይህ እግረ መንገዱም በአማራና ኦሮሞ መካከል መልካም ግንኙነት እንዲኖር ተስፋ የሰጠ፣ የሀሰት ትርክቶችን ጓዳ  በሰፊው ሕዝብ ዘንድ እንዲጤኑ  ያደረገ በመሆኑ መልካምነቱ የላቀ ነበር። በዚህ ወቅት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የትኛውም ጥግ የነበሩ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ከአሉታዊ መቀስቀሻ ስሜታቸው ወጥተው የ”ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን” ደግፈዋል። ወይንም ዝምታን መርጠዋል። አብዛኛዎቹ በኦሮማራ ፕሮጀክት ተስማምተው ጉዞውን ደግፈዋል። ለእነዚህ ልሂቃን የተሰጠ አንዳች ተስፋ ባይኖር በዘመቻው ላይ ጣት ሲቀሳሰሩ ባየን ነበር። ሆኖም የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው በሚል በትህነግ ላይ የተነሳውን ተቃውሞ በድል ለመወጣት አማራው ጋር መጓዝን እንደአዋጭ ስልት ያዩት ተቃዋሚዎች እንዲሁም በኢትዮጵያ ሱሴ ፕሮጀክት  አማራውን ቅምጥ ያደረጉ የኦህዴድ ሰዎችና ደጋፊዎች በዚህ ዘመቻ የገቡት ከዚህ ወቅትና በፊትም መከራውን ሊነገሩለት ቀርቶ፣ በገዥነት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ለተፈጠረው አሉታዊ ነገር ሁሉ ተጠያቂ የሚያደርጉትን አማራ የፕሮጀክታቸው  ቀዳሚ ቅምጥ ደጋፊ አድርገው በማሰብ ነው!
~እነ ዶክተር አብይ አህመድ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ሲያቀነቅኑ አማራው ድጋፍ እንደሚሰጣቸው በሙሉ ልብ ነው የገቡበት። ዶክተር አብይ ስልጣን ከያዘ በኋላ ጉብኝት ያደረገው ለአንድነቱ ብቻ ሳይሆን ለስልጣኑም ያኮረፉ የመሰሉት ቦታዎች ላይ ነው። ለስልጣኑም ሆነ ለአንድነቱ ስጋት የመሰለውን የአብዲን አሌ የሚገዛውን ክልል ከጎበኘ በኋላ ያቀናው  እነ በቀለ ገርባ በኦሮሞነት ያስጨፈሩትን አምቦን ነው። ከዛም ያቀናው ከ”መደመር” ፖለቲካው የሸሸውን ትህነግ መቀመጫ ወደሆነው ትግራይ ነው።
በእነዚህ ሁሉ መድረኮች ለስልጣኑም ሆነ ለአዲሱ ፕሮጀክት አስጊ የመሰሉትን ሲያባብል፣ ድጋፉን ይቸረኛል ብሎ የገመተው የአማራውን በደል ሲያወራ አልተሰማም። እንዲያውም ትህነግን ለማስደሰት ሲባል “አንድነት፣ አንድነት ስለው ወከክ ይልልኛል” ያለውን የአማራው ዋና ጥያቄ፣ ወልቃይት ላይ ቀይ መስመሩን ተሻግሯል።  መጀመርያ የጉዞ እቅዱ ወዳልነበረው አማራው ለመሄድ የተገደደውም ትህነግን ለማባበል ሲል በአማራው ላይ የሰነዘረው  አስተያየት ብዙ ተቃውሞ ሲያስነሳበት ነው።
~ትህነግን ለማስደሰት የወልቃይትን ጉደይ  የመሰረተ ልማት ነው ያለው ዶክተር አብይ ይህ አስተያየት ያልጠበቀውን ተቃውሞ ሲያመጣበት፣ ወደጎንደርና ባህርዳር አቅንቶ ስህተቱን ለማስተባበል ተገድዷል። በዚህ ወቅትም ቢሆን ግን የአማራውን  ቁስል ለመናገር አልደፈረም።  አንድነት አንድነት ስለው ወከክ ይላል ብሎ በዋነኛ የፕሮጀክቱ ደጋፊነት ያስቀመጠው አማራውን በስቴዲየምም ሆነ በአዳራሽ አግኝቶ ሲያወያይ የገጠመው ያልጠበቀው ነበር።  ከዛ በፊት በኢህአዴግ፣ ኦህዴድም፣ እነ ዶክተር አብይም በደሉን የማይናገሩለት፣ ይልቁንም ሲከሰስ የኖረው አማራው ቁስሉ ላይ ትኩረት አድርጎ አግንቶታል። ይህ ለዶክተር አብይ አስደንጋጭ ነበር።
~አማራው ካሰበው በላይ ስለ በደሉ አብዝቶ ሲናገር፣ ኢትዮጵያ ብሎ ስለለፋ የተጠቃ እንጅ ያልተጠቀመ፣ እነ አብይ ሱሴ ነው ስላሉ ብቻ እንዳሰቡት የሚዘምር አለመሆኑ ሲገባው ከባህርዳር በተመለሰ በቀናት ውስጥ ይህን የሕዝብ ብሶት ያቀዘቅዙልኛል ያላቸውን፣ መቼም ቢሆን አማራውን በማንነት እውቅና ሰጥተው ተከራክረው የማያውቁትን እንዲያውም በማንነት መደራጀቱን የሚቃወሙትን እነ ዳንኤል ክብረት የአማራ ወኪል አድርጎ ጠርቷል።  የአማራውን በደል በግልፅ ከሚናገሩት ይልቅ በአንድነቱ ፖለቲካ እንጅ በማንነት የተደራጀው የአማራ ሀይል ጎን አይተናቸው የማናውቃቸውን እነ አበባው አያሌውን፣ እነ ሰርፀ ፍሬስብሃትን በአማራው ጉዳይ ማቅረብ ጀመረዋል። እነ ዶክተር አብይ የተለያዩ ሀገራዊ ኮሚቴዎችን ሲያቋቁሙ በማንነት የተደራጁ የሌሎች “ብሔሮች”  ፖለቲከኞችን በብዛት ሲያካትቱ አንድም የአማራውን ጥያቄ በግልፅ የሚያነሳ ሰው አልመረጡም። የአማራውን ሕዝብ ይወክላሉ ተብለው የተመረጡት ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ቀናኢነት ኖሯቸው ፖለቲካውን በርቀት ከማየት ውጭ ለአንድነት ኃይሉም ቅርበት የሌላቸውም  ጭምር ነው። እነ ዶክተር አብይ በአንድ በኩል  ፅንፈኛ ብሔርተኛውን በኮሚቴ ውስጥ ሲያካትቱ፣  በአማራውን ወገን ይህ ነው የማይባል፣ የሌላውን ፅንፈኛ ብሔርተኛ እየሰጉ፣ የአማራውን መደራጀት በግልፅ ሊቃወሙላቸው የሚችሉትን  ግለሰቦች ማካተታቸው  ለአማራው መደረጀት ያላቸውን አመለካከት በግልፅ ያሳየ ነበር።
~በቅርቡ በተደረገው የአማራ ተወላጅ ምሁራን ምክክር መድረክ ላይ “አማራ” ተብለው መድረክ ላይ መቀመጥ የማይፈልጉት እነ ሰርፀ፣ እነ ዳንኤልም በእነ አብይ ምርጫ ተገኝተዋል። እነዚህ የአብይ ምርጫዎች በተለይም ዳንኤል ክብረት ለጠንካራ ትችት የዳረገውን “ጥናታዊ” ፅሑፍ አቅርቧል። ይህ ጥናት የተባለ ፅሑፍ በተዘዋዋሪም ሆነ በቀጥታ አማራ መደራጀት እንደሌበት የሚገልፅ እንጅ  የሚደግፍ እንዳልነበር ተገልፆአል። በዚህ መድረክ “አማራ” ተብለው ከቀረቡት መካከል  አንደኛው “አማራ ነን” የሚል ሙዚቃን እንደሚፀየፍ ሲናገር ተደምጧል።
~ከዚህ መድረክ ባሻገር ዶክተር አብይ አህመድ አሜሪካ በሄደበት ወቅት “ድልድዩ ፈረሰ” ያለው ከጃዋር ጋር ሲገናኝ አይደለም።  ወለጋ፣ መቀሌ ወይንም ጅግጅጋ ሳይሆን አማራው ዘንድ  “ጉሮ ወሸባዬ” ተብሎ አቀባበል ሊደርለት የሚችለውን አርቲስት ታማኝ በየነን ሲያገኝ እንጅ። ምንም እንኳ በዳያስፖራው  ዘንድ የአርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነን ያህል ተቀባይነት ያለው ባይኖርም፣ የእነ ዶክተር አብይ ፕሮጀክት ከዛም በላይ ነበር።
~ታማኝ በየነን ዜጎች በተለይ አዲስ አበባ፣ እና አማራ ክልል ላይ ሳይቀሰቀሱ የሚቀበሉት ሰው ቢሆንም በመንግስት ደረጃ ብዙ ተጥሯል። ባህርዳር ላይ ለታማኝ አቀባበል ለማድረግ መንግስት ሚሊዮን ብሮችን አውጥቷል። እነ አብይ በብአዴን በኩል ይህን ሲያወጡ ግን  ታማኝን ስለሚያከብሩት ብቻ አልነበረም። እንደ አዲስ የሚንቦገቦገውን የአማራውን  ብሶት ረገብ ለማድረግ ነው። በእርግጥ ታማኝ እነ ዶክተር አብይ ባሰቡት መንገድ የሄደ አይመስልም። ሁሌም እንደሚያደርገው የሕዝብን ቁስል አይክድም። አሁን ባለው ወቅታዊ የሀገር ሁኔታ አማራ መደራጀት የለበትም ብሎ በግልፅ  አላወገዘም። የአማራው መደራጀት የማያስገባቸው ኃይሎች እንዳሉ ግን የእነ ዶክተር አብይንና የአንድነት ኃይሉን ጭንቀት በገደምዳሜው ተገናግሯል።
~በአማራው ላይ ፕሪጀክት የሚነድፉት እነ አብይ ብቻ አይደሉም። የአንድነት ኃይሉም ሲዞር ውሎ መቀመጫው አማራው፣ አንዳንድ ከተሞች፣ ደቡብ (በአመዛኙ ጉራጌና አርባምንጭ አካባቢ)  ነው። እነ ዶክተር አብይ  የፕሮጀክታቸውን መሰረት መከራውን የማይናገሩለት አማራው ላይ ለመጣል እንደሚያስቡት፣ ከአማራ ጠሉ ተገንጣይ ጋር ለመቀራረብ አማራውን በመርገም፣ ወይንም የአማራው መከራ ቢነገር ኢትዮጵያ የምትፈርስ ያህል መከራውን በሚገባ የማይናገሩለትን አማራውን የፕሮጀክታቸው ማስፈፀሚያ አድርገው ያስቡታል። በዚህ ሂደት የተካደው አማራው ከብዙ ትግስት በኋላ በደሉን ጮህ ብሎ  በራሱ መናገር ሲጀምር እንደነ ዶክተር አብይ በመንግስታዊ መዋቅር ተጠቅመው ብሶቱን ለማቀዝቀዝ ባይችሉም፣ አማራውን የሚፈልጉት ለምን እንደሆነ ግን  ድርጊታቸው እየገለፀ ነው። መከራውንና ቁስሉን በሚገባው መጠን ቢናገሩ ተገንጣዮች የሚያኮርፏቸው፣ ኢትዮጵያም የምትበተን የመሰላቸው ወይም የሚያስመስሉት  የአንድነት ኃይሎች ከሌሎች ብሔርተኞች ጋር እየተቃቀፉ አማራውን ግን በጠባብነት፣ በጎጠኝነት እየፈረጁ ነው። በቻሉት መጠን ከበዳዮቹ ባልተናነሰ ብሶትና በደል እንዳይነገር፣ ሕዝብ  እንዳይደራጅ እየሰሩ ነው። ሌላ ቦታ ላይ የማይደፍሩትን  ቦዝነው ውለው ሲመለሱ እንዲሁ የሚያገኙት የመሰላቸው አማራው ላይ የሚያዩትን  እንቅስቃሴ በጠላትነት እየፈረጁ ነው። አማራው ለአንድነት እሳቤ አዲስ ይመስል ሌላ ቦታ ላይ የማያደርጉትን  ስብከት አማራው ላይ ለማድረግ ሲደክሙ፣ አማራው ይዞት የኖረውን ሲደግሙ እየተሰማ ነው። ሌላ መሄጃ እንደሌለ የአማራው መደራጀት የእነሱን የስልጣን ገመድ የበሰጠ መሆኑን በድንጋጤ እያሳዩ ነው።
~ ይህ  የአንድነት ኃይሉ ድንጋጤ ኢትዮጵያዊነት ሱሴ ነው ከሚለው የእነ ቲም ለማ አካሄድ ጋር ያመሳስላቸዋል። የአማራውን በደል ረስተውት ኖረዋል። እንደገዥዎቹ ባይሆንም ከፅንፈኞቹ ጋር አብሮ ለመዋል አማራን መስደብ፣ ሲያንስ በደሉን መሸፋፈን  ስልት አድርገውት ቆይተዋል። እንደ እነ ዶክተር አብይ ሁሉ የአንድነት ሀይሉም አማራው በደሉን በራሱ ሲናገር በድንጋጤ ጮኸቱ እንዲቆም ብቻ ሳይሆን ሌላው ላይ የማያደርገውን እንዲበተን የቻለውን እየሰራ ነው። የእነ ዶክተር አብይም ሆነ የአንድነት ኃይሉ የአማራ መበደል፣ አማራ ሲደራጅ  ያስጨነቀውን ያህል አስጨንቆት አያውቅም። የአማራው ቁስል፣ አማራ በራሱ ቁስሉን ሲናገር ይዞታየን ተቀማሁ በሚል ስሜታዊ ያደረገውን ያህል ስሜታዊ አድርጎት አያውቅም። አማራ ሲደራጅ  ያዙኝ ልቀቁኝ ያለውን ያህል አማራው የሚይዘውን የሚጨብጠውን ባጣበት ወቅት ስሜት ውስጥ አልገባም። ይህም ለአማራው ያለውን፣ ለአማራው የሚያስገኘውን ሳይሆን አማራው ላይ ያለውን፣ አማራው ላይ የሚያገኘውን ጥቅም፣ በተለይም ስልጣን እያሰበ ሲሰራ እንደኖረና እየሰራ እንደሆነ የሚያሳይ ነው። ገዥዎችም ሆነ ተቃዋሚ ነኝ የሚለው የአንድነት ሀይል አንድ የሚያደርገው አማራው ሲጠቃ የሚገባውን ሳይናገር፣ ወይንም ሲረግመው ኖሮ፣ አማራው ሲደራጅ የሚያወግዝ፣ እንዳይደራጅ የሚሰራ መሆኑ ነው። ይህም ለአማራውን መንቀሳቀሻ ሜዳ፣    የስልጣን   ፕሮጀክት አድርጎ አስቦት እየሰራ እንጅ አስቦለት እንደማይሰራ ትልቅ ማሳያ  ነው!
Filed in: Amharic