>
5:14 pm - Sunday April 20, 5147

ታማኝ እና ወልቃይት!

ታማኝ እና ወልቃይት!
ጌታቸው ሽፈራው 
ታማኝ “ወልቃይት የኢትዮጵያ ነው” ማለቱን የሰሙ ብዙ ብሎገሮች ተቃውሞ ሲያሰሙ አይቻለሁ! ማህበራዊ ሚድያ ላይ ብቻ ሳይሆን ሕዝቡም በጊዜው መልስ ሰጥቷል። የአማራ ነው ብሎ። ታማኝ ግን “ጠብቁኝ፣ ጠብቁኝ!” ነበር ያለው። ቀጥሎ ያለው ግልፅ ነበር። ማህበራዊ ሚድያ ላይ ይህን ተቃውሞ ያሰሙ ቀጥሎ የተናገረውን የት እንደጣሉት አላውቅም። አጀንዳውን ማደርጀት የፈለገ ሰው ከታማኝ በርካታ ነገር ሰምቷል።
ወልቃይት የኢትዮጵያ ነው ካለ ኢትዮጵያ የት? በሕዝቡ ምላሽ ታማኝ ወልቃይት የማን እንደሆነ አልተናገረም? ለእኔ ተናግሯል!
ታማኝ “ጠብቁኝ” ብሎ “ወልቃይትን አስገድዶ የሌላ ብሔር ማድረግ አይቻልም!” አለ። ይህ መልዕክት ምን ማለት ነው? ማን ነው ያስገደደው? ሱዳን ነው? ሶማሊያ ነው? ይህ ግልፅ ነው። አስገድዶ የትግራይ ማድረግ አይቻልም ማለት ነው። ከማን ነው ያስገደደው? ከአፋር ነው? ከኦሮሚያ ነው? ተው እንጅ ፈትፍታችሁ አጉርሱኝ እንዳይሆን!
ታማኝ ቀጠለ። “ወልቃይትን በሰነድ፣ በታሪካዊ ማስረጃ፣ በሕግ ሊመልሱ ይገባል”  ሲል ተናገረ። “ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ጀግናው ኮ/ል ደመቀ ዘውዱን እናሳያችኋለን” አለ። ይህ ምን ማለት ነው? ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ወልቃይትን የማን ነው ይላል? የግብፅ ነው? ታማኝ ወልቃይት በሰነድ፣ በታሪካዊ ማስረጃ ይመለስ የሚለው ለኬንያ ነው? ኮ/ል ደመቀ ዘውዱን ለምን ያሳያቸዋል? ኮ/ል ደመቀን አይተው ወልቃይትን ለየመን ነው የሚሰጡት?
የብሔርተኛው ችግር የሚመስለኝ!
~ብሔርተኛው የሚያምንበትን፣ ከአንድነት ጎራው ያለው ታማኝ በአንድ መድረክ ፍርጥርጥ አድርጎ እንዲናገር ማሰቡ
~ታማኝ የትኛው አቋም ውስጥ እንዳለ መዘንጋቱ እና የብሔርተኛውን የተወሰነ ጥያቄ እውቅና ሲሰጥ ማስረገጥ አለመቻል
~ የሕዝብን ግብረ መልስ አይቶ የተሰጠ አስተያየት ካለ የሕዝብን ግፊት አለማድነቅ፣ ስንት የሕዝብን ጥያቄና ቁስል የሚክድ እያለ የተወሰነውን የሚያንኑ ሲገኙ የእነሱን አቋም መዝዞ አጀንዳን የማደርጀት ልምድ ማነስ ነው!
በዚህ ረገድ ሸምጣጭነት እንዳለ ሆኖ፣ በአንድነት ጎራ ያሉ ፌስቡከኞች ከስንቱ ንግግር መሃል ሰበዝ መምዘዝ ይችላሉ። ለአብነት ያህል ታማኝ 2 ሰዓትም አውርቶ በማንነት መደራጀት አይገባም ቢል  ማህበራዊ ሚድያውን ያጣብቡት ነበር። አብን ላይ አንድ ነቀፌታ ቢያቀርብ የሁለት ቀን አጀንዳ ባደረጉት ነበር። ብሔርተኛው ታማኝ ስለ አብን የተናገረውን አያየውም፣ አማራውን ስለ ኢትዮጵያዊነት ለመስበክ ሞራል የለኝም ያለውን አይቶ ያልፈዋል።
ታማኝ ዛሬ ብዙ ነገር ብሏል። በአመዛኙ ብሔርተኛው የሚያነሳውን ጥያቄ እውቅና በመስጠት ነው። ይህን ግን መዝዞ የራሱን አጀንዳ ማስረገጫ በማድረግ በብሔርተኛው ሰፈር ትኩረት ያንሳል።
አይደለም ታማኝ፣ ከጠላት ወገን እንኳ የራስን አጀንዳ የሚያደረጅ ሰፊ ንግግር ቀርቶ አረፍተ ነገር፣ ቃልም ሲገኝ መምዘዝና መጠቀም በተገባ! እነ ደብረፅዮን በወልቃይትና ራያ ላይ መግለጫ ሲሰጡ ከሙሉው የውግዘት መግለጫ ባሻገር ተሳስተውም፣ አምልጧቸውም የሚናገሩትን አንድ ዐረፍተ ነገር፣ ቃል መያዝ ያስፈልጋል!
ሙሉውን ፍርጥርጥ ያድርገው ከሆነ ግን የሚዛን ችግር ይሆናል። ነባራዊ ሁኔታውን አለማወቅ ይሆናል! አጀንዳ ሲመዝም ሆነ ሲሰጥ ሙሉ ስምምነት የሚፈልግ ካለ ከየትም አያገኝም።
ያ አጀንዳ፣ የባለቤቱ ይሆናል! ሙሉውን የሚናገረው ራሱ ነው። ከሌላ ሰው፣ ሌላ አቋም ካለው ሰው የሚጠብቀው የድጋፍ ሀሳብ እንጅ ሙሉ መግለጫ አይደለም።
Filed in: Amharic