>
6:19 pm - Monday May 16, 2022

ነውር እንደ ጌጥ ሐጥያት እንደ ፅድቅ የተቆጠረበት ዘመን (አሰፋ ታረቀኝ)

ነውር እንደ ጌጥ ሐጥያት እንደ ፅድቅ የተቆጠረበት ዘመን

አሰፋ ታረቀኝ

   የእቴጌ ጣይቱ ብጡልን ሀውልት አዲስ አበባ ላይ ለማቆም በተነሳ ጥያቄ የተነሳው አቧራ አከባቢውን ጋርዶት ሰንብቷል፡፡ አይሰራም ባዮቹ ያቀረቡትን ምክንያት ለማየት እድል አላጋጠመኝም፡፡ ኢትዮጵያ እጅግ የደለበና ተቆፍሮ የማያልቅ የታሪክ ማእድን ናት፡፡ ከማእድኑ እየቆፈሩ ለትውልድ ማስተላላፍ የተሳናቸዉ የአዕምሮ ዲኩማን በሁለት ጎራ ተሰልፈው ሲያጎሳቁሏት አመታት ተቆጥሯል፡፡ በአንደኛው ጎራ የተሰለፈው የባንዳ ርዝራዥ ታሪኳን ወደ መቶ ዐመት ዝቅ ሲያደርገው እና አንዱ ብሔር ሌላውን ቀኝ ገዝቾል እያለ ሲተርት ታላቁን መጽሐፍ – መጽሐፍ ቅዱስን ለማስተማር በመጡ የአውሮፓ ወንጌላውያን ተኮትኩተው ያደጉት ደግሞ የአቢሲኒያ እምፓየር የሚል ሌላ ንድፈ ሀሳብ አዘጋጅትው ለብዙ ዓመታት ትውልዱን አወናበዱት፡፡ የተወናበደን ትውልድ መስመር የማስያዝ ከባድ ትግልን ይጠይቃል፡፡ የእቴጌ ጣይቱ ብጡል ሀውልት አዲስ አበባ ላይ የማይቆምበት ምክኒያት ምንድን ነው? ነፍጠኛ ናት ተብሎ ከሆነ ትልቅ ስህተት ነው፤ ከሰሜን በኩል የሚመጣው ኦሮሞ እንደ ምዕራቡ ኦሮሞ የደም ጥራት የለውም ካልተባለ በስተቀር ከእቴጌ ጣይቱ ብጡል በላይ ማንም ኦሮሞ ነኝ ሊል አይችልም፤ አዎ የአድዋዋ ጀግና እቴጌ ጣይቱ ብጡል ወርሸህ በመባል ከሚታወቀው የየጁ ባላባቶች የተገኘች፤ ከነወንድሟ እጅግ የላቀ ታሪክ ሰርታ ወደ የማይቀረው ዓለም ሔዳለች፡፡ ለጥቁር የሰው ዘር መኩርያ የሆነውን የአድዋ ድል አብሯት ለተሳተፈው ወንድሟ በዘመኑ የነበረው ሕዝብ እንዲህ በማለት ተቀኝቶበታል፡፡

“ወሌ ወሌ ቢሏችሁ

የወረባቦው እንዳይመስላችሁ

የእሳቱ ቁራጭ የጁ አለላችሁ”

ኢትዮጵያ በሁሉም ብሄረሰቦች ደም ተቦክታ፤ ተጋግራ እና ተማግራ የተሰራች የሁሉም ቤት ነች፤ ታሪክን በየፈርጁ አስቀምጠው ለፈራጁ ሕዝብ በትክክል ማቅረብ የተሳናቸውና ትውልድን በስሜት ማስጋለብ የቀለላቸው ፕሮፌሰሮች እና ተመራማሪዎች በዝተዋል፡፡ ትላንት የተዘራው የቅጥፈት እና ጥራዝ ነጠቅ ትንተና እንዲህ አይነት ውጤት ላይ አድርሶናል፤ ማን ነው የሚያስረዳኝ? በምን መመዘኛ ነው የእቴጌ ጣይቱ ሐውልት አዲስ አበባ የማይቆመው? ነፍጠኛ አጼ ሚኒልክን ስላገባች ነው ወይስ ኦሮሞነቷ ሚዛን የሚያነሳ ባለመሆኑ? ምናልባት ኦሮሞ ገዝቶ አይውቅም የሚለውን ባዶ ቅጥፊት ታጋልጣለች ተብሎ ተፈርቶ ነፍጠኛ ተብላ ይሆን? ወይስ ፊንፊኔን አዲስ አበባ በማለት ተወንጅላ ይሆን? የሚፈልጉትን ብቻ እየመረጡ የሚሰሙ ትውልዶች በበዙባት ኢትዮጵያ የእቴጌ ጣይቱ ብጡልን ሐውልት አይቆምም ማለት ለጊዜው ይቻል ይሆናል፡፡ አቧራው መሬት ይዞ መተያየት ሲጀመር ብዙዎች ማፈራቸው አይቀሬ ነው፡፡ ሀውልቱ እንዲቆም የተጠየቀው ሮም ላይ ቢሆንና እምቢ ቢባል ያስኬዳል፡፡ ጠላቱን በክብር የሚቀበል የለምና! የነጭ ዘር ለመጀመርያ ጊዜ በጥቁሮች ድል ሲሆን እቴጌ ጣይቱ ብጡል ከአዋጊዎቹ አንዷ ነበረች፡፡ በአደዋው ድል የተናደዱና የከፋቸው መሐል አገርም ውስጥ አሉ እንዴ? ኢትዮጵያኖቹ ለምን አይሆንም አሉ? የት ነው ያለነው? የሀገሬ ካህናት ከመጠምጠም መማር ይቅደም ይላሉ፡፡

      ናይሮቢ በስደት ላይ እያለሁ ቀለም ቀመስ የወለጋ ልጅ ጓደኛ ነበረኝ፡፡ በጋዜጠኝነቱ ችግር ስለበዛበት ተሰዶ ነው የተገናኘነው፤ በጣም ነበር የምንቀራረበው ጨዋታ ሲያልቅብን የመለስ ዜናዊን የጎሳ ቀመር እያነሳን መጣል የተለመደ ነበር፡፡ እንደምንም ብሎ የኦሮሞን በአቢሲኒያ ኢምፓየር መገዛት ሳያስገባ ውይይታችን ተቋዋጭቶ አያውቅም፡፡ እንዲህ አይነቱ በሬ ወለደ ዓይነት አቀራረብ እየተደጋገመ ሲመጣ እንደሚጎረብጠው እየገባኝ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ በክፉም በደጉም ሥልጣን ላይ የነበሩትን ኦሮሞዎች ከአጼ ፋሲል ጀምሮ እነ ትልቁ እና ትንሹ ራስ አሊ፤ ከየጁ የወረሸኮች የዘር ግንድ የወጣችውን እቴጌ ጣይቱ ብጡልን ወንድሟ ራስ ወሌ ብጡልን፤ የቀድሞው (የወረሂመኑው) ማመድ አሊ በኋዋላ ንጉስ ሚካኤል አሊ፤ ልጅ ኢያሱ  ሚካኤል፤ የንጉሱ ኃይለስላሴ ባለቤት እቴጌ መነን አስፋው አሊ ቦሩ፤ የሸዋው የጉዲሳ የልጅ ልጅ እና የወረኢሉዋ ወይዘሮ ልጅ የሆኑት ንጉስ ኃይለስላሴ ድረስ ሄድኩኝ፡፡ አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም እንደሚባለው፤ ይባስ ብሎ

“ወዴት ጠጋ ጠጋ

ጨለማው ሲነጋ”

ብሎኝ ተለያየን፡፡ ልብ በሉ ለዚያ ወንድሜ የጎሳው ትንተና ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ንጋት ነው፡፡ ያ ወንድሜ ባለፉት ሶስት ዓመታት የተከፈለውን የሕይወት ዋጋ አይቶታል ሰምቶታል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ምን እንደተሰማው ግን ማወቅ አይቻልም ፤ ጥላቻን እየቀፈቀፈ ትውልድን ለአደጋ የሚጋብዝ ባዶ ትንተና ስር ከመስደዱ የተነሳ የፀረ ኮሎኒያሊስት ትግሉ ግምባር ቀደም የሆነችውና አንፀባራቂ ታሬኳን ለትውልድ አስረክባ ያለፈችው የእቴጌ ጣይቱ ብጡል ሐውልት ለነፃነቷ በተጋደለችላት ሀገሯ ላይ እንዳይቆም የሚከላከል ትውልድ አፈራንና አረፍነው፡፡

ታሪክ ጨካኝ እና ብርቱ ነው፡፡ ለማንም ብሎ ቦታውን አይለቅም፤ በአንድም ወይም በሌላ የአደዋን ድል ማሳነስ ወይም በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ጥላሸት መቀባት ይቻል ይሆናል፡፡ አድዋ ላይ ጦርነት አልተካሔደም፤ ነጭ በጥቁር አልተሸነፈም ለማለት ግን ፈፅሞ አይቻልም፤ ምክንያቱም ታሪክ ለእንዲህ አይነቱ ውሸት ቦታ የለውም፡፡ ያ ማለት ግን ታርክን በነሱ ልክ ለመስፋት የሚፈልጉ እብዶች አይነሱም ማለት አይደለም፡፡ ለእንዲህ አይነቱ እብደት መለስ ዜናዊ እና ተከታዬቹ ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ እቴጌ ጣይቱ ብጡል የትውልድ ምስክር የሚሆን ሀውልት እንዳይቆምላት መከልከሉ ለታርክ ያለን ግንዛቤ መቀመቅ መውረዱን ከማሳየት በስተቀር እስከ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት ድረስ ማንም  የማያነቃንቀው ታሪክ ሰርታ አልፋለች፡፡ ዘመን እጇ ላይ የጣለላትን አጋጣሚ በትክክል ተጠቅማ በዓለም ዙርያ የተበተነው ጥቁር ዘር ቀጥ ብሎ እንዲሄድ ካደረጉት ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ግምባር ቀደሟ ናት፡፡

       የቀደሙት ዘመናት በአዲስ እንደተተኩ ሁሉ፤ ይህም ዘመን ጊዜውን ጠብቆ ያልፋል፡፡ የተፈለገውን ያህል አፄ ምኒልክን እቴጌ ጣይቱንና የአደዋን ጀግኖች መወንጀልና ስም ማጥፋት ይቻላል፡፡ የሰሩትን መልካም እና አስደናቂ ታሪክ ግን ከታሪክ ማህደር መፋቅ አይቻልም፡፡ የታሪኩ ወራሽ ትውልድ አድርጎ ራስን ለማየት አለመቻልም ርግማን ነው፡፡ የእቴጌ ጣይቱ ብጡል ሐውልት አዲስ አበባ ላይ መቆም የለበትም የሚል ትውልድ ከተነሳ፤ በክርስትናውም በእስልምናውም ያሉ የዕምነቱ ተጠሪዎች ለምዕመኑ ፆም እና ፀሎት ማዘዝ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ በእርግጥም አገሪቱ አደጋ ላይ ናት፡፡ እንዴት ነው በዘመኑ የነበረውን የዓለም ህዝብ ያስደመመ ታሪክ በአድዋ ላይ ያከናወነች ጀግና በገዛ ሀገሯ ላይ መታሰቢያ የምትከለከለው? ወዴት እየሄድን ነው? ሲከር እንዳይበጠስ!  

Filed in: Amharic