>

የኢትዮጵያ የከፍታ ዘመን!!! (መሳይ መኮንን)

የኢትዮጵያ የከፍታ ዘመን!!!
መሳይ መኮንን
ልዩ ነው። ያምራል። ከሰነበትንበት የመከፋት ዘመን እየወጣን ነው። መቃብር ውስጥ የቆየችው ኢትዮጵያ አፈሩን ገልጣ ከጨለማው ጊዜ ልትፋታ እየተንደረደረች ነው። ያ የውርደት ዘመን ሊሰናበተን ነው። መጨረሻውን ያሳምረው።
ደስ ይላል። ብዙ ቢቀርም ተስፋው ያጠግባል። የኢትዮጵያ ልጆች የስደት ዘመናቸው አብቅቶ ወደ ውድ ሀገራቸው እየተመሙ ነው። የእስራዔል ህዝብ የምጸአት ዘመን አብቅቶ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ወደ ሀገራቸው ያደረጉትን ”መመለስ” የሚያስታውስ ነው። ከየዓለማቱ የኢትዮጵያ ልጆች የእናት ሀገራቸውን ምድር ለመርገጥ ተነቃንቀዋል። ወገን እየተሰባሰበ ነው።
እነዓለም ጸሀይ ወዳጆ ከ25ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያን አፈር ረግጠዋል። ታማኝ በየነ ሲያለቅስላት ሲጮህላት የነበረች ሀገሩን ስሟል። ከአዲስ አበባ – ባህርዳር- ጎንደር – አዳማ ኢትዮጵያዊነት በታማኝ መድረኮች ነግሰው ከርመዋል። አዲስ አበባ በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላም ተጥለቅልቃለች። ድብቡ ልዩ ነው። አዲስ ዓመት አዲስ ተስፋ ሁለ ነገር አዲስ፡ ኢትዮጵያ! አዲስ አበባ የአርበኞች ግንቦት ሰባትን አመራሮችና አባላት ልትቀበል ሽርጉዷን ተያዛዋለች። ሰፈር መንደሩ፡ መንገድ ጎዳናው እዚህም እዚያም ዝግጅቱ እየተካሄደ ነው። ነገ ሙሽሮቹ ይገባሉ።
በፕ/ር ብርሃኑ ነጋና በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የሚመራው የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራር ዛሬ ምሽት ከአውሮፓ ይነሳል። በየሀገራቱ የሚገኙ የንቅናቄው አባላት ፍራንክፈርት ላይ እየተሰባሰቡ ነው። በዶ/ር አዚዝና አቶ ነአምን ዘለቀ የሚመራው የሰሜን አሜሪካው ቡድን ከደቂቃዎች በፊት ከዋሽንግተን ዲሲ ተነስቷል። ነገ ጠዋት በእኩል አዲስ አበባ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል። የኢሳቱ ጋዜጠኛ ደረጀ ሀብተወልድም ይህን ታሪካዊ ጉዞ ለመከታተል ከአውሮፓው ልዑክ ጋር አብሮ ይጓዛል።
ነገ እሁድ አዲስ አበባ ስታዲየም ጠጠር መጣያ የሚገኝ አይመስልም። የአርበኞች ግንባት ሰባት ንቅናቄ አመራሮች ከአዲስ አበባ ስታዲየም የሚያደርጉት ንግግርን በአካል ተገኝቶ ለመከታተል ከአቅራቢያ የአዲስ አበባ ከተሞች ህዝቡ እየጎረፈ ነው። በመስቀል አደባባይ ስክሪን የሚሰቀል በመሆኑ ከስታዲየም ውጭ ላለው ህዝብ የሚከታተልበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩም ተሰምቷል። አዲስ አበባን ተከትሎ ባህርዳር፡ ጎንደር ደሴ አዳማ እያለ በ32 ከተሞች የንቅናቄው አመራሮች ህዝባዊ ስብሰባ እንደሚያደርጉ ከወጣው መርሀ ግብር መረዳት ተችሏል።
ዛሬ በዋሽንግተን ዲሲ የነበረው አሸኛኘት ልዩ ነበር። የዲሲ የኢትዮጵያውያን ግብረሃይል አባላት አንድ ሆነ ቆይተው አንድ ላይ ወደ እናት ሀገራቸው ይገባሉ። እንግዲህ ምን ይባላል?! ለዚህ ቀን ላበቁንና ውድ ህይወታቸውን ለከፈሉ የኢትዮጵያ ልጆች ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ ይሁን ከማለት ውጪ ለምስጋና አቅም ያለው ቃል ለጊዜው አላገኘሁም። መልካ አዲስ አመት። መልካም መንገድ!
Filed in: Amharic