>
4:44 pm - Wednesday November 30, 2022

መቼ ይሆን?!? (አሰፋ ሀይሉ)

መቼ ይሆን?!?
አሰፋ ሀይሉ
በኢትዮጵያ ታሪክ ከሥልጣነ መንበራቸው በሰላም ለቀው በሰላም ከሕዝቡ ጋር መኖር የቻሉ ብቸኛው ሰው ምናልባት የኢህአዲግ ዘመኑ ርዕሰ-ብሔር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳና ሀይለማርያም ደሳለኝ ብቻ ሳይሆኑ አይቀሩም ብዬ አስባለሁ፡፡ በተረፈ ኢትዮጵየ በታሪኳ መሪዎቿ (በምስሉ የሚታዩት ሁሉ) አንዳቸው ለሌላኛቸው ምንም ግርግር ባልነፈሰበት የሠላም አየር በፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን አስተላልፈው የማያውቁባት ሃገር ናት – ኢትዮጵያ ሃገራችን፡፡
ከምስሉ ራሱ ብትጀምር አፄ ቴዎድሮስን ከሥልጣናቸው ለማስወገድ አፄ ዮሐንስ እንግሊዞችን መቅደላ ድረስ እየመሩ የአፄ ቴዎድሮስን ግብዓተ-መሬት ሲፈጸም ከተመለከቱ በኋላ በንጉሠ-ነገሥት ዙፋኑ ተቀመጡ፡፡
አፄ ምኒልክ ደግሞ ከኢጣልያኖች፤ ከእንግሊዞች፤ ከፈረንሣዮች የጦር መሣሪያ እየገዙ ግዛታቸውን እያስፋፉ ካፄ ዮሐንስ የሚገላገሉበትን ጡንቻቸውን እያጠናከሩ በሩቅ ሆነው ሲጠባበቁ ቆይተው አፄ ዮሐንስ ብቻቸውን ወደመተማ ዘምተው ግብዓተ-መሬታቸው ሲፈጸም ከተመለከቱ በኋላ በንጉሠ-ነገሥት ዙፋኑ ተቀመጡ፡፡
ንግሥተ-ነገሥታት ዘውዲቱ አጤ ምኒልክን በቀረቻቸው ዕድሜ በሽታቸውን ከሕዝብ ሰውረው በቤተመንግስት ከእቴጌ ጣይቱና ከሌሎች ታማኝ ባለሟሎቻቸው ጋር ሲያስታምሙ ከቆዩ እና ከሞቱም በኋላ በምኒልክ ስም በዙፋኑ ተቀምጠው ከቆዩ በኋላ ምኒልክ ዙፋኔ ላይ ይቀመጥበት ያሉትን አቤቶ ልጅ እያሱን ከሌሎች ጋር ተባብረው እስርቤት በመጨመር በመጨረሻ ንግሥተ-ነገሥታት ዘውዲቱ ተብለው ዙፋኑ ላይ ተቀመጡ፡፡
ራስ ተፈሪ ደግሞ አልጋወራሽ ተብለው ከዘውዲቱ ዙፋን ሥር በትዕግስት ሲያደቡና በህቡዕ ሲያሳድሙ ቆይተው በመጨረሻ ንግሥተ-ነገሥታት ዘውዲቱን ወደገዳም አፈናቅለው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በሚል የንግሥና ስም በንጉሠ-ነገሥቱ ዙፋን ላይ ተቀመጡ፡፡
ሻለቃ (ኋላ ሌ/ኮሎኔል) መንግሥቱ ኃይለማርያም በበኩሉ በንጉሡ አሜሪካን ሃገር ተልኮ ወታደራዊ ሳይንስ እና መፈንቅለ-መንግሥት አጥንቶ ከተመለሰ በኋላ የበታች መኮንኖችን አሳድሞና አስተባብሮ ደርግ በሚባል የወታደሮች ኮሚቴ ንጉሡንና ቤተዘመዶቻቸውን ካስረሸነ በኋላ እያደባ ብቸኛ የደርግ ሊቀመንበር ሆኖ ያገሪቱ ርዕሰ,-ብሔር፤ መራሔ-መንግስት እና የጠቅላይ አዛዥነቱን ሥልጣነ-መንግስት ተረከበ፡፡
አቶ መለስ ዜናዊ ደግሞ በደርግ ማግስት ወደሰሜኑ ትውልድ ሃገራቸው በማምራት ከጥቂት ጓዶቻቸው ጋር በመሆን ከኢትዮጵያ ተገንጥለው ነፃነታቸውን ለማግኘት ከደርግ ጋር ትንቅንቅ የገጠመውን የኤርትራ ሐርነት ሕዝባዊ ግምባር በህወሐት ስም ተቀላቅለው ለዓመታት ደርግን ሲዋጉ ቆይተው በመጨረሻ ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያምን ወደ ዚምባቡዌ ሐራሬ አስኮብልለው የመንግስቱን መንበር በፕሬዚዳንትነት እና ቀጥሎም በጠ/ሚኒስትርነት ተረከቡ፡፡  እስከ እለት ሞታቸው ድረስ  ሀገሪቱ እና ህዝቡ ላይ መከራ ሲያዘንቡበት ኖረው ለአንዲትም ቅጽበት የጥፋተኝነት እና የጸጸት ስሜት ሳይሰማቸው በዛው የጥፋት መንገዳቸው እንደነጎዱ ሀገርን የማፈራረስ ህዝብን የመለያየት ፋሽስታዊ ቀመራቸውን የሚቀምሩበር ጭንቅላታቸው በካንሰር ተጠቅቶ ለሞት ተዳረጉ።
በእግራቸው የተተኩት አቶ ሀይለማርያም አንድም ቀን የመሪነት ቅርጽና ይዘት ሳይኖራቸው በአማካሪ ስም በስራቸው በተኮለኮሉ የህወሀት ሰዎች ሲነዱ ኖረው በአገሪቱ የተቀጣጠለው ህዝባዊ አመጽ እርሳቸውንም ነጻ አውጥቷቸው የነጻነት አየር እየተነፈሱ ይገኛሉ።
አንጻራዊ በሆነ መልኩ ሰላማዊ ሽግግር ሊባል በሚያስደፍር ሁኔታ መንበረ መንግስቱን የተረከቡት ዶ/ር አብይ በአጭር ጊዜ በሰሯቸው በርካት ስራዎች በህብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን ያገኙ ይመስላል ፍጻሜውን አብረን የምናየው ይሆናል።
የደላቸውን የአሜሪካ መሪዎችን ደግሞ ተመልከቷቸው፡፡ 
በቀኝ በኩል መጨረሻ ላይ ጂሚ ካርተር አሉ፡፡ 39ኛው ያሜሪካ መሪ ናቸው፡፡ ለአራት ዓመት በስልጣን ሰንብተው በሰላም ተሰናበቱ፡፡
ቀጥሎ በግራ በኩል የመጀመሪያው ትልቁ ጆርጅ ኸርበርት ቡሽ ብዙ ዓመት በምክትል ፕሬዚዳንትነት ቆዩ፡፡ ኋላ ግን በፕሬዚደንትነት ሬገንን ተክተው ለአራት አመት ብቻ ቆዩ፡፡ ከዚያ ደህና ሰንብቱ ብለው አዲዮስ፡፡
ደግሞ ከጂሚ ካርተር ጎን የቆሙትን ቢል ክሊንተንን ተመልከታቸው፡፡ እንደርሳቸው ህዝቡን ያነቃነቀ ተወዳጅም አነጋጋሪም መሪ የለም ይባልላቸዋል፡፡ ስምንት አመት ቆዩ፡፡ ከዚያ ደህና ሰንብች ስልጣን ብለው የሰላም ኑሯቸውን፡፡
ትንሹን ቡሽ (ማለትም የጆርጅ ቡሽን ልጅ) ደግሞ እያቸው፡፡ ተወዳጅ መሪ አልነበሩም፡፡ ሆኖም በጦርነት ወቅት 43ኛው ያገሪቱ መሪ ሆነው በህዝቡ ፈቃድ መርተዋል፡፡ አሁን ተሰናብተው የራሳቸውን ቢዝነስ ያጧጡፋሉ፡፡
ደግሞ ባራክ ኦባማን ውሰዳቸው፡፡ እርሳቸውም የሚገርሙና ምናልባትም በአሜሪካ ታሪክ እና በዓለምም ታሪክ እንደ እርሳቸው ያለ ምሉዕና በህዝብ ተወዳጅ መሪ አይገኝ ይሆናል፡፡  ደሞ ወጣትም ናቸው፡፡ ግን ሁለቴ ተመረጡ፡፡ ስምንት አመት ሃገሪቱን መሩ፡፡ ከዚያ አሁን ደህና ሰንብች ዋይት ሃውስ ብለው ካሻቸው 24 ሠዓት ሙሉ የስኖው ዋይትን ተረት እያነበቡ ቀሪ ህይወታቸውን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ጠቃሚ ህይወትን እየመሩ ማሳለፋቸውን ይቀጥላሉ፡፡
በቃ አሜሪካኖችን ስታይ.. አለ አይደል.. በተለይ ኢትዮጵያዊ ሆነህ አሜሪካውያኑን መሪዎች ስታይ.. በቃ.. አንጀትህ ስፍ..ስፍ..ስፍ..ስፍ…… ይልብሃል፡፡
በበኩሌ በዕድሜዬ የሽግግር መንግስቱን ጨምሮ ሶስት መንግስታትን አሳልፌያለሁ!! በመጨረሻ ግን እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ በዕድሜዬ ፍፁም የምመኘው ነገር ቢኖር… (ደግሞም የሆነ ኦፕቲሚስቲክም ሆኜ ተስፋ የማደርገው ነገር ቢኖር).. እኛም እንደአሜሪካኖች.. መሪዎቻችንን በነፃነት የምንመርጥበትን ቀን እና.. በቃ ልክ በምስሉ እንደሚታዩት አሜሪካኖች.. ከሥልጣን መንበራቸው በሰላም አንዱ ለሌላኛቸው እየለቀቁ.. እነርሱ በምታካቸው ከዚህች ምድር የበቀሉ በአባቶቻቸውና በእናቶቻቸው ከሚኮሩ ልጆቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ጋር.. በሰውም ዘንድ ተከብረው… የሚያማክሩት ነገር ቢኖር ለቁምነገር ቤተመንግስት እየተጠሩ.. የግል ህይወታቸውን በሰላም የሚኖሩበት.. ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የሚኖርበት ቀን ይናፍቀኛል፡፡
ለእኔ ጠብ የሚልልኝ አንድም ጉርሻ ባይኖርም.. ግን.. እንዲያው በህይወት ዘመኔ… ለአንዲት ቀን እንኳ እንደአሜሪካኖቹ ብዙ ተከታታይ መሪዎች ቢቀርብን.. እንዲያው ቢያንስ ሶስት ተከታታይ መሪዎች አንድ ላይ ሆነው.. በቤተመንግስት ራት ሲገባበዙ.. ባይ እና ከዚያ በኋላ ብሞት እንደአንድ ኢትዮጵያዊ አይቆጨኝም ነበር፡፡ ያ በሃገራችን መቼ እንደሚመጣ አንድዬ ብቻ ይወቀው፡፡
በእኛ ዘመን የሆነ ፍንጭ ያለ ይመስለኛል፡፡ የሆነ ተስፋን ያዘለ ጭላንጨል፡፡ ምናልባት በኛ ዘመን ካልሆነ በልጆቻችን ዘመን ይኖር ይሆን…?? ፈጣሪ አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ፡፡ ወዳጆቻችንን አሜሪካኖችንም ጭምር፡፡ መልካም ጊዜ ለሁላችን፡፡
Filed in: Amharic