>

"ራሱን በጭብጨባ ያሳበጠ ሰው ጭብጨባው ሲቆም ይተነፍሳል!!!”  (ፋሲል የኔአለም)

“ራሱን በጭብጨባ ያሳበጠ ሰው ጭብጨባው ሲቆም ይተነፍሳል!!!” 
ፋሲል የኔአለም
የልደቱ አጀንዳ የሚነሳው ግለሰቡ በአማራነቱ እንደተጠቃ እንዲሁም በጉራጌና በአማራ  መካከል ፀብ  እንዳለ አድርጎ በማቅረብ ፣ ርካሽ ፖለቲካ ለመስራት ታስቦ  ነው
ሚዲያዎች ብርሃኑንና ልደቱን አቅርበው እንዲያነጋግሩ ዘመቻ ተከፍቶባቸዋል። ለቅንጅ መፍረስ የብርሃኑንና የልደቱን “ጸብ” ምክንያት አድርገው የሚያስቡ ሰዎች፣ በምርጫ97 ወቅት ለአቅመ-ፖለቲካ ያልደረሱ ወይም ድርጅቱን በቅርበት የማያውቁ ሰዎች እንደሆኑ ይሰማኛል።  ልደቱ ከቅንጅት ለምን እንደለቀቀ ማወቅ የሚፈልግ ሰው መጀመሪያ መጠየቅ ያለበት ብርሃኑን ሳይሆን የኢዴፓ አመራሮችን ነው። በተለይም አቶ አንዱዓለም አራጌ፣ ዶ/ር ሃይሉ አርዓያ፣ አቶ ታምራት ታረቀኝና ሌሎችንም። በሁለተኛ ደረጃ መጠየቅ ያለበት ደግሞ መኢአድ ነው። የመኢአድ መሪዎች ከልደቱ ኢዴፓ ጋር መቀናጀት ቀርቶ መነጋገር እንኳን አይፈልጉም ነበር። ኢ/ር ሃይሉ በህይወት ባይኖሩም ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁትን አቶ ማሙሸትንና ሌሎች አመራሮችን ማነጋገር ይጠቅማል። ዶ/ር ብርሃኑ መጠየቅ ካለበት በሶስተኛ ደረጃ ነው።
 97 ዓም ላይ ልደቱን “ከብርሃኑ ጋር ያላችሁ ችግር ምንድነው?” ስል ጠይቄው ነበር፤ ካስታወሰው ሁለታችን ብቻ  ሂልተን ሆቴል ቁጭ ብለን በዚህና በሌሎችም ጉዳዮች አውርተናል። ብርሃኑንም ተመሳሳይ ጥያቄ ጠይቄው ነበር። ሁለቱም ምንም ችግር እንደሌለባቸው ነግረውኛል። “ታዲያ ችግር ከሌለባችሁ ለምን ሁለታችሁንም  አላናግራችሁም?” ስላቸው “ይቻላል” ብለው፣ ሁለቱም በወቅቱ በአዲስ ዜና ጋዜጣ “ የአሉባልታ ሰለባዎች” በሚል ርዕስ  የወጣውን ቃለምልልስ ሰጥተዋል።  ልደቱ በዶ/ር ብርሃኑ ላይ የነበረው ቅሬታ እየጨመረ የመጣው ወ/ት ብርቱካን ተቀዳሚ ም/ሊ/መንበር ሆና ከተመረጠች በሁዋላ ነው። ልደቱ “ እኔ እንዳልመረጥና ብርቱካን እንድትመረጥ ያደረገው ብርሃኑ ነው” የሚል ቅሬታ ነበረው።  ብርሃኑ ልደቱ ምክትል ሆኖ እንዳይመረጥ ፍላጎት ነበረው ቢባል እንኳ መኢአድ፣ ኢዴፓና ኢድሊ የሚባሉት ድርጅቶች ድጋፋቸውን ካልሰጡ በስተቀር፣   ብርሃኑ ብቻውን ልደቱ እንዳይመረጥ ማድረግ እንደማይችል ልደቱ የተረዳው አይመስለኝም። መኢአድ፣ ኢዴፓና ኢድሊ የልደቱን አቋም በማየት፣ አይደለም ምክትል አድርገው ሊመርጡት ቀርቶ፣ ከእሱ ጋር አብረው በአንድ ድርጅት ውስጥ ታቅፈው ለመቀጠልም ፍላጎት የነበራቸው አይመስለኝም።
በምርጫው ማግስት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በብዛት የሚገኘው ልደቱ ነበር። ልደቱ በተደጋጋሚ የሚሰጣቸው በሃይለቃል የተሞሉ መግለጫዎች ለሌሎች የቅንጅት አመራሮች የሚጥም አልነበረም። “ፓርላማ እንግባ አንግባ” በሚባልበት ወቅት ልደቱ መጀመሪያ የያዘውን አቋም እያለሳለሰ ከመጣ በሁዋላ፣ “ፓርላማ እንግባ” የሚል አቋም መያዙ ሲሰማ ብዙዎች ልደቱን በከሃዲነት መክሰስ ጀመሩ። ልደቱ አቋሙን የቀየረው  ከዶ/ር ብርሃኑ ጋር ስለተጣላ ነው የሚል የዋህ ሰው ስለማይጠፋ ከእንዲህ አይነቱ ሰው ጋር ሙግት አልገጥምም።  ልደቱ ከቅንጅ መንገድ ሲወጣ፣ 3ኛ መንገድ የሚል አምጥቶ መሃል ሰፋሪነትን መረጠ። የቅንጅት መሪዎች ታስረው በነበረበት ወቅት መለስ  ሶማሊያን ሲወር ልደቱ ደገፈው።  አንዳንዴ ከመለስ በላይ መለስ እየሆነ ስለ ኢኮኖሚው እድገት ማብራሪያ ሰጪ ሆነ፤ እነ ዶ/ር መረራ እስኪያቅለሸልሻቸው ድረስ ፓርላማ ውስጥ ተቃዋሚዎችን ይጨረግዳቸው ጀመር። ህዝቡም ልቡ ይበልጥ ተሰበረ። ልደቱ ሶስተኛ አማራጭ አምጥቶ ፓርላማ ሲገባ፣ ብርሃኑ እስር ቤት ነበር፤ ታዲያ ብርሃኑ ነበር 3ኛ መንገድ ብለህ መሃል ላይ ስፈር ያለው?
ጊዜና ቦታው ስላልሆነ እንጅ የማውቀውን ብዙ መጻፍ እችላለሁ። በአጭሩ ግን በእኔ እምነት ልደቱ የወደቀው በሁለት ዋና  ምክንያቶች ነው። አንደኛው የህዝቡን ድጋፍ በተሳሳተ መንገድ መረዳቱ ነው። ብዙ መሪዎችን የሚጥላቸው ጭብጨባ ነው፤ ልደቱም ጭብጨባውን እንደ ጭፍን ድጋፍ ወስዶ የፈለገውን ማድረግ እንደሚችል እንዲሰማው አደረገ። ታበዬ። የቅንጅት ድል በእሱ ንግግር ብቻ እንደተገኘ ቆጥሮ፣ ከቅንጅት ቢወጣ ህዝቡ እሱን መሪ አድርጎ እንደሚከተለው በማሰቡ ለስህተት ተዳረገ። ልደቱ በሚያዚያ 30 ው ሰልፍ መኪና ላይ ወጥቶ እጁን እያወዛወዘ ሰላምታ ሲሰጥ ብዙዎች አካሄዱ አስፈርቷቸው ነበር። በዚያ ድርጊት ያልተሸማቀቀ ሰው አልነበረም። ልደቱ ቅንጅት ከመግባቱ በፊት በነበሩት ምርጫዎች ተሳትፎ ውጤት አለማምጣቱን ሊያስታውሰው አይፈልግም። በወቅቱ ህዝቡ ለቅንጅት ድጋፉን የገለጸው በኢህአዴግ ስለተማረረ፣ ፓርቲዎች ተጣምረው ስላያቸው እና ምሁራን ወደ ፖለቲካው ስለገቡ እንጅ ልደቱ ስላደራጃቸው ወይም ስለቀሰቀሳቸው እንዳልነበር ማስታወስ ያስፈልጋል። ልደቱ ቅንጅት አሸናፊ ሆኖ እንዲወጣ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፤ ብቸኛ ሚና ተጫውቷል ሊባል ግን አይችልም።
  ከልደቱ በሁዋላም ብዙ የተቃዋሚ መሪዎች ጭብጨባ አልችል ብለው እንደጠዋት ጤዛ ወዲያው ታይተው ረግፈዋል። ልደቱን የገደለው ጭብጨባ ነው። ወይም ጭብጨባውን በአግባቡ አለመያዙ ነው። የሆነ ጸሃፊ “ማንነቱን በጭብጨባ የገነባ ሰው ጭብጨባው ሲቆም ይተነፍሳል” ማለቱን አንብቤአለሁ። ትክልል ይመስለኛል።
ልደቱን ለኪራሳ የዳረገው ሌላው ምክንያት ደግሞ በሮኬት ፍጥነት የአቋም ለውጥ ማድረጉ ነው። በምርጫው ማግስት  ልደቱ ጠንካራ ቃላትን እየተጠቀመ ህዝቡ ኢህአዴግን በተቃውሞ እንዲጥለው ይቀሰቅስ ነበር። አብዛኞቹ የቅንጅት መሪዎች አንዲህ አይነቱን ቅስቀሳ የሚደግፉ አልነበሩም። በዚህ አቋሙም ልደቱ እንደጀግና የእሱን ቅስቀሳ ያልተቀበሉት ደግሞ እንደፈሪ ተደርገው ይቆጠሩ ነበር።  በዚህ አቋሙ ልደቱ ብዙ ደጋፊዎችን አፍርቶ ነበር ነገር ግን ተከታዮችን ሳያምክር  እጥፍ አለና ፓርላማ እንግባ የሚል ቅስቀሳ ጀመረ። ይህም ክፋት አልነበረውም፤  3ኛ አማራጭ ብሎ መጣና ከኢህአዴግ በላይ የኢህአዴግ አፍ ሁኖ ሲያርፈው የ ህዝቡ ልብ ተሰበረ።
ልደቱን ብርሃኑ አልገደለውም፤ ሚዲያውም አልገደለውም። ልደቱን የገደለው ራሱ ልደቱ ነው። ብርሃኑንና ልደቱን ቁጭ አድርጎ በማናገር የሚወጣ ሃቅ ይኖራል ብዬ አላምንም። ወጣት ፖለቲከኞች ከልደቱ መማር ካለባቸው፣  መማር ያለባቸው ጭብጨባን መጥላትና በአቋም መጽናትን ነው። አቋማቸውን ሲቀይሩ ደግሞ በጥበብና ህዝብን በማግባባት እንጅ በጭብጨባ በተገኘ ማን አለብኝነት መሆን የለበትም የሚለውን ቢማሩ ጥሩ ነው።
የልደቱ አጀንዳ የሚነሳው ግለሰቡ በአማራነቱ እንደተጠቃ እንዲሁም በጉራጌና በአማራ  መካከል ፀብ  እንዳለ አድርጎ በማቅረብ ፣ ርካሽ ፖለቲካ ለመስራት ታስቦ  ነው። እነዚህ ሰዎች የማይገባቸው ግን  ልደቱ ከመላው አማራ ድርጅት  ወጥቶ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ፓርቲን የመሰረተው በብሄር መደራጀትን ጠልቶ ነው። መአዶችም ሆኑ መኢአዶች ልደቱን የሚጠሉበት ምክንያት ይኸው ነው። ልደቱ ወያኔ ነው የሚለው ክስ በመጀመሪያ የመጣው ከመአህድ ( መኢአድ) ሰዎች ነው። ፕ/ር አስራት ከመሰረቱት መአህድ በላይ ለአማራ መብት ስታገል ነበር የሚል የብሄር ድርጅት ካለ እጁን ያውጣ!  ልደቱ በአላማና አስተሳሰብ ወደ ፖለቲካው ተመልሶ  እድሉን ቢሞክር ችግር የለውም፤ መሞከረም አለበት። ነገር ግን ብሄርን አስታኮ ለመግባት የሚደረገው ሙከራ የሁዋላ ሁዋላ በራሱ ላይ ብዙ ችግሮችን ይዞበት ይመጣልና ቢታሰብበት ጥሩ ይመስለኛል።  ልደቱን የተቃወሙት መኢአዶችና በርካታ የኢዴፓ አባላት አማራዎች መሆናቸውን መርሳት አይገባም።
Filed in: Amharic