>
3:05 am - Friday February 3, 2023

ኢትዮጵያ ትቅደም (ሙክታሮቪች ኡስማኖቭ)

ኢትዮጵያ ትቅደም
ሙክታሮቪች ኡስማኖቭ
ኢትዮጵያ ትቅደም 1
(በዚህ አርዕስት ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ክርር ያለና ፅንፈኛ አቋሞችን እናንፀባርቃለን)
 
እህዕ! ኢትዮጵያዊነት በእራሱ እግር ቀጥ ብሎ የሚቆም እውነት ነው ብለን ተኮፈስን እንጂ ብናስጮኸው ጎሰኞችን አይደለም የቀድሞ ኮሎኒያልስቶችን ያስበረግጋል። አፍሪካዊና የካሪብያን ወንድሞቻችንን ያነቃቃል። ጥቁር አሜሪካውያንን ከየለቱ ሞት ይታደጋል ሆኖም አሁን ይህ ሀቅ ከእንቅልፉ ቀስቅሰን በጎሰኞች ላይ ጃስ እንለውና ትሩፋቱ ለሌሎች ይደርስ ዘንድ እንፅፋለን! ከኢትዮጵያዊነት ጋር ወደፊት! ኢትዮጵያ ትቅደም!
ኢትዮጵያትቅደም 2
በአስቾካይ የኢትዮጵያ መንግስት በህዝብ ቆጠራ የማንነት ጥያቄዎች ተርታ “ኢትዮጵያዊ” ማንነትን እንደ አንድ አማራጭ ማስቀመጥ አለበት። ከጎሳ ይልቅ ኢትዮጵያዊ ማንነት ነው የሚገልፀኝ የሚል ህዝብ መጠኑ በስርአቱ ሊታወቅ ይገባል። እንደ ካናዳ ያሉ ሀገሮች ይህን አማራጭ አስገብተው ፖለቲካቸውን ከመካረር ታድገውታል። እኛም ልናስገባው የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ ደርሰናል! ኢትዮጵያዊ ማንነታችን በይፋ፣ በቁጥርና በሳይንሳዊ ዳታ ይታወቅልን!
 ከዚያ የፖለቲካ ትግሉን ሀገርን በማዳን ብቻም ሳይሆን በጎሰኞች ሴራ ከመጠለፍ እራሳችንን ለመከላከል እንጠቀምበታለን! ምን ያህሉ የተማረና የነቃ በዚህ ኢትዮጵያዊ ማንነት ጥላ ስር እንደ አንድ  የማንነት ስብስብ እንደሚኖር፣ በአራቱም የሀገሪቱ ዙርያ፣ በሁሉም ሌሎች ንዑስ ማንነቶች (ሀይማኖት፣ ቋንቋ ወዘተ) ተበታትኖ እንዳለ በሚገባ ማወቅ ያስችለናል! ኢትዮጵያዊ ማንነት አሁኑኑ! #ኢትዮጵያትቅደም #ጎሰኝነትይክሰም
ኢትዮጵያትቅደም 3
እኛ ኢትዮጵያን ብለን ሙጭጭ የምንል በዜግነት አንድነት በፅናት በማመን ለሀገራችን እድገት የበኩላችንን ለማበርከት የምንፈልግ ሀይሎች፣ ጎሰኞችን የምንለማመጥበት ጊዜ ማብቃት አለበት! የጎሳ ልዩነት መሰረት ላይ የሚቆም ፖለቲካ መጀመሪያ የሚያጠቃው እኛን ስለሆነ እራሳችንን መከላከል አለብን! #ኢትዮጵያዊነትወይምሞት
ኢትዮጵያትቅደም 4
ሂድና የጎሳህን ጀግና ፈላልግ! ቴዎድሮስ፣ ዮሃንስ፣ ሚኒልክ! አርበኞችና ሀገርን ያቆሙ ባለምርጥ ጭንቅላት የሀገር ባለውለታዎች ሁሉ ማንነታቸው “ኢትዮጵያዊ” ነው! ለጎሳህ ብሎ የተሰዋ አንድም ጀግና የለም! አባቶች ማንነታቸውን ለልጆች ያስተላልፋሉ እንጂ፣ እንቡር እንቡር የሚሉ የነገ ጨቋኝ ጨረንቋዎች ለአባቶች ማንነትን አይሰጡም! ኮሮኮንች አስተሳሰብ ነው! ጅረት ወደታች ይወርዳል እንጂ ሽቅብ አይፈስም! ከጀግኖቻችን ላይ እጃችሁን አንሱ! – ኢትዮጵያዊማንነት አሁኑኑ!!!
ኢትዮጵያትቅደም 5
አስር ጊዜ አንሸወድም! ኢትዮጵያዊነት የሀገር ሉኣላዊነት ሲደፈር ብቻ ከጣልከው ቦታ ትዝ እያለህ ወላውለህ ወኔ መቀስቀሻ የምታደርገው “ባጣ ቆየኝህ” ሆኖ በፍፁም አይቀጥልም! የፖለቲካ የትግል ንቅናቄ ሆኖ ከች ይላል! በዚህ አጋጣሚ የንቅናቄውን ስም ለመቅረፅ አስፈላጊ በመሆኑ በኮሜንት መስጫ ሳጥን ውስጥ የበኩላችሁን ጥቆማ አስቀምጡ! ኢትዮጵያዊነት ከመከላከል ወደ ማጥቃት መሸጋገር ያለበት ጊዜ አሁን ነው!!!
ኢትዮጵያትቅደም 6
የኢትዮጵያዊ ማንነት መሰረቱ ከፍ ሲል ሰው መሆን ዝቅ ሲል ኢትዮጵያዊ ዜግነት ነው! ሰዉ የሚባለዉ ነፃነትን የተቀዳጀ ሰዉ ነዉ። ነፃ የሆነ ሰዉ ደግሞ በእራሱ ላይ ከባድ ሀላፊነትና ሸክም አለበት። ትልቅ ሸክም የሆነዉን የማሰብ ዕዳ ተሸክሞ እስከ አለተ ሞቱ ይዞራል። ነፃ ሰዉ ስለሚናገረዉ፣ ስለሚለብሰዉ፣ ስለሚጠጣዉ፣ ስለሚፅፈዉ ስለሚያነበዉና ስለሚሰማዉ፣ ስለሚዉልበትና ስለሚያድርበት፣ … ወዘተረፈ በእራሱ ያስባል፤ በእራሱ ይፈፅማል። ዉሳኔዉ የሚያስከትልበትን ዉጤት በእራሱ ይቀበላል። የሀገራችንን ፖለቲካ እየቀማን ያለውን ሰው የመሆን ክብራችንን ማስመለሻ አንዱና ወሳኝ እስትራቴጂ ቀድመን ኢትዮጵያዊ ማንነታችንን ማስመለስና በህግ መትከል ነው!!
ኢትዮጵያትቅደም 7
ኢትዮጵያዊማንነት ሞግተን የማናንበረክከው አካል የለም!!!
አሳፋ ጫቦ ይህን አጋጣሚ ሲገልፅ የኢትዮጵያዊ ማንነትን ክብርና ሰው የመሆን ቁመና ያፀናልናል!
« ፖውል ሔንዝ ሥራው ዋሽንግተን ዲ.ሲ Rand Corporation የሚባለው ግዙፍ የስለላ ማቀነባበሪያ ኩባኒያ ውስጥ ነበር። ምሳ ሊጋብዘኝ እምድር ቤት ይዞኝ ወርዶ የጠየቀኝ የመጀመሪያ ጥያቄ “ከየተኛው ጎሳ (Tribe) ነህ?” የሚል ነበር። ገርሞኝ “አልገባኝም!” አልኩት። “እንደምታውቀው ኢትዮጵያ ሁሉም ጎሳ አለው! …” ሲለኝ “ያንተስ?” አልኩት “እኔማ አሜሪካዊ ነኝ! አለኝ “እኔም ኢትዮጵያዊ ነኝ!” አልኩትና ምሳዬንም ሳልበላ ተለያየን።»
አሰፋ ጫቦ 
(ጋሞነቴና ኢትዮጵያዊነቴ አንዴም ተጋጭተውብኝ ላስታርቃቸው ቁጭ ብዬ አላውቅም) ይህን አቋም ጎሰኞች ስላላከበሩለት በስደት ሲንጨረጨር ሞተ!! እኛም በጎሰኞች እንሰደድ? ስራ እንጣ? ሀገራችንን ለማገልገል በጎሳ ካባ መሸፈን አለብን? የሚናገርልን ጎሳ እስኪመጣ ስንቴ እንታሰር? ኢትዮጵያዊማንነታችንን ስጡን? በሱ ጥላስር ተደራጅተን እንታገላለን!! በጎሰኞች ሰበብ በሰለጠነው አለም ሃላቀር እየተባልን ማፈራችንን አሁኑኑ ማስቆም አለብን!ኢትዮጵያዊማንነታችንን አሁኑኑ!!!
ኢትዮጵያትቅደም 8
አዎ ለኢትዮጵያዊማንነት አስጊና ለራሱ እወክለዋለሁ ለሚለውም ጎሳ የማይጠቅመውን ጎሰኝነት በምክንያት እየሞገትን ልኩን ማሳየት የትግላችን አንዱ ስልት ነው!!! በዚህ መሰረት
ጠባብ ጎሰኛ ስትሆን
         ★ ሀይማኖት የለህም – የቱም ሀይማኖት የሰው ልጅን እኩልነት ነውና የሚሰብከው ።
         ★ እውቀት የለህም – እውቀት ማለት ሚዛናዊ አስተሳሰብ ነውና ።
         ★ በራስህ አትተማመንም – በራስ መተማመን የጭፍንነት ፀበል ነውና ።
         ★ ፈሪ ነህ – ብቻህን ብትቆም ሙሉነት ስለማይሰማህ ቢጤዎችህን ትሰበስባለህ ።
         ★ እንደ ጋሪ ፈረስ ነህ – ዙሪያህን አታይም ። ስለዚህ ዓለምህ ጠባብ ናት ።
         ★ ሀገር የለህም –ከሀገርህ ፍቅር ላይ ቀንሰህ ነው ለጎሳህ የምትሰጠው።ጎሳህ ደግሞ ሀገር አይደለም።
         ★ ፍልስፍና የለህም – ፍልስፍና ከሚጠላቸው ጉዳዮች አንዱ መጥበብና መሰረታዊ ከሆነው እውነት በእውቀት ሳይሆን በስሜት መቃረን ነው ።
ዋሸሁ!? ከኢትዮጵያዊነት ማንነት ጋር ወደ ፊት!
ኢትዮጵያትቅደም 9
ግልፅ እናድርገው!
ኢትዮጵያ እንደሃገር ትቅደም ማለት ብሄርብሄረሰቦች ወደኋላ ይቅሩ ማለት እንዳይመስልህ/ሽ (:የኢትዮጵያ ማንነት ዥንጉርጉርነት እስከሆነ ድረስ ሁሉንም አቅፋ ወደፊት እንድትንቀሳቀስ ማድረግ ነው ዋናው ቁም ነገር፡፡ ኢትዮጵያ ከቀደመች አንድም ወገን ከሗላ አይከተልም፡፡ አንድ አካሏ ወደሗላ ከቀረ ያው አልቀደመችም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያን ካላስቀደምን ሁላችንም ኃላ ቀሪዎችና በቆሙበት ረጋጮች ነን፡፡ ጎሰኞች የነሱ ብቻ እንዲቀድም ሲታገሉ እኛ ደግሞ በአንድነት ሁላችንም እንደ ሀገር አብረን እንቅደም ነው የምንለው። ገቢቶ? ኢትዮጵያ ትቅደም! ትግሉ ይፋፋም!
ኢትዮጵያትቅደም 10 
ኢትዮጵያ “የዛሬ” ብቻ ሀገር አይደለችም። ኢትዮጵያ “የዛሬይቱ” በሚል ቅኝት ውስጥ የምትወድቅ ሀገር አይደለችም፡፡ “የዛሬይቱ” በሚል ቅኝት ውስጥ ወድቃ፣ ዛሬ በተሰጣት መስፈርትና ልክ ብቻ እንድትኖር ብትገደድ የማይተኛ፣ የማይሞት፣ የማያንቀላፋ፣ ወድቆ የማይቀር፣ አያቶቻችን የሰሩት፣ በየጊዜው ጎናችንን እየቆሰቆሰ የሚያስነሳ በርካታ ታሪክ ያለን ህዝቦች ነን፡፡ ኢትዮጵያዊነት በየዘመናቱ  ለጊዜው ያዘቀዘቀ ቢመስልም ሁሌም እራሱን ከጥቃት ለመከላከል እንደቆሰለ አውሬ ደመነፍሳዊ ማንነቱን ያሳያል። ከፍ እያለ፣ ይበልጥ እያበበና እየለመለመ  ይሄዳል! ወገን! በዚህ ሀሳብና የሚያንፀባርቅ ማንነት ስር የሚያሸንፍ እንጂ የሚሸነፍ አካል የለም!!
ኢትዮጵያ ትቅደም
Filed in: Amharic