>
5:13 pm - Friday April 18, 4279

የባንዲራ አምባጓሮ ከአርማው ወደ መደቡ ሲሻገር!!! (ሞሀመድ እንድሪስ)

የባንዲራ አምባጓሮ ከአርማው ወደ መደቡ ሲሻገር!!!
ሞሀመድ እንድሪስ
በሰፊው የሚታየው የባንዲራ ፉክክር ርእዮተ-አለማዊ መሰረቱን እያጣ የብሔርተኝነት መግለጫ ምልክት ወደመሆን በጎ ሽግግር ውስጥ እያለፈ ነው የሚል ሀሳብ በተደጋጋሚ አንስቼ ነበር። ለዚህ ደግሞ ያበቁኝ ሶስት ምክንያቶች ነበሩ:
በሀገር ቤትና ከሀገር ውጭ የተለያየ ርእዮተአለማዊ መሰረት እንዳላቸው የሚታመኑ ባንዲራዎች ለተመሳሳይ መፃኢ የፓለቲካ ግብ በጋራ መታየታቸውና የማይደግፈውን ባንዲራ ለሚደግፈው ትግል ሲል መታገስ ብሎም ማውለብለብ በተግባር በመለመዱ
ሁለቱ ተቀናቃኞች እሳት እና ጭድ ሲባሉ የነገ የለውጥ ፍላጎታቸው ገፍቷቸው እንደዛ አለመሆናቸውን ለማሳየት በድርጅትም በአክቲቪዝም ደረጃም የሄዱትን ርቀት በማስተዋል
ኢትዮጵያዊነትን አውልቆ እንደጣለ ሲከሰስ የኖረው ክፍል ኢትዮጵያን ከገባችበት ቅርቃር እንድትወጣ ግንባር ቀደም ተሰላፊ መሆኑ በሌሎች ህዝቦች ውስጥ የፈጠረው መልካም ምስል
አሁንም ይህ ሀሳብ እንደሚሰራ አምናለሁ። ሰሞኑን የተፈፈጠረው ውጥረትም በህግ አካላት ጣልቃገብነት እና በግዜ ሂደት ይረግባል። ከመስከረም አምስት በሁዋላ የባንዲራ ፖለቲካችን አንድ እርከን ከፍ ብሎ መሰረት እንደሚይዝ ይጠበቃል። የባንዲራ ጉዳይም ህዝበ ውሳኔ የሚፈልግ እየሆነ መምጣቱ የሚያጠራጥር አይመስልም። ነገር ግን እስከዛሬ በአመዛኙ የአረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ መደብ እንደ ዋና ተወስዶ አርማው ላይ የነበረውን ክርክር (ድርድር) ወደመደቡ ያሻግረዋል። ከዚህ በሁዋላ የልሙጡ ባንዲራ መደብ ብቸኛ የብሔራዊ ባንዲራ እጩ ሆኖ የመቅረቡ እድል በራሱ ጥያቄ ውስጥ ይገባል። ክርክሩ አርማ ብቻም አይሆንም። ከአንተ በላይ ኢትዮጵያዊና የኢትዮጵያዊነት አርማ ብይን ሰጪ ነኝ የሚሉ ስሜቶች በተቃራኒው ወገን ላይ የሚፈጥሩት ስሜት አርማ የለሹን ባንዲራ ይበልጥ ዳር እያስያዙት ብሔራዊ የመሆኑን እድል ይቀንሱታል። በተቃራኒው የኦነግ እና ሌሎች ባንዲራዎች ቢያንስ ይወክለኛል ለሚሉት ህዝቦች የማይነካ መብት ይሆናሉ። የአዲስ አበባውን ፀብ የጫሩት አካላት ለዚህ ሰበብ ሆነው ማለፋቸው የሚቀር አይመስልም።
የፖለቲካ ሀይሎች ይሄንን እውነታ መቀበላቸው የተሻለ ይሆናል። በህግ ሊፀኑ የሚችሉ በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም እንደ ባንዲራ ያሉ ብሔራዊ አርማ እና ክብር መግለለጫዎች ግን ብሔራዊ ተቀባይነት ሲያገኙ እና በእርግጥም መከበር ሲችሉ ነው ሊፀኑ የሚችሉት። ይህ እውን እስኪሆን የወደድከውን እየሰራህ የሌሎችን መብት ከማክበር ውጭ አማራጭ አይኖርም። ለባህላዊ እና መንፈሳዊ አገልግሎቶች እንደሚደረገው አንድን አካባቢ ቀድሞ በቀለም ውክልና በመያዝ ቋሚ ርስት የማስመሰል አካሄድ አያስኬድም። በታሪክ እና አርማ ላይ አቁሞ ያስቀረን የፖለቲካ ርዕይ እጦታችን እንዲቀረፍ ከሰፈር የታሪክና የባንዲራ ዘቦች ይልቅ የፖለቲካ ሀይሎች በይፋ ወደመፍትሄው እንዲያመሩ ከምንግዜውም በላይ አሁን ይጠበቃል። ይህን ማድረግ ከተሳናቸው የፓርቲ ፖለቲካዎች ከፕሮግራሞቻቸው በላይ በአርማቸው የሚፈረጁበት ግዜ ውስጥ እየገባን ነው።
Filed in: Amharic