>

"ፈሪ በራሱ ጠብ ገላጋይ ይሆናል" (ኢ/ር ይልቃል ጌትነት)

“ፈሪ በራሱ ጠብ ገላጋይ ይሆናል”
ኢ/ር ይልቃል ጌትነት
ይህንን አባባል ያስታወሰኝ  የአማራ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ዛሬ በፌስ ቡክ ገፃቸው  የኦነግን ወደ ሃገር መግባት ምክንያት በማድረግ ከሚካሄደው የአቀባበል ዝግጅት ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን አለመግባባት በተመለከተ የሰጡትን አስተያየት በማንበቤ ነው። አቶ ንጉሱ እንደሚያስታውሱት በባህርዳር “ለውጥን” በመደገፍ በተደረገው ሰልፍ ጊዜ ጎልቶ ከወጣው አመለካከትና አርማ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሃይል አሰላለፍ በሚቀይር መልኩ በብዙ የፖለቲካ ሃይሉች ሰፈር ከፍተኛ መደናገጥ እንደፈጠረ የታወቀ ነው።
በቅርቡ በአዲስ አበባ የአርበኞች ግንቦት7ን መምጣት ተከትሎም ያንኑ አመለካከት የሚያጠናክር መረበሽ በብዙ የፖለቲካ ቡድኖች ካምፕ እየታየ ነው።
ሰሞኑን አዲስ አበባ የተፈጠረውም ችግር በወጣቶች መካከል የተፈጠረ ጊዚያዊ ግጭት ሳይሆን የዋናው ችግር መገለጫ ምልክት ነው።በኔ እምነት የርስወ ድርጅት የግንባር አባል የሆነውን ህወሃትን ጨምሮ ሌሎች ተመሳሳይ አመለካከት ያላቸው ወገኖች አሸንፈን የቀበርነው “የአማራ ትምክትና በእነሱ አባባል ጠቅላይ አንድነት” ተመልሶ እያንሰራራ ነው በሚል ስትራቴጂያዊ አጋር ፈጥሮ ይህን በህገ መንግስት ታግለው የቀበሩት ኢትዮጵያዊ ማንነትና የአማራ ትምክት እንዳያንሰራራ የመድፈቅ ስትራቴጅ አካል ነው።
አቶ ንጉሱ ጥላሁንና ድርጅታቸው በብዙ ሰው ዘንድ የለውጥ አካል ተደርገው እንደሚታዩ አውቃለሁና አሁን እየታየ ያለውን የአመለካከቶች ግጭት መገለጫ ምልክት የተረዱበት መንገድ ፈሪ በራሱ ጠብ ገላጋይ ይሆናል እንደሚባለው እንዳይሆን ያሰጋል።
በተለይም እወክለዋለሁ ከሚሉት የአማራ ህዝብ መብትና ፍላጎት አንፃር ቢመለከቱት መልካም ይመስለኛል።ግጭቱ የትልቅ ነገር መገለጫ እንጂ ትልቁን ነገር የመዘንጋት አይመስለኝም። ማድበስበስና በግልፅ የሚታይን ችግር አቃሎ ማየት ሀገራችንን ብዙ ዋጋ አስከፍሉዋልና ራስን አዘናግቶ ሌላውንም ማዘናጋት ይብቃ
Filed in: Amharic