>

የአቶ በረከት እና መሰሎቻቸው ሐሳቦች የሙታን ሐሳቦች ናቸው!!! (ታምራት ላይኔ)

የአቶ በረከት እና መሰሎቻቸው ሐሳቦች የሙታን ሐሳቦች ናቸው!!!

ታምራት ላይኔ
ቢቢሲ 
በሸኘነው ዓመት ማገባደጃ በሚዲያ ጎልተው ከወጡ ሰዎች መሐል የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ታምራት ላይኔ አንዱ ናቸው። በጥቂት ፖለቲካዊና በርከት ባሉ ማኅበራዊ ጉዳዮች ዙርያ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ጥያቄ፦ 2010 እንዴት ነበር?

አቶ ታምራትአንደኛው ለረዥም ዓመት የነበረው የፖለቲካ አስተሳሰብ አዲስ ነገር እንደሚፈልግ፤ ያለፈው ሁኔታ መሞት እንዳለበት ሕዝቡ ራሱ በተለያዩ መንገዶች ያሳየበት ዓመት ነበር። አሮጌ አስተሳሰቦች፣ አሮጌ አስተደደራዊ ዘይቤዎች ማለፍ፣ መሞትና መቅረት አንዳለባቸው የተበሰረበት ነበር።

ሁለተኛ መልካም ጅማሮች የታዩበትና ተስፈ የፈነጠቀበት ዓመት ነበር። ይህን የምለው ሕዝብ አስተያየቱን ያለምንም መደናቀፍ በነጻነት የሚገልጽበት ሁኔታ የተፈጠረበት በመሆኑ ነው። ይሄ ነው አዲሱ ፋና። ገና ጅማሮ ነው። ግን ጥሩ ጅማሮ ነው።

ጥያቄ፦ ከሰጧቸው ቃለምልልሶች በመነሳት የቀድሞው ባልደረቦችዎ ለምሳሌ እንደነ አቶ በረከት ስምኦን እርሶ ላይ የተአማኒነት ጥያቄን አንስተዋል?

አቶ ታምራት: በእኔ በኩልና ቤተሰቤ የነበርንበትን ሁኔታ ለረዥም ጊዜ ኢህአዴግና ባለሥልጣናቱ፣ በተለይ አቶ በረከትን ጨምሮ፣ ሕዝቡን ሲዋሹና ሲያጭበረብሩ የነበረበትን ሁኔታ እውነቱ ይሄ ነው ብለን ተናግረናል። እሱ ብቻ ሳይሆን እኔ በበኩሌ በሥልጣን በነበርኩባቸው ዓመታት አጠፋሁ ያልኳቸውን ‘አጠፋሁ’ ብዬ፣ ሕዝቡንም በሆነው ነገር ሁሉ ይቅርታ ጠይቄ፣ በኔ በኩል ሒሳቤን ዘግቻለሁ።

ከዚህ በኋላ እንደገና እሰጣገባ ውስጥ የምገባበት ምክንያት የለኝም። ሕዝቡ የትኛው እውነት የትኛው ውሸት እንደሆነ ያውቃል ብዬ አምናለሁ።

አቶ በረከት መግለጫ ሰጡ ከተባለ በኋላ የሕዝቡን ምላሽ እያየሁ ነው። ሕዝቡ ያውቃል። ማን ውሸታም እንደሆነ ያውቃል።

አብረዋቸው ለረጅም ጊዜ የሠሩ ሰዎች ሳይቀር እየወጡ ምን ያህል ዋሾ እንደሆኑ እሳቸውና ሌሎችም ጓደኞቻቸው ምን ያህል በቀለኛ ፣ ምን ያህል ቂመኛ እንደሆኑ እኔ ሳልሆን ሌሎቹ እየተናገሩ ናቸው። እኔ እንኳ እነኚህን ሁሉ ነገሮች ባውቅም ጉዳዩ የመበቀል ሳይሆን አዲሱን ትውልድ የማስተማር ጉዳይ ስለሆነ ዝርዝር ውስጥ አልገባሁም ነበር።

ሁለተኛው [እዚህ ጉዳይ ውስጥ መመለስ]የማልፈልግበት ምክንያት ይሄ የአቶ በረከትና የመሰሎቻቸው ሐሳቦች የሙታን ሐሳቦች ናቸው፤ ከዚህ በኋላ፥ የሕያዋን ሐሳቦች አይደሉም። እኔ ደግሞ የሕያዋን የሆነ ሐሳብ ይዤ፣ አዲስ ከሚመጣው አስተሳሰብና ኢትዮጵያዊያን ወደ ፊት ሊያራምዳት ይችላል ብዬ ከማስበው ጋር ወደፊት የማስብ እንጂ ወደ ኋላ የማስብ ሰው አይደለሁም።

ጥያቄ፦ በሰጧቸው ቃለ ምልልች የሞቱ ሰዎችን ወቅሰዋል። ለምሳሌ አቶ መለስ እና አቶ ክንፈን። በሕይወት ያሉ ባለሥልጣናትን ስም ግን ከመጥቀስ ይቆጠባሉ። እውነትን ለትውልድ ማስተላለፍ ከፈለጉ ለምን ግማሽ እውነት መናገር መረጡ?

አቶ ታምራት፦ እንደኔ አመለካከት የሰዎችን ስም አለመናገር ግማሽ እውነት ሊባል አይችልም። ስም ያላነሳሁበት ምክንያት ቃለ ምልልሴ በዋናነት እውነቱን ለመናገርና ሁኔታውን ለትምህርት ለመተው ነው እንጂ ሰዎችን እያነሱ ለማብልጠል አይደለም።

አቶ በረከት ምስጋና ይግባቸውና በኔም በቤተሰቤም ላይ ሲያሴሩ የኖሩትን ሰዎች እነማን እንደሆኑ እኔ ሳልናገር ራሳቸው ተናግረውልኛል። እነማ እነማ እንደሆኑ፣ እነ እገሌ እነ እገሌ ብለው ራሳቸው ጠቅሰዋቸዋል። አንድ ጊዜ እኔን አንድ ጊዜ አቶ ታደሰን፥ አንድ ጊዜ አቶ ህላዌን አንድ ጊዜ አቶ አዲሱን እያሉ ጠቅሰዋል ሰዎቹ።

የሰዎችን ስም መናገር ለእኔ በጣም ቀላል ነገር ነው። ወደፊትም ደግሞ በዚህ ብቻ የሚቆም አይደለም። አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ በመጽሐፍ መልክም ይሁን በሌላ ስሞችን መግለጽና ማውጣት ይቻላል።

እናንተም ቢሆን ስም ላይ ባተተኩሩ ጥሩ ነው። ዋናው እውነቱ ፤ የተደረገው ነገር ነው። እኔ ይሄን ያደረኩት የሚመጣው መንግሥት እንዲህ ዓይነት ሥራዎችን እንዳይሠራ ነው እንጂ ወደኋላ ተመልሶ ለመቆዘም አይደለም።

በነገራችን ላይ በዚያ ቃለ መጠይቅ ውስጥ ክስና በቀል እንዳይመስል ብዬ ያላነሳኋቸው ብዙ ሌሎች ጉዳዮች አሉ። አዳዲስና ያልተሰሙ ጉዳዮች። ወደፊት እንደ የሁኔታው በመጽሐፍ ወይም በሌሎች መንገዶች ላነሳቸው የምችል።

ጥያቄ፦ መጽሐፍ እየጻፉ ነው ማለት ነው?

አቶ ታምራት: የመጽሐፍ ሐሳብ አለኝ። በዚህ ጉዳይ ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በእኔም በቤተሰቤም ሕይወት ላይ ያተኮረ እንደ ማስታወሻ ዓይነት ነገሮች የመጻፍ ሐሳብ አለኝ። ደግሞ እንዳልኩት ዋናው ዓላማ ለመበቀል ለመክሰስ ሳይሆን ትምህርቱ ለሚቀጥለው ትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ ነው።

ተስፋ አደርጋለሁ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይሆናል።

ጥያቄ፦ ትዊተር ወይ ፌስቡክ ገጽ አለዎት?

አቶ ታምራት: ትዊተር የለኝም። የፌስቡክ ገጾች ነበሩኝ በተለያየ ጊዜ የኔን የፌስቡክ ገጾች ሌሎች እየወሰዱ እቸገራለሁ። የኔ ያልሆነ መልዕክት እየተላለፈ ተቸግሬያለሁ። አንደኛው ችግርም የኢህአዴግ መሪዎች ናቸው፤ ስልካችንንም እየጠለፉ፣ ፌስቡካችንንም ‘ሀክ’ እያደረጉ ይጠቀሙ የነበሩት እነርሱ ናቸው።

ባለፉት 10 ዓመታት ከተፈታሁም በኋላ እስከዚህ ደረጃ ድረስ የወረደ ክትትል ነበረ፤ አሁንም ፌስቡክ አለኝ፤ ነገር ግን የኔ ያልሆኑ መልእክቶች እየተላለፉ ስላየሁ አልጠቀምበትም።

ጥያቄ፦ የት አገር ነው የሚኖሩት? ለመሆኑ የግል መኖርያ ቤት አለዎት?

አቶ ታምራትብዙ አሉባልታዎች ተብለው ያውቃሉ። ንግድ ውስጥ ተሰማርቷል። አሜሪካ ውስጥ ነዳጅ ማደያ አለው። ኮካ ኮላ ኩባንያ ውስጥ ሼር አለው። ትላልቅ ሕንጻዎች አሉት። ያልተባለ ነገር የለም። የኢህአዴግ መሪዎች ናቸው ሲዋሹ የኖሩት። እግዚአብሔር ፈቃዱ ከሆነ [እኔና ቤተሰቤ] አገራችን ተመልሰን መኖር እንፈልጋለን። እንደማንኛውም ሰው ቤት እንዲኖረን እፈልጋለሁ። አሁን የምኖረው መንግሥት በሰጠኝ የኪራይ ቤት ነው።

ጥያቄ፦ ኪራይ ቤቱን እንዴት አገኙ?

[ከእስር እንደተፈታሁ] ኪራይ ቤት እፈልጋለሁ፤ ቤት የለኝም አልኩ። እንደሌለኝ ያውቁም ስለነበር ኪራይ ቤት አገኘሁ።

ጥያቄ፦ ዶ/ር ዐብይ የእርስዎ እርዳታ ቢያስፈልጋቸው በምን መንገድ ሊያግዟቸው ይችላሉ?

አቶ ታምራት: አሁን ያለው ለውጥ ግንባር ቀደሞች የሆኑት ዶ/ር ዐብይን ጨምሮ እገዛ ያስፈልገኛል በሚሉበትና በሚያምኑበት ሁሉ ለማገዝ እኔ በበኩሌ ዝግጁ ነኝ። በዚህ በዚህ ብዬ አልመርጥም። ዓላማዬ ሁለት ነው። እንደኛ አሁን የተጀመረው ተስፋ በምንም መንገድ መቀልበስ አለበት ብዬ አላምንም። ሁላችንም እንደዛ እንዲሆን መፍቀድ የለብንም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን መፍቀድ የለበትም።

ሁለተኛ ለኢትዯጵያ ዘላቂ የሆነ የፖለቲካ ነጻነትና ፍትህ የሚሰፍንበት ሁኔታ እንዳይ ነው የምመኘው። እነዚህን ጉዳዮች እስካገዘ ድረስ በዚያ ቦታ በዚህ ቦታ፣ በዚህ ሁኔታ በዚያ ሁኔታ ሳልል ምርጫ ሳይኖረኝ ለማገዝ ዝግጁ ነኝ።

Filed in: Amharic