>

ስለ "ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች" ተረት ተረት (ሳሙኤል ገዛህኝ በላቸው)

ስለ “ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች” ተረት ተረት
ሳሙኤል ገዛህኝ በላቸው
ይህ የተንዛዛ እና የተግተለተለ ሀረግ ህወሃት ህዝብን ለማታለያ እና ለክህደት ዓላማው መጠቀሚያ እንዲሆን ያጨቀው ነው:: (ኦነግም ተባባሪ ነበር)
የህገ-መንግስቱ መግቢያ (preamble) የሚጀምረው በነዚህ በተምታቱና በተጭበረበሩ ሀረጎች ነው እኛ በማለት:: እነዚህ ህወሓት ሰራሽ የተግተለተሉ ሀረጎች የህገ-መንግስቱ (የቃልኪዳን ሰነድ) ባለቤት ናቸው ይለናል::
እነማን ብሄር እነማን ብሄረሰብ እነማን ህዝቦች እንደተባሉ አይታወቅም:: አሁን ህወሓትም የሚያውቀው አይመስለኝም::
በህገ-መንግስቱ የተገለፀና የአንቀፅ 39 አጃቢ  ተደርጎ ጎጠኞች ደጋግመው የሚጠቅሱት: አንድ ሌላ  ተቀፅላ አለ ‘በህዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተች አገር’ የምትል ሀረግ::
በእርግጥ እነዚህ የተፈቃቀዱትና ፈቃዳቸውን የሰጡት እነማን ናቸው? የነማን ፈቃድ ነው ኢትዮጵያን ትሁን ትኑር ብሎ ያቆማት ? ብለን እንጠይቅ::
እንደ ክህደቱ: አንዳንድ ህዝብ እና ብሄር ተብለው የተጠቀሱት አስቀድመው ራሳቸውን የቻሉ: በራሳቸው የቆሙ: እንደ ሀገር መሪ ስርአት እና ግዛት የነበራቸው ናቸው ይሉናል:: እነዚህ ህዝብና ብሄር ደረጃ ደርሰዋል ተብለው የተሰየሙት አሁን የክልልነት መብት እና ቁመና የተሰጣቸው ናቸው:: በኃላ ላይ የተደፈጠጡትን ወደ 8እና 9 ግድም በደቡብ የነበሩ ክልሎችንም አስቧቸው::
ኢትዮጵያን እና ህገ-መንግስቱን ፈቅደው የመሰረቱት እነዚህ ክልሎች ሉዓላዊ አገራት ነበሩም ይሉናል:: በዚህም መሰረት ኦሮሚያ የሚባል: ከጭንሀክሰን እስከ ደምቢዶሎ: ከሞያሌ እስከ ጎሀ ፅዮን የተዘረጋ አገር: አማራ የሚባል: ከደባርቅ እስከ ደጀን: ከባህርዳር እስከ ወልድያ የተዘረጋ አገር:  ትግራይ የሚባል: ከዛላምበሳ እስከ አላማጣ: ከሁመራ እስከ እስከ መቀሌ የተዘረጋ አገር: ሶማሌ የሚባል: አፋር የሚባል: ቤንሻንጉል የሚባል: ጋምቤላ የሚባል: ሀረሪ የሚባል እንዲሁም በኃላ የተጨፈለቁት በደቡብ ያሉ 9 ሉዓላዊ አገራት ነበሩ ይሉናል:: እነዚህ ሉዓላዊ ሀገራት ፍቃደኛ ሆነው ኢትዮጵያን መሰረቱ ነው የተረቱ ማጠንጠኛ::
ኢትዮጵያዊ ዜግነት ብቻውን አይቆምም: ኢትዮጵያዊ ማንነትም የለም የሚለው ክህደታቸው መሰረት የሚያደርገው ይሄን ‘የብሄር በሄረሰቦችና ህዝቦች’ ተረት ነው:: ከኢትዮጵያዊ ዜግነት ይልቅ የአማራ አገር ዜጋ: የኦሮሞ አገር ዜጋ…ወዘተ ናቸው ያሉት ይሉናል::
ግን ይህ ሁሉ ክህደት አላማው ምንድነው? ለምን አስፈለገ ? በቀጥይ እናየዋለን::
 
ኢ ት ዮ ጵ ያ  እ ና  ኢ ት ዮ ጵ ያ ዊ ነ ት  
 ለ ዘ ላ ለ ም   ይ ኑ ር  !!
Filed in: Amharic