>

‹‹በብሽሽቅና በስድድብ እልህና ጥላቻ እንጂ የሀሳብ የበላይነትን መጎናጸፍ አይቻልም!!!›› (አህመዲን ጀበል)

‹‹በብሽሽቅና በስድድብ እልህና ጥላቻ እንጂ የሀሳብ የበላይነትን መጎናጸፍ አይቻልም!!!››
አህመዲን ጀበል
የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለጉብኝት ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ የኤርትራን ባንድራ  ያውለበለቡ ወጣቶች ዛሬ ደግሞ በራሳቸው ሀገር ዜጎች በሚውለበለቡ ባንድራዎች ምክንያት የቃላት ጦርነትን ተከትሎ ይህ ሁሉ ግጭትና የሰው ሕይወት እስከማጥፋት መድረሱ ያሳዝናል፡፡ይህ ብቻውን ቆም ብለን ስለሀገራችንና ሕዝቦቿ ያለንን እምነትና ስሜት እንድናስብ ካልገፋፋን እኛም አንዱን ጎራን ተቀላቅለን በስሜትና በእልህ ባህር ዉስጥ እየተጓዝን አልያም ደንታቢስነት እየተጠናወተን ለመሆኑ ማሳያ ይሆናል፡፡ ወገኖቼ ሆይ!
ስድድብ፣ማጠልሸትና ብሽሽቅ ስሜትን እንጂ አእምሮን ለመማረክ ታሳቢ ስለማያደርግ በብሽሽቅና በስድብ ተጨማሪ እልህና ጥላቻ እንጂ የሀሳብ የበላይነትን መጎናጸፍ አይቻልም፡፡ ተበድሎም ይሁን የተበደለ መስሎት በማህበራዊ ሚዲያዎች እንደምናየው በስሜት ተሞልቶ የጥላቻ ቃላትን ከአንደበቱ ያወጣ ሰው ልብ ላይለው ይችል ይሆናል እንጂ ፣አናደድኳቸው ወይም ልክልካቸውን ነገርኳቸዉ ብሎ ኃላፊነቱን የተወጣ የመሰለው ሰው የተናደዱቱ  በመናደዳቸው ብቻ ስሜት ዉስጥ ገብተው ምን ሊሆኑና ምን ሊያመጡ እንደሚችሉ በንቀት ተመልክቷል አልያም ዘንግቷል፡፡ እስቲ አስተዉላችሁ ተመልከቱ፡፡ ጥላቻና ንቀት ተፈጽሞብናል ብለው ያመኑ አካላት የጠሏቸውንና የናቋቸውን አካላት ብቻ ሳይሆን በስሜት ተነድተው የነኛን ንጹኻን ወገኖችን ጭምር በጥላቻ ሊመለከቱ ወይም ሊፈርጁ ባስ ካለም ሊበቀሉ ይችላሉ፡፡ይህ ደግሞ በቀላሉ ሊታለፉ ይችሉ በነበሩ ጉዳዮች ሀገራችን ስትታመስ፣ዜጎች ሲሳቀቁ ማየት ‹‹ሀገሬንና ወገኖቼን እወዳለሁ›› ለሚል ሰው በቀላሉ የሚታይ ተራ ነገር ሊሆን አይችልም፡፡
መልካም እና ችግሩን ሊፈታ ወይም ሊቀንስ የሚችል ነገር መጻፍ ወይም መናገር አቅሙ የለኝም ብሎ ቢያስብ እንኳ በችኮላና በስሜት ተነድቶ በሚሰጠው አስተያየት በሺዎች የሚቆጠሩ የማህበራዊ ሚዲያ ተከታዮቹን ከማሳሳት አልያም በችግሩ ላይ ችግር ከመጨመር መቆጠብ ይችላል፡፡ በኛ ስሜታዊ ንግግር ወይም ድርጊት ወይም አዎንታዊ ሚና መጫወት ስንችል በቸልተኝነታችን ምክንያት ለሚያልፍ ጊዜያዊ ክስተት የተነሳ ዘላቂ ጠባሳ የሚያሳርፍ መቃቃርና ጸብ ምክንያት ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ሕይወት ሲጠፋ እንዴት አስችሎን በስሜታዊነታችን እንቀጥላለን?
ዛሬ የዉዝግብ ምክንያት የሆኑ ባንድራዎች ከጥቂት ወራት በፊት ህገወጥ ተብለው በነርሱ ምክንያት ብዙዎች ታስረዋል፡፡ለምሳሌ በእስር ቤት በነበረኝ ቆይታ በርካቶች አሁን በየአደባባዩ እየተሰቀሉ ያሉ የኦነግ ባንድራዎች በቤታቸው መገኘቱ ብቻዉን በቂ ማስረጃ ሆኖ ዓመታት ሲያስፈርድባቸው ነበር፡፡በተመሳሳይ መልኩ ኮከብ የሌለውን ባንድራ ይዞ መገኘትን ህገወጥ ብሎ የሚፈርጀው ህግ በተግባር እንጂ አልተሻረም፡፡
ባለፉት ጥቂት ወራት በመጠኑም ቢሆን እያጣጣምነው ያለው የነጻነት አየር ገና ተቋማዊ መሰረት ይዘው አስተማማኝነት ደረጃ ላይ አልደረሱም፡፡ ብዙ ሥራ ይቀረዋል፡፡ በአሸባሪነት ተፈርጀው የነበሩት የተቃዋሚ ፓርቲዎችም ዛሬ እየመጣ ያለውን ነጻነት ለማምጣት ብዙ ዋጋ ከፍለዋል፡፡ በዋነኛነት በህዝባዊ እንቢተኝነት እና በኢህአዴግ ፓርቲ ዉስጥ ለውጥ ፈላጊ መሪዎች ባይፈጠሩና በመናበብ ትግሉን ማፋፋም ባይችሉ ኖሮ እነኚህ ፓርቲዎች ይህንን ነጻነት ለማምጣት በትጥቅ ትግሉ ለዓመታት ይቀጥሉበት ነበር፡፡ ይህን ሁሉ በመረዳትና በማስታወስ በየሀገሩ የተሰደዱና ትናንት በአሸባነት የተፈረጁትን የኢትዮጵያ ልጆችን ለሀገራቸው ስለበቁ ደስ ብሎናል፡፡ አቀባበልም አድርገንላቸዋል፡፡ በፖለቲካዊ አቋም፣ በብሄር፣በሃይማኖትና በሌሎች ነጥቦች የምንለያያቸው ቢኖሩም ባመኑበት መንገድ ለውጥን ፍለጋ ታግለዋል፡፡ ዋጋ ከፍለዋል፡፡ ስለሆነም በፖለቲካ አቋማቸው የምንደግፋቸውንም የማንደግፋቸውን የፓርቲ አመራሮችን፣አክቲቪስቶችን እና ሌሎች ተሰዳጆችን ተቀብለናል፡፡ ደስም ብሎናል፡፡ ሆኖም ደስታችን ዘላቂ የሚሆነው ያስደሰተን ሁኔታ ቀጣይነት ሲኖረው ብቻ ነው፡፡ የኛ ተግባራት ግን እየተፈጠረ ያለውን የነጻነት ማስቀጠል የሚችል ነው? ወይንስ ቀልባሾችን  የሚያግዝ ነው? እስቲ ቆም ብለን  በማስተዋል እንጠይቅ፡፡ አበቃሁ፡፡
Filed in: Amharic