>
5:13 pm - Wednesday April 19, 9499

ቄሮ ለለማ ፣ ለማም ለቄሮ  (ፋሲል የኔአለም)

ቄሮ ለለማ ፣ ለማም ለቄሮ 
ፋሲል የኔአለም
እውነት ይነገር። ቄሮ ወያኔን መቀመቅ ለመጣል በተደረገው ትግል ትልቅ መስዋዕትነት ከፍሏል። ከወያኔ በሁዋላ ግን ሚናውን መለየት ተስኖታል። ከፋፍለውታል፤ ቅርጽ የለውም፤ አንድ መሪ አላገኘም። በምስራቅ ሃረርጌ፣ በቡሌ ሆራ እና በብዙ ቦታዎች ቄሮ ካልፈቀደ የመንግስት ስራ አይሰራም።  በድሬዳዋ መሬት እየሸነሸነ ይሸጥ እንደነበር ተድርሶበታል፤ በጉጂ፣ በቡራዩና ሌሎችም ቦታዎች  እንዳየነው ደግሞ ከዘረፋ አልፎ ብሄር ተኮር ጥቃት ይፈጽማል። ቅዱስ አላማ ይዞ የተነሳውና ብዙ ተስፋ የተጣለበት ቄሮ በመሪና በአደረጃጃት ችግር ባክኖ እየቀረ እንደሆነ ይሰማኛል። ቄሮ የተስፋ ምንጭ እንዳልተባለ የስጋት ምንጭ ተደርጎ እየተቆጠረ ነው። ቄሮ ከድል በሁዋላ ምን እንደሚፈልግና ፍላጎቱን እንዴት እንደሚያሳካ ባለማወቁ፣ በቄሮ ስም የሚነግዱ ሃይሎች እንደፈለጉ እንዲዘውሩት በር ከፍቶላቸዋል። የምስራቅ ሃረርጌው፣ የቦረናውና የጉጂው ቄሮ በማን እንደሚመራ አይታወቅም፤ የቄሮ መሪ ነን የሚሉ ብዙ የሰፈር ጎርምሶች አሉ። የአርሲና ባሌ ቄሮ በእነ ጃዋር እንደሚመራ ይታወቃል። የወለጋው ቄሮ ልቡ ከእነ ዳውድ ኢብሳ ጋር ነው፤ መሃል ያለው የሸዋው ቄሮ አብዛኛው ከኦህዴድ የተወሰነው ደግሞ ከ ኦፌኮ ጋር ነው። ለኦህዴድ አክብሮት ያለውና በአንጻራዊነት በስርዓት እየተመራ ያለው ይህ ክፍል ቢሆንም፣ ኦህዴድ ገና ሙሉ በሙሉ አልተቆጣጠረውም። የተለያዩ ሃይሎች ሊጠቀሙበት ሲሞክሩም እያየን ነው።
የእነ በቀለ፣ ጃዋርና ዳውድ ቡድን የለማን ቡድን መደገፍ ይኑርበት አይኑርበት ገና አልወሰነም። እነ ለማ ኦሮሞ ስለሆኑ ሊደግፋቸው ይፈልጋል። እነሱን መቃወም የኦሮሞ ሃይል እንዲከፋፈልና እንዲዳከም ያደርጋል ብሎ ይሰጋል። በሌላ በኩል ግን እነ ለማና አብይ ይዘውት የተነሱት የኢትዮጵያነት ትርክት ምቾች አልሰጠውም። ለአንድነት ሃይሉ “ተሽጠዋል” ብሎ ያስባል። ከብአዴንና ከአርበኞች ግንቦት7 ጋር ህብረት ይፈጥሩ ይሆን ብሎም ይሰጋል። በግንቦት7 ላይ የሚደርሰው ውግዘት መንስዔውም ይኸው ነው። ፍርሃት የወለደው ውግዘት ። እነዚህ ሃይሎች የአንድነት ፖለቲካው የብሄር ፖለቲካውን አክስሞ ከገበያ እንዳያስወጣቸው ይሰጋሉ። ስለዚህ የደገፉ መስለው እየተቃወሙ መቀጠልን እንደ ስትራቴጂ ወስደውታል። ዛሬ ደገፉ ስንላቸው ነገ ሲቃወሙ የምናገኛቸው ለዚህ ነው። ነገሩ “ላም እሳት ወለደች፣ እንዳትልሰው ፈጃት እንዳትተወው ልጇ ሆነባት” አይነት ነው። ለማ እሳት ሆኖባቸዋል። ይህ ሃይል ህልውናውን ለማቆየት ወይም “አለሁ” ለማለት የተወሰነ ደጋፊውን ስሜት እየኮረኮረ ለማነሳሳት ሲሞክር ይታያል። በሰለጠነው አለም ቁጭ ብሎ ዘረኝነትን ሲስብክ ትሰማዋለህ። ዛሬ በየቦታው “ያዝ” እየተባለ የሚላከው ወጣት ተስፋ ሲቆርጥ ነገ በራሱ ላይ እንደሚነሳበት እንኳ ትንሽ ለማወቅ አልቻለም።  ፍርሃትና የስልጣን ፍቅር ማሳላሰያውን ደፍኖታልና። ይህ ሃይል ተጣማሪ ብሄርተኛ ለመፈለግ ላይ ታች እያለ ነው፤ ህወሃትን ጨምሮ የብሄር ድርጅቶችን በማሰባሰብ የአንድነት ሃይሉን ለመገዳደር እየሞከረ ነው፤ ነገ ከህወሃት ጋር ጥምረት ቢፈጥር አንገረም።  የወደፊቱ የሃይል አሰላለፍም ከዚህ አያልፍም።
ቄሮ የለውጥ ሃይል ሆኖ እንዲቀጥል በአንድ መሪ ስር መደራጃት አለበት። በእኔ እምነት  ቄሮን ለማ መገርሳ ቢመራው ወሳኝ ሃይል ሆኖ ይወጣል። ለማ ያልተቆጣጠረው ቄሮ ስጋት እንጅ ለኢትዮጵያ ተስፋ ሊሆን ስለመቻሉ እጠራጠራለሁ። እስካሁን ባየሁት የለማ ቄሮ አገር ይገነባል እንጅ አያፈርስም፤  ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን ይሰብካል እንጅ ጥላቻችን እና ልዩነት አይሰብክም። ቄሮ ለለማ ፣ ለማም ለቄሮ ተስማሚ ናቸው።
አሁንም በዘረኝነት መንገድ ለመንጎድ መንገዱን የጀመራችሁ የአገሬ ልጆች ይህን ልምከራችሁ። ዘረኝነት እንደሚያጠፋ እየሱስ ክርስቶስ ነግሮን አልገባንም፤ ነብዩ ሙሃመድ ደግሞልን አልተረዳነውም፤ ለ27 ዓመታት ብንጋተውም አልጠገብነውም። ሲገዘግዘን የማይሰማን፣ ሲጥለን የማይታወቀን በሽታ ዘረኝነት ነው።  የዘረኝነትን ቫይረስ የምትረጩ ሰዎች ቆም ብላችሁ አስቡ፤ እናንተ በምትረጩት የዘረኝነት ቫይረስ አገር ይታመሳል፤ ወገን ይታረዳል፣ ይፈናቀላል፣ ይዘረፋል።  ዛሬ በሳቅ የምትረጩትን መርዝ ነገ በለቅሶ ትጋቱታላችሁና ቆም ብላችሁ አስቡ። ዘረኝነት በአገራችን ጠፍቶ ሁላችንም በፍቅርና በአንድነት የምንኖርባትን ኢትዮጵያ እንመስርት!
Filed in: Amharic