>
5:14 pm - Monday April 20, 7153

“የዘር ፖለቲካ ከበደኖ እስከ ቡራዩ!”  (በያሬድ ሀይለማርያም)

“የዘር ፖለቲካ ከበደኖ እስከ ቡራዩ!” 

በያሬድ ሀይለማርያም

እንዴት አንድ ሃገር ከሁለት አስርት አመታት በኋላም ተመሳሳይ ዘር ላይ ያነጣጠረን ጥቃት ልታስተናግድ ቻለች? ይህን ጥያቄ የማቀርበው በዘር ላይ የተመሰረተውን ፖለቲካ አትንኩብን እያሉ ለሚጮኹ እና የትላንቱን የቡራዩን ጭፍጨፋ ከዘር ጋር እንዳልተያያዘ አድርጎ ለመሸፋፈን የሚደረገው ሙከራ አግባብ አለመሆኑን ለማሳወቅም ነው። መወገዝ የሚገባው ነገር በቅጡ ሳይጋነን እና ሳይቀባባ መወገዝ አለበት። መሬት ላይ ሕዝብ እያለቀ በሶሻል ሚዲያ ስለሚነገረው እውነታ የምትጨነቁ ሰዎች ነገሩን መልሳችሁ እንድታጤኑት ነው።

የዘር ፖለቲካ እያስከተለ ያለውን ኪሳራ እና እጅግ አስነዋሪ የሆነ የወንጀል ተግባር ከማውገዝ ይልቅ ስለአድራጊዎቹ የዘር ማንነት መጠቀስ የሚያሳስባችሁ ሰዎች እባካችሁ ቆም ብላችሁ ለአንድ አፍታ አስቡ። ትላንት የወያኔ ታጣቂዎች ሊያውም ከሁሉም ብሄር የተወጣጡ ንጹሃን ዜጎቻችንን ሲገድሉ ‘ትግሬ’ ገዳይ ስትሉ የነበራችው ሰዎች ዛሬ በአደባባ እና በጠራራ ጸሐይ በዘር ፖለቲካ ናላቸው የዞረ የተወሰኑ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች በሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻቸው ላይ አስነዋሪ እና የአውሬ ድርጊት ሲፈጽሙ ጉዳዩ ከዘር ጋር አይያያዝም እያሉ የወሮበሎች ተግባር ለማስመሰል የሚደረገው ሙከራ እጅግ የሚያስተዛዝብ ነው። እውነታው መነገር አለበት። የችግሩ ምንጭም በአግባቡ መገለጹ ወደ ዘላቂው መፍትሔም ይወስደናል።

የሆነውን ነገር በአግባቡ እና ባልተጋነነ መልኩ ተጣርቶ መገለጽ አለበት። አንዲ ሺ የሚሆኑ የኦሮሞ ወጣቶች በዚህ እኩይ ድርጊት ቢሰማሩ ቀሪውን የኦሮሞን ሕዝብ የማይወክሉ መሆኑን ሳይታለም የተፈታ ነው። የኦሮሞ ሕዝብ ጨዋ፣ ስልጡን እና እሩህ ሩን መሆኑ የታወቀ ነው። እንደነዚህ አይነቶቹ የአውሬ ባህሪ የተላበሱ ወጣቶች በሁሉም ማህበረሰብ ውስጥ ያሉ መሆኑን በጋንቤላ፣ በኦጋዴን፣ በአዋሳ እና በቤኒሻንጉል ጉምዝ የተከሰቱት ተመሳሳይ ድርጊቶች ማሳያዎች ናቸው። ነገር ግን እነዚህ ወጣቶች ድርጊቱን በዘረኝነት መንፈስ ውስጥ ሆነው እስከፈጸሙት ድረስ ይህ እውነታ ሊገለጽ እና ሊወገዝ ይገባል።

አንዳንድ በማህበራዊ ድህረ ገጾች እና በግልም የተላኩልኝ የቪዲዮና የምስል ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት የተፈጸሙት ድርጊቶች እጅግ ሰቅጣጭ፣ የአድራጊዎቹን የአዕምሮ ጤንነት እንድጠራጠር የሚያደርጉ የአውሬ ተግባራት ናቸው። ሰዎች፤ ሕጻናት ሳይቀሩ አንገታቸውን በገጀራ ታርደዋል፣ እርጉዝ ሴት ሳትቀር ተደፍራለች፣ ሽማግሌና አሮጊቶች ሳይቀሩ በገጀራና በዱላ ተደብድበዋል። ድርጊቱን የፈጸሙት ወጣቶች በዚህ መጥፎ አድራጎታቸው ምንም ሳይሸማቀቁ እና ሳያፍሩ ከገደሉት አስከሬን አጠገብ እየቆሙ እራሳቸውን ፎቶ አንስተው፣ አንገት ሲቆርጡም ቪዲዮ ቀርጸው በማህበረ ሚዲያዎች ጭምር ለቀዋል። አብዛኛዎቹ ወጣቶች ከሰላሳ ዓመት በታች ያሉ እና በወያኔ ዘመን ተወልደው የህውሃትን እና የኦነግን የዘር ጥላቻ ፖለቲካ እየተጋቱ እና እየተማሩና ያደጉ ወጣቶች ናቸው።

የወያኔን የመብት እረገጣ ለመታገል እና ለማውገዝ ባለፉት ጥቂት አመታት በብሔር መብት አቀንቃኞች የተደረጉት ዘር ተኮር የሆኑ የጥላቻ ፕሮፖጋዳዎች እና ቅስቀሳዎችም ወያኔ ባርከፈፈፈው የዘር ነዳጅ ላይ ክብሪት ሆነው አገሪቱን አደጋ ላይ ጥለዋል። ንጹሃን ዜጎችንም ለሞት እና መፈናቀል ዳርገዋል። በዘር መደራጀት፣ መብትን ማስከበር፣ ባህልን ማሳደግ እና ሌሎች ጥቅሞችን ማስጠበቅ ሊከበር የሚገባው መብት ነው። ይህን መብት ለመጠቀም ግን የሚደረጉ ዘር ተኮር ቅስቀሳዎች እና የጥላቻ ትርክቶች ውጤታቸው መጠፋፋት ብቻ ነው። እይን ለመማር ሱማሌን እና እሩዋንዳን መጥቀስ አያስፈልግም የትላንቱን በደኖን እና የዛሬውን ቡራዩን ማየት በቂ ነው።

እራሳችንን ከዘር ጥላቻ እናንጻ! በዘር ላይ የሚፈጸፉ ጥቃቶችንም በስማቸው እየጠራን እናውግዝ! ጥቂት የትግራይ ተወላጆች ለዘረፉት ትግሬዎች ዘረፉ እያለ ሲያለቃቅስ የሚውል ሰው እና ያንን ሲናገር ያልቀፈፈው ሰው፤ ጥቂት የኦሮሞ ወጣቶች በዘረኝነት ስሜት ሌሎች ኢትዮጵያዊያንን ጨፈጨፉ ማለት ሊቀፈው አይገባም።

Filed in: Amharic