>

በቡራዩ  ሕገ መንግሥት ተብዬው እየተተገበረ እንጂ እየተጣሰ አይደለም!!! (አቻምየለህ ታምሩ)

በቡራዩ  ሕገ መንግሥት ተብዬው እየተተገበረ እንጂ እየተጣሰ አይደለም!!!
አቻምየለህ ታምሩ
«ኦሮምያ  ክልል» በሚባለው ክልል ውስጥ በተለይም በቡራዩ  ከተማ  በተለይም ተወላጆች ላይ  እየተፈጸመ ያለው ዘግናኝ ግድያ፣ ግፍ፣ ጭካኔ፣ መድፈር፣ ዝርፊያና  የንብረት ማውደም  ብዙ ሰው እንደሚያስበው «ሕገ መንግሥት» የሚባለው ነገር እየተጣሰ አይደለም፤ እንዴውም እየተተገበረ እንጂ።  ሆኖም ግን ያገራችን ሰው  ሲደመር የከረመውን «ደማሪውን»  ዐቢይ አሕመድንና ቃለ መሐላ የፈጸመበትን  የወያኔ «ሕገ መንግሥት» ተቀብሎ  መሆኑን  ስንናገርር  ሰሚ አልነበረም።
ሕገ መንግሥት ተብዮው የተጻፈው «ለዘመናት ነበረ» የተባለውን የተዛባ  «የጨቋኝና የተጨቋኝ »፤ «የሰፋሪና የነባር» ብሔር፣ ብሔረሰቦች  ግንኙነት  ለማጥፋት ነው። በሕገ መንግሥቱ መሰረት  የቡራዩ ባለቤት ኦሮሞ ብቻ ነው። ከኦሮሞ  ውጭ ያለው መጤና ሰፋሪ ቅኝ ገዢ  ነው ተብሏል። ነዋሪው አማራ ከሆነ ደግሞ ጨቋኝ እንደሆነ ተደርጎ ተረክ ተፈጥሯል። በሕገ መንግሥቱ መሠረት  መጤና ሰፋሪ የተባለው ቡራዩ  መኖር የሚችለው በነባር ተብዮው ችሮታና ተከራይቶ ብቻ ነው። በሕገ መንግሥቱ መሠረት ክልልህ አይደለም የተባለ «ብሔር፣ ብሔረሰብ» ዜጋ አይደለም። ዜጋ ካልሆነ ጉዳዩ የሚታየው በሰብዓዊነት እንጂ እንደ ዜጋ  ተቆጥሮ አይደለም። በሰብዓዊነት ደግሞ እንደ ሰው ሁኔታ ይለያያል። ስለዚህ ሕዝበ አዳም ሕገ መንግሥታዊ መብታችን ይከበር እያልህ የምትጠይቀው  ሕገ መንግሥት ተብዮው የሰጠህ «መብት» እየተከበረልህ እንጂ ሕገ መንግሥቱ የሰጠህ መብት እየተጣሰብህ  አይደለምና የምትጠይቀውን እውቅ!
ዐቢይ አሕመድ ጠቅላይ ሚንስትር ሲሆን አገዛዙ የተዋቀረበት ርዕዮተ ዓለም እስካልተቀየረ ድረስ ምን ቅን ሰው ቢሆን ከወያኔ ዘመን የተለየ ነገር እንዲያመጣ ሕገ መንግሥቱ አይፈቅድለትም ብለን ተናግረን ነበር። ገፋ አድርገንም እውነተኛ ስልጣን ቢኖረው እንኳ የትግሬን የበላይነት በኦሮሞ የበላይነት ከመተካት በስተቀር ለኢትዮጵያውያን ሁሉ እንደዜጋ የሚበጅ ነገር እንዲያመጣ ርዕዮተ ዓለሙ አይፈቅድለትም ብለን ተናግረን ነበር።
አሁንም እንደግመዋለን! የኢትዮጵያ ችግር ጸረ ሰብ፣ ጸረ ሀገርና ሕገ ወጥ የሆነው አገዛዙ የተዋቀረበት ርዕዮተ ዓለም ነው። ከዐቢይ አፍ ማር ቢዘንብ እንኳ ተፈጻሚ የሚደረገው  ጸረ ሰብ፣ ጸረ ሀገርና ሕገ ወጥ የሆነው ርዕዮተ ዓለም ነው። ጸረ ሰብ፣ ጸረ ሀገርና ሕገ ወጥ የሆነው የወያኔ ሕገ አራዊት እስካለ ድረስ የሕግ የበላይነት፣ ንብረት የማፍራት፣ ዜጋ የመሆን፣ የሕይወት ጥበቃ፣ ወዘተ የሚባሉ መብቶች የሉህም።
ባጭሩ የጭካኔ አስተሳሰብ የወለደው የፋሽስት ወያኔ ሕገ አራዊት ዋጋ እንዲያጣ ሆኖ እስካልተወገደ ድረስ ክልልህ አይደለም በተባለው አማራና ኦሮሞ ላይ ዛሬ በጅግጅጋ እየደረሰ ያለው የወያኔ ሕገ መንግሥት የወለደው ግፍና ጭካኔ የጊዜ ጉዳይ እንጂ በየተራ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ላይ መፈጸሙ የማይቀር ነው።
የፋሽስት ወያኔ አገዛዝ  የተዋቀረበት ርዕዮተ ዓለምና  ዋለልኝ መኮነን በፈጠረው እስር ቤት ውስጥ የታጎሩትን  «ብሔር፣ ብሔረሰቦች» ለማስፈታት  በመለስ ዜናዊ  እሳቤ የተወለደችው  አዲሲቷ ኢትዮጵያ  የተፈጠረችበት  የ ያ ትውልድ ጸረ ሰብ ትርክት ከነ ግሳንግሱ  ከስሩ ተለቅሎ ዋጋ እንዲያጣ ተደርጎ  እስካልተወገደ ድረስ አንዱ  ብሔርተኛ  ሄዶ  ሌላው ብሔርተኛ  ቢመጣ የበላውና  የጠገበውን ሸኝቶ  የራበውና ሁሉ ብርቁ የሆነውን ከመተካት በስተቀር ለኢትዮጵያ ሕዝብ  አንዳች ጠብ  የሚያደርግለት ነገር የለም።
በጠቅላይ ሚንስትሩ ወንበር ላይ  ማን እንደሚቀመጥ ሳይታወቅ ከወራት በፊት በአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው ክፍል ባዘጋጀው የክርክር መድረክ ላይ ተሳትፌ  በነበረ ወቅት የተናገርሁት ሀሳብም  ተመሳሳይ  ነበር። የወያኔ አገዛዝ የተዋቀረበት ርዕዮተ ዓለምና ሕገ አራዊት ሳይወገድ ማንም ወደ ስልጣን ቢመጣ ወያኔ የቆላንን ያሳርረን  እንደሆነ እንጂ  የሚፈይድልን ነገር የለም ብዬ ነበር! የትናንትናውና የዛሬው የአዲስ በባ ውሎ ለዚህ አንድ ማሳያ ተደርጎ ሊወደድ ይችላል!
Filed in: Amharic