>
4:42 pm - Wednesday January 18, 6536

ስለጎሰኝነት፣ ክልል፣ ዲሞክራሲ እና ተዛማጅ ጉዳዮች ምክረ ሃሳብ!!!  (ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ)

ስለጎሰኝነት፣ ክልል፣ ዲሞክራሲ እና ተዛማጅ ጉዳዮች ምክረ ሃሳብ!!!
 ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ
ጎሰኝነት
እንደዚህ ቃል የሰለቸን ሌላ ቃል ያለ አይመስለኝም። ግን ብዙ ቢተችም፥ ብዙ ቢጣጣልም፥ ዱሮውንም ሊሆን የማይገባውን የጎሰኝነትንና የፖለቲካን ጋብቻ ማፋታት አልተቻለም። ስንተቸው አድረን ጠዋት ሲነጋ እዚያው ማታ እተውንበት ቦታ ቁጭ ብሎ እናገኘዋለን። ለምን ይሆን? እንደሚመስለኝ፥ ጎሰኝነትን የተማሪዎቹ እንቅስቃሴ ለአንዳንዶች ካቀመሷቸው ወዲህ ሱስ ሆኖባቸዋል። ጎሰኝነት ሱስ ነው። ሲኖሩም ጎሰኛ፥ ሲሞቱም ጎሰኛ ሆነው ሊቀሩ። አንዳንድ ሰዎች በሱስ መይያዛቸውን ስለማያምኑ የሱስ መድኃኒት ፍለጋ አይሄዱም፤ ቢሰጣቸውም አይቀበሉም።
ኦሮሞዎች በሚኖሩበትና በአዲስ አበባ ከተማ ጎሳን የማያመለክት የመታወቂያ ወረቀት እየወጣ መሆኑ ይነገራል። ትልቅ ዜና ነው። ግን ጎሰኝነት መፋቅ ያለበት ከወረቀቱ ላይ ይልቅ ከሰዉ አስተሳሰብ ላይ ነው። እነዚህ በጎሰኝነት ሕዝብ የሚበጠብጡት ልጆች መታወቂያቸው ጎሳ-አልባ ስማቸውም ኦሮምኛ፥ ወላይትኛ፥ ሱማልኛ፥  ያልሆነ ሊሆን ይችላል። የነሱ አስተሳሰብ ግን በጎሰኝነት ተበክሏል። የሚፈልጉት ምን ይሆን? በአንድ አፍ የሚናገሩ ቢሆን፥ ያንን አፍ ፈልገን እንጠይቀው ነበር። አገር መግዛት ነው? ወይስ መገንጠል? ማንን እንጠይቅና ለዚህ ጭቅጪቅ ፍጻሜ እናግኝና እፎይ እንበል? መግዛት አምሯቸው እንደሆነ፥ ከእንግዴህ ወዲህ ማንም በማንም መገዛት አይፈልግም። መለያየት ከሆነም፥ መለያየት ማንንም ከሌላው የበለጠ አይጐዳም።
ክልል
ጎሰኝነትና ክልል የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጾች ናቸው። ክልል የቆመው ሰብአዊ መብት ላይ ነው። የትም ቦታ የመኖር መብትን ይጥሳል። ስለክልል ክፋት የተጻፈው ስለጎሰኝነት ክፋት የተጻፈውን ያህል ቢሆንም፥ አንድ ያልተሠመረበት ጉዳይ ቀርቷል። እሱውም፥ ያንድ ክልል ሰው ወደ ሌላው ክልል ሄዶ እንዳይኖር መከልከሉ የሚያስከትለው ጉዳት ነው። ተጎጂው የዚያ ክልል ሰዎች ናቸው። አዲስ ደም እንዳያገኙ ይከለከላሉ። አሜሪካ በቴክኖሎጂ ልቃ የሄደችው የውጪ ደም የሚገባበትን ቦይ ሁል ጊዜ ክፍት ስላደረገች ነው።
ዲሞክራሲ
አንዳንድ ሰዎች በዲሞክራሲና በጎሰኝነት ሲምሉ ይሰማሉ፤ “በአንድ ራስ ሁለት መላስ” እንደሚባለው ነው። ከሁለቱ አንዱን መያዝ ግድ ይላል። ምክንያቱም፥ ዲሞክራሲ የአሸናፊ ፓርቲ አስተዳደር እንጂ የጎሳ ገዢነትን አያመጣም። ኢትዮጵያ ውስጥ ማንም በጎሳ የተደራጀ ፓርቲ በምርጫ ሊያሸንፍ አይችልም። ግፋ ቢል፥ ሁለት ሦስቱ የጎሳ ፓርቲዎች ጣምራ ቢፈጥሩ ነው። የቱና የቱ ጎሳ? ሁሉም በተፋጠጠበት አገር ሰላማዊ የጎሳ ፓርቲ ጣምራ አይታሰብም፤ አይቻልምም። ቢቻልም እንኳ የተሸነፉትን ጎሳዎች ለመጨቈን እንጂ ከዚያ አልፎ፥ የአንድ ጎሳ ግዛት አይሆንም። ባጭሩ፥ አንድ ሀገር የተኳረፉ ጎሳዎች በሰላም መኖሪያ ልትሆን አትችልም። ዶክተር ዐቢይ የኢትዮጵያን ትልቅነት ለማሳየት ይጥራል። የሕዝቧን ኋላ-ቀርነት የሚያውቅ አይመስልም። እግዚአብሔር ይርዳው።
ባንዲራ
ካሳደገችን ባንዲራ ጋር ፍቅር የያዘን ጥቂቶች አይደለንም። እኔ ሳያት ሆዴ ይንሰፈሰፋል። ምንም ምክንያት ቢሰጠን ከሷ ፍቅር (ሱስም በሉት) ሊለየን አይችልም።  አሁን ያለው መንግሥት የሚገዛን ደርግ ዘውዱንና መስቀሉን በጐረደው አንበሳ ምትክ ኮከብ ባለበት አረንጓዴ፥ ቢጫ ቀይ ቀለም ባለው ባንዲራ ነው። ቀለሙን ያቈየው የሕዝብ አመፅ ነው እንጂ፥ ያ ተንኮለኛማ ሌላ ቀለምና አርማ ባለው ባንዲራ ሊተካት አስቦ ነበር። ሆኖም፥ ሊለውጣት ያሰበው “ከቀለሙ በስተጀርባ ባለው ምክንያት ነው” በማለት ክፉ ትርጕም ስለሰጣት፥ በዚያ ትርጕም ምክንያት የሚጠሏትም አሉ። ብዙ የአፍሪካ አገሮች በቅኝ ግዛት ሥር በነበሩበት ጊዜ የኛ ባንዲራ ብቸኛ አፍሪካዊት ባንዲራ ስለነበረች እንደ አፍሪካ (እንደ ራሳቸው) ባንዲራ ያዩዋት ነበረ። ነፃ ሲወጡ የራሳቸውን ባንዲራ ከኢትዮጵያ ባንዲራ ጋር እያዛመዱ ፈጠሩ። ፍቅራችን አብረናት ስላደግን ከመሆን አልፎ በዓለም ላይ የምታስከብረንም ሆነች። ራሱንና ታሪኩን የሚጠላ ገዢ ካልመጣብን ይቺ ባንዲራ አትቀየርም። የምንመኘው ዲሞክራሲ ሲሰፍንና የሀገሪቱ ባንዲራ በሕዝብ ድምፅ ይወሰን ቢባልም፥ በድል አድራጊነት ትውለበለብ ይመስለኛል።
ግን ልብ እንበል፤ “ወታደር በጦርነት የሚዋደቀው ለባንዲራው ነው” ሲባል ምን ማለት ነው? ለምሳሌ፥  የኢትዮጵያ ወታደር አድዋ ላይ፥ ካራ ማራ ላይ፥ ባድሜ ላይ የተዋደቀው ለባንዲራው ከሆነ፥ በጊዜው አገሪቱን ወክሎ ለሚያውለበልበው ባንዲራ እንጂ፥ ሁል ጊዜም ለአንድ ዓይነት ባንዲራ አይደለም። መዋደቁን ከአንድ ከተወሰነ ባንዲራ ጋራ ብቻ ማያያዙ ስሕተት ነው።
ዶክተር_ዐቢይ_አሕመድ
ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በቅርብ ጊዜ በባንዲራው ምክንያት ስለተነሣው ብጥብጥ የተናገረው ብዙዎችን አስቈጥቷል። ይኸ ብቻ አይደለም፤ የኢሕአዴጉ መሪ የኢሕአዴግን ባንዲራ ሲያውለበልብ ሲያዩም የሚገረሙ አሉ። እነዚህ ሰዎች የኢትዮጵያ ባንዲራ በመንግሥት ደረጃ ከ1964 ዓ. ም. ጀምሮ ሁለት ጊዜ እንደተለወጠ  ልብ አላሉትም። ሌጣውን ባንዲራ እነሱ ስላውለበለቡት የሀገሩ ሕጋዊ ባንዲራ መስሏቸዋል። በአሁኑ ጊዜ ከባለ ኮከቡ በቀር ማንኛውም ባንዲራ (ሌጣው ባንዲራ ሳይቀር) የኢትዮጵያ መንግሥት ሕጋዊ ባንዲራ አይደለም። ራሱ ዶክተር ዐቢይና ባንዲራው ከሕገ መንግሥቱ ጋራ የኢሕአዴግ ወገኖች ናቸው። የኢሕአዴግን ሕገ መንግሥት መጣስና የኢሕአዴግን ባንዲራ አለመቀበል ዶክተር ዐቢይን አለመቀበል ነው።
የዶክተር ዐቢይን አመራር ተቀብሎ፥ የኢሕአዴግን ሥርዓት አለመቀበል፥ “ከመረቁ አውጡልኝ ከሥጋው ጦመኛ ነኝ” ማለት ይሆናል። ከነዚህ ሰዎች ይልቅ የዶክተር ዐቢይን ለውጥ የማይቀበሉ ይሻላሉ። ሌጣውን ባንዲራ ማውለብለብ ያሳስር ነበረ። ዶክተር ዐቢይ “አንድ ኢትዮጵያዊ የፈለገውን ባንዲራ ቢያውለበልብ፥ ያልፈለገውን ቢያቃጥል ሐሳብን በነፃ ከመናገር የተለየ አይደለም” ብሏል። በዲሞክራሲ የሚምል ሰው ይኸንን አነጋገር መቀበል እንዴት ያቅተዋል? ሌላው ቢቀር፥ በዚህ ረገድ ከሠለጠኑት አገሮች እኩል አደረገን እኮ።
የጥንቱ ባንዲራችን እንዲመለስልን እንታገላለን። እስከዚያ ግን ሕጋዊው የኢትዮጵያ ባንዲራ የምንጠላው ባለኮከቡ ነው። ሌጣውን ባንዲራና የኦነግን ባንዲራ ስናውለበልብ ላለመታሰራችን ዶክተር ዐቢይን እናመስግን። በሕግ ፊት አሁን ሁለቱም እኩል ሌላ ባንዲራዎች ናቸው። ዶክተሩ፥ “በዘዴ የማመጣው ለውጥ ካላስደሰታችሁ ያውላችሁ አገሪቷን ሌላ ሰው ይምራት” ብሎ ሥራውን ቢለቅ እናጨበጭባለን ወይስ ሌላ ሰው ሲተካ፥ “ጉልቻ መለወጥ ወጡን አያጣፍጥም” እንላለን? እሱ ቢለቅ የሚተካ አይጠፋም። ግን ማነው የሚተካው? ሰዶ ማሳደድ እንዳይሆንብን እፈራለሁ። ሆኖም፥ ሕገ ወጦችን በስብከት ብቻ ማስተዳደር አይቻልም።
የፖለቲካ_ለውጥ
በአሁኑ ሰዓት ሁለት ዓይነት የፖለቲካ ለውጦች ይታዩኛል፤ ግን ሁለትነታቸውን መለየት አቅቶን እያምታታናቸው ተቸግረናል። አንዱ ለውጥ ኢሕአዴግ የራሱን ሕገ መንግሥት ጥሶ ሕዝብ ማጥቃቱን እንዲያቆም ማድረግ ነው። ኢሕአዴግ ያለ ሕግ ያስር፥ ይገርፍ፥ ያኰላሽ፥ በሰው አፍ ውስጥ ይሸና፥ ይዘርፍ ነበር። ዶክተር ዐቢይ ሊያመጣ የሚችለው ለውጥ ይኸንን ኢ-ሕገ-ኢሕአዴጋዊ ወንጀል ማቈም ነው። አቁሞልናል፤ ነፃነት ተሰምቶናል። ሳንፈራ እንናገራለን፥ እንጽፋለን፤ ሕዝብ (ከወያኔ በቀር) ከዳር እስከ ዳር እልል ብሏል።
ሁለተኛው ለውጥ ኢሕአዴግ ባወጣው ሕገ መንግሥት አገሪቱ የምትሠቃይበትን ሥርዓት ማቆም ይሆናል። ዶክተር ዐቢይ ይኸን በራሱ ፈቃድ ማድረግ አይችልም፤ ሥልጣኑ የለውም። ሥልጣኑ የፓርላማ ነው። ያሁኑ ፓርላማ ይኸንን ዓይነት ለውጥ ለማምጣት ቢጠየቅ ይስማማ አይስማማ እርግጠኛ አይደለሁም፤ ግን የሚስማማ አይመስለኝም። እንዲያ ከሆነ፥ ዶክተር ዐቢይ ሊያደርግ የሚችለው፥ ቃል በገባልን መሠረት፥ የሚቀጥለውን ምርጫ  ተቀባይነት እንዲኖረው ማድረግ ነው። ይህን ካደረገ፥ ለውጥ ለማምጣት የሚችል ፓርላማ እንድንመርጥ ዕድል እናገኛለን ማለት ነው። ይኸንን ሁለተኛውን ዓይነት ለውጥ የምንፈልግ ሁሉ፥ የማይሆን ጥያቄ መደርደራችንን ትተን፥  ኑ፥  ለውጥ ያመጣሉ የምንላቸውን ተወዳዳሪዎች ለመምረጥ እናሰፍስፍ።
ድዮስጶራ
ኢትዮጵያ የተመለሰው ድዮስጶራ ነገር ግራ የሚያጋባ ሆኖብኛል። ልክ ከትልቅ ጦርነት በድል አድራጊነት የተመለሰ ሆኗል። እርግጥ ብዙዎቹ የተቃውሞ ድምፃቸውን አስሰምተዋል፤ አገር ውስጥ ለሚታገሉ ፓርቲዎች የገንዘብ እርዳታ አድርገዋል። ሬዲዮና ቴለቪዠን አቋቁመው የአገር ውስጡን ተቃውሞ ደግፈዋል፤ አበረታትተዋልም። ትግሉ አገር ውስጥ ነበር ማለት ነው። ታዲያ፥ ይኸ ሁሉ ሆሆታ አገር ውስጥ ሆነው ጠላትን ፊት ለፊት በተዋጉት ጀግኖች ጀግንነት ላይ ጥላ መጣል አይሆንም? “ገንዘብ አለው” የሚባለው ድዮስጶራ ሆቴል ሲገባ ቅናሽ ይደረግለታል!
ከሁሉም የገረመኝ የድዮስጶራውን ጉዳይ የሚያይ መሥሪያ ቤት ይቋቋማል መባሉ አንሶ፥ “ሲቋቋም እኛ የድዮስጶራው አባላት መሳተፍ አለብን” የሚል ጥያቄ መነሣቱ ነው። ድዮስጶራ የሚባል ጎሳ ተፈጠረ ማለት ነው? ከእነዚህ ሰዎች ውስጥ ትምህርት ቤት ያልገቡ ቢኖርባቸውም እሠለጠነ አገር በመኖራቸው ምክንያት በማየትና በመስማት ብዙ ነገር ሳይማሩ አልቀረም። ታዲያ ራሳቸውን ከተማሪ ቤት እንደተመለሱ ቈጥረው ዕውቀታቸውን የሚያካፍሉበትን መሥሪያ ቤት እየፈለጉ፥ ለምን አገራቸውን አይረዱም? በነሱና ከተማሪ ቤት ከተመለሱ ኢትዮጵያውያን መካከል ምን ልዩነት አለ? ምንም።
የኢንጂኔር_ስመኘው_በቀለ_ሞት
መጀመርያ ሰውየው ታላቅ ኢትዮጵያዊ እንደሆነ በሰፊው ተወራ። የምርመራው ውጤት ራሱን የገደለ መሆኑን ሲያመለክት፥ የምርመራውን ውጤት መግለጫ በደምብ ያልተረዳውም የተረዳውም እኩል፥ “እንዴት አንድ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ራሱን ይገድላል?” አሉ። ከዚያም አልፈው፥ ከምርመራው በፊት ሊጠየቅ የሚገባውን ጥያቄ ከምርመራው በኋላ ጠየቁ፤ “መርማሪዎቹ ገለልተኞች መሆን አለባቸው” የሚሉ ተነሡ።ያስገደለው ደብረ ጽዮን ነው ቢባል ግን ይቀበሉት ነበር።
እምነትን ማፍረስ ይቸግራል። ግን ስመ ጥሩው Anthony Michael Bourdain እና እሱን የመሰሉ ሰዎች ራሳቸውን ይገድላሉ ብሎ የሚያስብ ማንም አልነበረም። የሰው ሆዱን የወፍ ወንዱን ሁሉ ሰው አያውቅም። ግን ሁሉ በጁ፥ ሁሉ በደጁ የነበረ Anthony Michael Bourdain  ባለፈው ጁን  8, 2018 ራሱን አጠፋ። ኢንጂኔሩ ለምን ራሱን ገደለ ብሎ መጠየቅ ይቻላል፤ ተገቢም ነው። ለዚህም ጥያቄ ቢሆን መልሱን የሚሰጡን ከመርማሪዎቹ በቀር ሌላ ዐዋቂ እስካሁን አልተገኘም። ከሥራው ጋር የተያያዘ ነገር እንዳለ እንጠረጥራለን፤ ጥርጣሬ ነው። ራሱን የገደለው ለግድቡ ሥራ የተመደበ ገንዘብ ሲዘረፍ ዝም ብሎ አይቶ፥ አሁን ምርመራ የማይቀር መስሎት ከሆነ፥ ራሱን ከመግደል ለመከራከር ቢዘጋጅ ይሻል ነበር። “ባለሥልጣኖች አስገድደውኝ ፈርሜያለሁ” ቢል፥ የቱ ዳኛ “ይሙት በቃ” ይፈርድበት ነበር? በዚያ ላይ ዘመኑ የይቅርታ ዘመን ስለሆነ፥ በይቅርታ ይታለፍ ነበር። ሌላ ምክንያት (የቤተሰብ ጉዳይ) ሊኖርም አይችልም?
እንቆቅልሽ
አንድ ሴት የዓለሙ ሁሉ ሴት ሲደፈር እሷ ብቻ ሳትደፈር የቀረች ይመስል፥ “እኔ አልተነካሁም” እያለች ስትኵራራ ብትሰሙ ምን ትላላችሁ? “ኢትዮጵያ በቅኝ ገዚዎች ያልተገዛች ትልቅ አገር ናት” ማለት ምን ማለት ነው? የአስተሳሰብ ግጭት የለበትም? ሰውየው ኩሩ አባት ነው። ኵራቱ የሚያኰሩ ጨዋ ልጆች ስላሳደገ ነው። ድንገት ከልጆቹ አንዱ በሌብነት ተከሰሰ፤ አባቱ ተከራክሮ ነፃ አወጣው። ከአደባባይ ሲመለሱ፥ ልጁ የሚመሰገን መስሎት ቀደም ቀደም ብሎ ነበር። እቤት ሲደርሱ አባቱ ገረፉት። “ምነው! አባባ፤ ዳኛው ነፃ አውጥቶኝ የለም እንዴ” ቢላቸው፥ “ዱሮውኑ የኔ ልጅ ሆነህ መጠርጠርህስ!” አሉት ይባላል። ታላቋ አገሬ፥ “ሌላ አገር ቅኝ ግዛቴ አላደረግሁም” ብላ ትኵራ እንጂ፥ እንዴት “አልተገዛሁም” ማለት ኵራት ይሆናታል? አገራችንን አናዋርድ።
ኦሮሞዎች፤ ኦሮሞዎች በዓሥራ ስድስተኛው ምእት ዓመት ማህል ኢትዮጵያ ከገቡበር ጊዜ አንሥቶ እስከ እኛ ዘመን ድረስ የመንግሥቱ ሥልጣን ተሳታፊና የተመዘገበው የኢትዮጵያ ታሪክ ሠሪ መሆናቸውን ማንም  የማይረታው መዝገብ አለን። የባለሥልጣን ሰዎችን ስም ዘርዝሩ ብንባል እንዘረዝራለን። ኦሮሞች የኢትዮጵያ ታሪክ ደግ ከሆነ ከመመስገን፥ ክፉም ከሆነ ከመታማት ከሌላው ሕዝብ አይለዩም። ግን ይህ እውነታ የዛሬዎችን ኦሮሞች አያረካቸውም። እንደምገምተው፥ የሚሉት እንዲህ ነው፤
“ታሪኩ እውነት ቢሆንም፥ አባቶቻችን በኢትዮጵያ ታሪክ የተካፈሉት የአማራውን መንግሥት በማገልገል ነው እንጂ፥ እነሱ ባቋቋሙት የኢትዮጵያ መንግሥት አይደለም። የመንግሥቱ ባህል የአማራው ባህል ነው። ኦሮሞዎች በኢትዮጵያ መንግሥት የተካፈሉት የአማራውን፥ የአማራውን ቋንቋ በመናገር፥ የአማራውን ሃይማኖት በመያዝ፥ የአማራውን ባህል ባህላቸው በማድረግ ነው። ምንም እንመን ምን፥ በሃይማኖታችን መኖር፥ በቋንቋችን መናገር እናፍር ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥት ተሳታፊዎች የምንሆነው የኦሮሞ መንግሥት አቋቁመን ነው ባንልም፥ አማሮች በባህላቸው (በሃይማኖታቸው፥ በቋንቋቸው፥ በኪነ ጥበባቸው) የሚኰሩትን ያህል የሚያስኰራን ሁኔታ ሲፈጠር ነው። በኢትዮጵያ ብዙዎች ነን። ብዙነታችን በመንግሥቱ ላይ መንፀባረቅ አለበት።”
ዶክተር ዐቢያ “እኔ ወደ ለውጡ አሸጋግራችኋለሁ” ሲል፥ “ይኸ እውነታ ለብዙዎቻችሁ መራር ስለሆነ፥ እኔ እንዲዋጥላችሁ እረዳችኋለሁ” ማለቱ ይመስለኛል። ይኸው የኦነግ ባንዲራ ሲውለበለብ፥ ውይይት በኦሮምኛም ሲካሄድ ጸጥ ብለን እናያለን፤ እናዳምጣለን። “ተዉ” ለማለት ምን ምክንያት እንሰጣለን? በገዛ አገራቸው፥ “በባህላችሁ አትኑሩ” ልንል አንችልም። ኢትዮጵያዊነትን፥ የዲሞክራሲ አስተዳደርን፥ የኢትዮጵያ የትኛውም ክፍል የሁላችንም  መሆኑን ከተቀበሉ፥ ግዴታችን ያላንዳች ማጕረምረም ሕይወትን በብልጽግና እንድንኖራት የሚያስችል ዘዴ  መፈለግ ብቻ መሆን አለበት። የተማሩት የኦሮሞ ፖለቲከኞች አማርኛ ስለሚያውቁ ንግግራቸው በአማርኛ ቢያደርጉ ብዙ አዳማጭ ያገኙ ነበር። ግን በኦሮምኛ መናገራቸው ማንነታቸውን ለማስረገጥ እንጂ ለመሰማት ብቻ አይደለም።
ብዙ ጊዜ እንደተናገርኩት፥ አንድ ኢትዮጵያዊ ከራሱ ቋንቋ በተጨማሪ የመረጠውን አንድ ሌላ ኢትዮጵያዊ ቋንቋ ቢማር  የበለጠ እንቀራረባለን። ሐሳቡን ሳቀርብ፥ የአብዛኛው ምርጫ ኦሮምኛ እንደሚሆን በመገመት ነው። በአንድ ዘመን በጎንደር ከተማ ኦሮምኛ ይነገር ነበር እያልን ስንተርክ  በአዲስ አበባም ቢደገም ማንም ቅር እንደማይለው በማመን ነው።
ይኸን ሰሞን በኦሮዎች መካክል አንዳንድ ወሮበሎች ወሮበልነታቸውን አሳይተውናል። “ወሮ በላ” ማለት “የሌላ ቤት እየወረረ የሌላ ንብረት የሚቀማ” ማለት ነው።  ወሮበሎቹ በአዲስ አበባ አካባቢ በሚኖሩ ሰላማዊ ሰዎችን ያደረጉት ይኸ ነው። ዘርፈዋል፤ ሕይወትም አጥፍተዋል። ወሮበሎች ወሮበላ ስለሆኑ፥ ሕግ ማክበር የሚሉት ቋንቋ አያውቅም። ስለዚህ፥ እነሱ ፊት  ስለ ሕግ ማክበር መነጋገር በማያውቁት ቋንቋ ማናገር ነው። የሚያዋጣው እነሱ በሚያውቁት ቋንቋ ማነጋገር ነው።
አቶ ለማ መገርሳ እንደነገሩን፥ እነዚህ ወሮበላዎች፣ ኦሮሞዎች በሰፈሩበት አገር ሁሉ ኦሮሞ ያልሆነውን ሊያጠቁ ሲዘጋጁ ተይዘዋል። ይህ የሚሆነው በሕወሐቶች አሻጥር ብቻ አለመሆኑ መታወቅ አለበት። ያም ሆነ ይህ፥ ይህን ዓይነት ጥቃት ለመቋቋም ኢትዮጵያውያን ተዘጋጅተው መገኘት አለባቸው። “አልሞት ባይ ተጋዳይ” ያልሆነ ሰው ለቅሶው ያናድዳል እንጂ አያሳዝንም። ሌባ በመጣ ቍጥር እጅን ሰብስቦ የፖሊስ ያለህ ማለት ፈሪነት ነው። የሥልጣኔ ልዩነትም አለ። የኢትዮጵያ ልጆች ልስልስና ግርድፍ፥ ብስልና ጥሬ፥ ሥልጡንና ኋላ-ቀር፥ ሰብአ ትካትና ዘመናዊ ነን።
ይኸን ክፉ የሽግግር ዘመን አምላክ በሰላም እንዲያሳልፍልን እንጸልያለን። ለውጥ ለማምጣት ለሚጥሩ መሪዎቻችን ብርታቱንና ትግሥቱን ይስጣቸው፤ ጤንነታቸውን ይጠብቅላቸው።
Filed in: Amharic