>

ይድረስ ለኢትዮጵያዊው ሰው ጀዋር መሀመድ!!! (በላይ በቀለ ወያ)

ይድረስ ለኢትዮጵያዊው ሰው ጀዋር መሀመድ!!!
በላይ በቀለ ወያ
.
ጉዳዩ “ገዳዩን” ያመለክታል
“እምዬ ኢትዮጵያ ፣ ሞኝ ነሽ ተላላ”
ሰብሳቢሽ ደብዝዞ ፣ ሚበትንሽ ጎላ!!!”
* “ዘረኞች መሆን ባለብን ጊዜ ፣ በዘራችን ምክንያት ጥቃት የሚያደርሱብን ጊዜ ዘራችንን መዝዘን እንደ ዘረኞች አሰብን! ለዘራችን ወገንን። ለብሔራችን አደላን። 
* ሀገር መሆን ባለብን ጊዜ እንደሀገር እናስባለን። ለሀገር እናደላለን!!! 
* ከዘርና ከሀገር በፊት ግን ሰው ብቻ እንደሆንን እናውቃለን!!!”
 አክቲቪስት ጃዋር መሀመድ ሆይ የደህንነት ትርጉሙ ይገለጥልኝ ዘንዳ አላማህን በግልፅ እንድትገልፅልኝ ስል በኢትዮጵያ ህዝብ ስም ይህን ልልህ እወዳለሁ።
ብዙ ጊዜ ቄሮ ብቻውን ታግሎ ለውጥ ያመጣ ይመሥል በቄሮ ስም ትምክህት ታበዛለህ። ራስህን እንደ ኦሮሞ ህዝብ ፈጣሪ አድርገህ ማየት የጀመርክም ይመሥለኛል። የሆነው ሆኖ በዘር ከፋፍለው ያጠቁን በነበረ ወቅት ዘር መዘህ መታገልህን አልነቅፍም። ነገር ግን ያ ቀን ካለፈ በኋላ አሁንም ዘረኝነት ላይ ነህ።
 ሀውልት እንኳን በእድሳት ምክንያት ከቦታ ቦታ ይንቀሳቀሳል። ምንድነው በነበሩበት ቆሞ መቅረት ? እባክህ ተንቀሳቀስ!!! ብዙ ጊዜ ስለ ሚኒሊክ የኦሮሞን ጡት መቁረጥ  ስታወራ አይሀለሁ። (ባላምንበትም)ነገር ግን በጣሊያን በመርዝ ጋዝ እና በቦንብ ናዳ ኦሮሞ መጨረሱን አንዲትም ቀን ስታወራ አይቼህ አላውቅም።
ለምን? ዘር እንቁጠር ካልን ከጣልያን እና ከሚኒሊክ ማን ነው የበደለን? ማነው የጠቀመን? ማነው ወገናችን?
 ሲሻህ ደሞ “የኦሮሞ ጠላት አማራ ነው” ትላለህ። ሲሻህ “አማራና ኦሮሞ አንድ ናቸው” ትላለህ። እንደፈለክ ትወላውል ዘንድ ማን ነኝ ትላለህ? ከዶክተር አብይ እና ከለማ መገርሳ የበለጠ ለኦሮሞ ህዝብ የታገልከውና የከፈልከው መስዋእት ምንድነው? ውጪ ሀገር ተቀምጦ ለኦሮሞ ህዝብ የታገለና እሳት ውስጥ ተቀምጦ ከታገለው የቱ ነው መሥዋእት የከፈለው? እነሱ ስለ ኢትዮጵያ የሚያወሩት ካንተ የተሻለ ለኦሮሞ ህዝብ ሳይታገሉ ቀርተው ነው ወይ? አማራው “የኦሮሞ ወንድሞቻችን ደም የኛ ደም ነው!” ብሎ በገዳይ ፊት በአደባባይ የተቃወመው ኦሮሞ ስለሆነ ነው ወይ? ኦሮሞው “የአማራ ወንድሞቻችን ደም የኛም ደም ነው!” ብሎ በጠብመንጃ ፊት በአደባባይ የተቃወመው ኦሮሞ ስለሆነ ነው ወይ?
 በጋምቤላ ለተጨፈጨፉት ወገኖች ፣ በሊብያ ለታረዱ ዜጎች ፣ በመላው ኢትዮጵያ በግፍ ለሚገደሉና ለሚታሰሩት የጮኽነው ዘር ለይተን ነው ወይ? ፋኖ ዘርማ ቄሮ እንዲሁም እያንዳንዱ ሰው አልታገለም ወይ? አደዋ ላይ ብዙ ኦሮሞዎች የተዋጉት ለኦሮሞ ብቻ ነው ወይ?
እንደ እስልምና አላህ የፈጠረው ኦሮሞን ብቻ ነው ወይ? እንደክርስትና እምነት ክርስቶስ የተሰቀለው ለኦሮሞ ህዝብ ብቻ ነው ወይ? የኦሮሞ ህዝብ ቢሾፍቱ ሆራ ላይ በግፍ ሲያልቅ ያላለቀሰ ያልጮኸ ፣ያልተቃወመ ብሔር አለ ወይ?
 የአማራው ህዝብ በገፍ ሲረሸን ያላለቀሰ ፣ያልተቃወመ ብሔር አለ ወይ? ከዛም ስናልፍ በበርማና በሶርያ በገፍ ለሚጨፈጨፉ ሰዎች ያቅማችንን አልተቃወምንም ወይ? የብሔር ፖለቲካ አይጠቅምም ብለን አልተቃወምንም ወይ?በሻሸመኔ በቀን በአደባባይ ተዘቅዝቆ ስለ ሞተው ሰው ገዳዮቹን ለማውገዝ ሟቹ ኦሮሞ መሆን አለበት ወይ? በሶማሌ ክልል ተቃጥለው አመድ ለሆኑት ሰዎች ለመቆርቆር ሟቾቹ ኦሮሞ መሆን አለባቸው ወይ? የትኛው ሐይማኖት ነው ሰው በዘሩ ይለያያል ብሎ ያስተማረህ?
 ለሰው ለማዘንና ለመቆርቆር ሰው መሆን በቂ አይደለም ወይ? ታዲያ ምንድነው ሰሞኑን በቡራዩና በተለያዩ አካባቢዎች ሰው ሞተ ብለን ሁላችን እንደሰው ስናዝን “ይህን ያህል ኦሮሞ ሞቷል “የምትለው? እስቲ በሞቱት ሰዎች ደስ ያለው ብሔር ጥራ? አንተ ብቻ ነህ እንዴ ለኦሮሞ ህዝብ ጥቃት የምታዝነው? ሁላችን አላዘንንም እንዴ? እሺ 60 ኦሮሞ ሞቷል ካልክ ስንት አማራ ፣ስንት ትግሬ ?ስንት ወላይታ እንደሞተና እንደተፈናቀለ ንገረን? ሁሉም ወገኖቻችን ናቸው እኮ!!!
ድርጊቱን የፈፀመው ቄሮ ነው የሚሉ ሰዎች ቢበዙም እንኳን ድርጊቱን ቄሮ እንዳልፈፀመው መመሥከር ማረጋገጥ ስትችል ሌላ መጠፋፋት የሚያመጣ ነገር መፈብረክ ለምን አስፈለገ? የኦሮሞ ህዝብስ ከዚህ ተግባርህ ምን የሚጠቀም ይመሥልሃል?
 በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሚያግባቡን ነገሮች ፣
አንድ የሚያደርጉን ውበቶች ፣
የሚያቀራርቡን ማንነቶች እያሉን የሚያራርቁንን ነገሮች ነጥሎ ለህዝቡ ማቅረብ ለምን አስፈለገ?
 ከነ ለማ ቲም የተሻለ ሀሳብ አለኝ ካልክ ለምን ለህዝቡ ግልፅ አታደርገውም? ኢትዮጵያዊነትን መሥበክ ለምን አቃተህ?የኦሮሞ ህዝብ የሌለበት የኢትዮጵያ ታሪክስ የቱ ነው? ብዙ ሀገር አውሮፖ ውስጥ እንደመኖርህና የፖለቲካል ሳይንስ ምሩቅ እንደመሆንህ መጠን እንዴት የአውሮፖውያን ተፅእኖ አላደረብህም? የለውጡ አካል መሆንህ ባይካድም ስለምን የለውጡ ተቃራኒ ሆንክ? ለውጡ አንዲት ኢትዮጵያ ነችና!!! በተረፈ አንድን አሳ ከባህር ውስጥ አውጥቶ “ከመሥመጥ አዳንኩት” ማለት አይቻልም። ጥሩ የፖለቲካ እውቀት አለህ ብዬ አስባለሁ። በአንድ ሰአት ትኩሳት የሚበቃን ሰዎች ነንና። መች እንደምንሞት አናውቅምና ።ትምክህታችንን አሽቀንጥረን ሰብአዊነትን እናስቀድም።  አንዲት ኢትዮጵያን እናንፅ። ያለፈ ጠባሳ እየጠቆምን አዲስ ቁስሎችን አንፍጠር።
ኢትዮጵያዊያን ለኢትዮጵያ ጠላት አይደለንም!!!እርስ በራሳችን እየተባላን የአለም መሳቂያ ሆነን አናውቅም!!! ከመበሻሸቅ ወደ መተራረም እንሸጋገር። ከመሰዳደብ ወደ መገሳፀፅ እንለፍ። ከእኔ ወደ እኛ እንምጣ።
Filed in: Amharic