>
4:42 pm - Thursday January 18, 2920

በትግራይ ነጋዴዎች የተጥለቀለቁት ኤርትራውያኑ "አሁንስ በቃ" ማለት ጀመሩ!! (ዘመድኩን በቀለ)

በትግራይ ነጋዴዎች የተጥለቀለቁት
ኤርትራውያኑ “አሁንስ በቃ” ማለት ጀመሩ!!
ዘመድኩን በቀለ
*  ኤርትራ የትግራይ ነጋዴዎችን ንብረት በይፋ መውረስ መጀመሯ!
* ከአስመራ ወደ ትግራይ የሚገባው ፎርጅድ ብር መጨመሩ!
*  የትግራይ ነጋዴዎች ወደ አስመራ መፍለስና የኤርትራውያኑ በሁኔታው መደናገጥ * መቐለ_አስመራ ! አዲስ ፍቅር ያመናቅር ሆኖባቸዋል
~ ከድንበሩ መከፈት በኋላ የእኛዎቹ የትግራይ ልጆች እንዲያው ግርርርርር ብለው ልክ እንደግሪሳ ወደ ኤርትራ መሮጣቸውን፣ በዚያም አስመራንም ማጥለቅለቃቸው ለኤርትራውያኑ ብዙም የተስማማቸው አይመስልም።
በኢትዮጵያ ውስጥ በተፈጠረው ምቹ ያልሆነ ሁኔታ እንደቀድሞው እንደልባቸው ለመነገድ ያላመቻቸው ትግራዋያኑ በእጃቸው ላይ የሚገኘውን ገንዘብ በመያዝ ከዚህ በፊት ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ ልክ እንደ ስደተኛ ወደ ሀገረ ኤርትራ እየጎረፉ መሆናቸው እየተነገረ ነው። ከኤርትራም እንዲሁ የጤፍ የሲሚንቶና የብረት ሸመታው መጧጧፉ ነው የሚነገረው። ኤርትራውያን የሀገር ልብስ አምሮታቸውን ለመወጣት ማሰፍሰፋቸውና ለሸማኔዎች ምቹ የሆነ ቀን እንደመጣም የሚያስቡ አሉ። ነገር ግን በኢትዮጵያ አሁን የጥበቡ ጌታ እምዬ ዶርዜ ኃዘን ላይ ነው።
ይህ አይነቱ ደራሽ ጎርፍ የመሰለ የትግራውያኑ ነጋዴዎች ወደ ኤርትራ መትመም የተከሰተው ደግሞ የኢትዮጵያው ጠሚዶኮ ዐቢይ አህመድና የኤርትራው ፕሬዘዳንት አይተ ኢሳይያስ አፈወርቂ ህዝቦቻቸውንም ሆነ ፓርላማዎቻቸውን ሳያማክሩ [ ኢሱ እንኳን ፓርላማ የላቸውም ፓርላማው ራሳቸው ናቸው ] ባደረጉትና እስከአሁንም ለህዝቦቻቸውም ሆነ ለታዛቢ ሀገራት ምስጢራዊ በተደረገ ስምምነት ምክንያት በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረውና ለረጅም ዓመታት ተዘግቶ የነበረው ድንበር ከተከፈተ በኋላ መሆኑ ነው።
የንግድ ልውውጡ ለጊዜው መልካም ቢመስልም ነገር ግን የንግድ ልውውጡ በሕግ ማዕቀፍ ያልታገዘና የአንድ የኤርትራ ናቅፋ ከአንድ ከኢትዮጵያ ብር ጋር መሳ ለመሳ መመንዘርም ለብዙዎች ታዛቢዎች እንዳልተዋጠላቸው እየተሰማ ነው። በኤርትራ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ14 የኤርትራ ናቅፋ መቀየሩን ያዩና በኢትዮጵያ ደግሞ አንድ ዶላር በ28 የኢትዮጵያ ብር መመንዘሩን እያነሱና እያጣቀሱ ይሄ ነገር ከአሁኑ ሕጋዊ ገደብ ካልተበጀለት በቀር ኋላ ላይ ውሎ ሲያድር ልክ የ1990 ዓመተ ምህረቱን ዓይነት አሰከፊ ጦርነት በሁለቱ ሀገራት መካከል አንዳይቀሰቅስ ሲሉ ስጋታቸውንም ያስቀምጣሉ።
የዚያን ጊዜውም ጦርነት መነሻ ምክንያቱ የድንበር ክርክርና ጠብ ሳይሆን የፈረንጅ ላሟን ኢትዮጵያችንን ለመጋጥ ሲሉ ሁለቱ የበረሃ ጓዶች የፈጠሩት ከሕጋዊ መስመር ውጪ ያፈነገጠ ግኑኝነት ነው የሚሉም አሉ ] ። አሁንም ምጥንቓቕ ።
ሰሞኑን በዛ ያሉ መኪኖች ከመቐለ ጭነው ለንግድ ወደ አስመራ ይዘው የሄዱትን የብረት፣ የጣውላና የቆርቆሮ ምርቶች የኤርትራ የህንፃና ቤቶች ሚንስቴር መውረሱንም መረጃዎች ያመለክታሉ። [ “ሚንስትሪ ህንፃ ሃገረ ኤርትራ ነቲ ነጋዶ ካብ ትግራይ ዘእተውዎ # ቴንዲኖ ፣ # ስሚንቶ # ጣውላካብ ዘዝፀዓንዎ ገፊፉዎም ኣሎ፡፡”]
በማለትም ነው ዜናው የተሠራው። ከዚህ ጋር ተያይዞም በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ፎርጅድ የኢትዮጵያ ብሮች መነሻቸውን ከአስመራ አድርገው መቐለ ትግራይ ላይ እየተበተኑ ነውም ተብሏል። ይሄም ከዚያው ከትግራይ የተገኘ መረጃ ነው።
ሰሞኑን ደግሞ ከኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ ለመግባት የሚተራመሰውን ህዝብ ለማቆም ሲባል ኤርትራ ከምሽቱ 12 ሰዓት በኋላ ድንበሯን መዝጋቷም ተነግሯል። ለዚህ የተሰጠው ምክንያት ደግሞ በሌሊቱ ጉዞ በኤርትራ ምድር የመኪና አደጋ እየጨመረ በመምጣቱ ነው የሚል ምክንያትም ተሰጥቷል።
ምክንያቱ ግን ምክንያት አይመስልም። ሌላው ደግሞ የኤርትራ ፕሬስ በመባል የሚታወቀው የኤርትራውያኑ ገጽ ከትግራይ ወደ ኤርትራ የሚፈልሰውን የነጋዴ ማዕበል ካየ በኋላ እንዲህ ሲሉ ስጋቱን አስቀምጧል።Enough Is Enough – Someone has to do something to control this madness. – Where are our leaders when we need an explanation? – “Abrahaley, Aytered’anin.”
 ትርጉም ! በራሴ በገባኝ መጠን። ” አሁንስ በቃ ” ወይም በቃ ማለት በቃ ነው። ! [ ሆሆይ አልበዛም እንዴ? ] አይነት ቃና ያለው ትርጉም ነው የሚሰጠን።
– አንድ ሰው ይሄንን እብደት ለመቆጣጠር የሆነ ነገር ማድረግ አለበት።
– ማብራሪያ ሲያስፈልገን መሪዎቻችን የት ነው ያሉት?
– “አብርሃሌ አይትረድአኒን ” በማለት እሪታውን አቅልጧል።
ለማንኛውም ኋላ ላይ ማጠፊያው እንዳያጥር ሁሉ ነገር በሕግ አግባብ ይሁን እላለሁ። ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግኑኝነት በዶላር እንዲሆን ብትፈልግም የትግራይ ምስኪን ገበሬ ከየት ያመጣዋል? ዶላሩ ያለው ጥቂቶች እጅ ነው። የቸገረ ነገር ሆነ እኮ። አንድ ህዝብ ለሁለት መክፈልና መለያየት ችግሩ እዚህ ላይ ነው። እትዬ አልጋነሽ ከትግራይ እህታቸውን እትዬ ትርሃስን ኤርትራ ሄደው ለመጠየቅ ዶላር የግድ ያስፈልጋቸዋል። ቪዛው ቢቀር ዶላሩ ግን የግድ ነው የሚሉ አሉ። ~ ለማንኛውም ሁለታችሁም ተረጋጉ ። ረጋ ፣ ቀስ በሉ።
Filed in: Amharic