>
4:17 pm - Thursday May 19, 2022

የሐዋሳው ቀይ መስመር (ሀብታሙ አያሌው)

የሐዋሳው ቀይ መስመር
ሀብታሙ አያሌው
የሐዋሳውን የኢህአዴግ ጉባዔ በተመለከተ መግለጫ የሰጡት የጉባዔው ቃል አቀባይ አቶ ፍቃዱ ተሰማ “አብረው መጓዝ ያልቻሉ የግንባሩ አባል ድርጅቶች እና መፈፀም ያልቻሉ አመራሮች ቀይ መስመር ተሰምሮላቸዋል”  ሲሉ በኢህአዴግ ቤት የተለመደውን ቋንቋ በመጠቀም በጉባዔው የተፈጠረውን ከባድ የስልጣን ሽኩቻ የሚያመላክት ቃል ጠቆም አድርገው ብቻ  አልፈዋል።  የውስጥ መረጃ እንደሚያመለክተው ጉባዔው የገጠመው የስልጣን ግብ ግብ እዚያው በኢህአዴግ ቤት ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን መዘዙ ለአገር የሚተርፍ አደጋ ነው።
ጉዳዩ ብርቱ ጥንቃቄ ይፈልጋል። በዚህ ወቅት የለውጥ ኃይሉን እንደ ቲም አጠናክሮ ከመቀጠል በቀር አማራጭ የለም።  መፈፀም ላልቻለ አመራር  ቀይ መስመር የሚለው ቃል ከኢህአዴግ አሰራርና ደንብ አንፃር ሲታይ በእጅጉ ግራ አጋቢ ነው። ጉባዔው የአፈፃፀም ሪፖርት መርምሮ ከማፅደቅ እና የቀጣዩን ሁለት አመት እቅድ እና አቅጣጫ ከማስቀመጥ በቀር  በርዕዬት ዓለም፣ በአርማ፣ በስያሜ እና ሌሎች ወሳኝ የፊደራሉ ስርዓት ማሻሻያ ፣ ከኢኮኖሚ ቀውሱ መውጣት የሚያስችል የፖሊሲ ማሻሻያ ሃሳብም ሆነ አቅጣጫ ላይ ውይይት እንደማይደረግ ተገልጿል።
በነዚህ ነጥቦች ላይ እስካልተወያየ ደግሞ አባል ድርጅቶች መሃል ቀይ መስመር ጫፍ የሚያደርስ ምንም አይነት ምክንያት የለም። በሌላ በኩል መፈፀም ለማይችል አመራር ብሎ ያነሳው ቀይ መስመርም ቢሆን መፈፀም ያልቻለን አመራር ቀይ መስጠት የግምባሩ አባል የድርጅቶች እንጂ የኢህአዴግ ጉባዔ ስልጣን አይደለም። ሌላው ቀርቶ ሊቀመንበር እና ምክትል እንኳን የሚመረጡት በምክር ቤት እንጂ በጉባዔው  አይደለም።  ስለዚህ የጉባኤው ቃል አቀባይ  አቶ ፈቃዱ ተሰማ መፈፀም ለማይችል አመራር ገባዔው ቀይ ይሰጣል ያሉትም ትርጉም አልባ ነው። ምናልባት  በምክር  ቤቱ ስለሚመረጡት ሁለቱ ለዎች ሊቀመንበርና ምክትል ማለትም ዶክተር አብይ አህመድ እና አቶ ደመቀ መኮንን ሊያወሩን ፈልገው ከሆነ እና አቶ ደመቀ መኮንን ከስልጣን እንዲወገዱ እየተደረገ ላለው የሴራ ዘመቻ ሽፋን እየሰጡ ከሆነም በእሳት እንደመጫወት የሚቆጠር ይመስለኛል።
በጥቅሉ የለውጥ ሃይሉን ሳይነካኩ አጠናክረው ከማስቀጠል በቀር ሌላው ሙከራ እንደ አገር ከባድ  ዋጋ እንደሚያስከፍል መገንዘብ ያስፈልጋል።   በሌላ በኩል የጉባዔው ይዘት ሲገመገም ቀይ መስመር ደረጃ የሚያደርስ ምንም ጉዳይ የለውም። አንዳንዶች ይህ ጉባዔ አገሪቷን አሁን ካለችበት አጣብቂኝ የሚያወጣ ወሳኝ ውሳኔ ይኖራል የሚል ግምት ይዘን የነበረ ቢሆንም የኢህአዴግ ጉባዔ አዴፓ (ብአዴን)  በጉባዔው አንስቶ አቅጣጫ ለማስቀመጥ በደፈረው ልክ መራመድ እንኳን ተስኖት ተሽመድምዷል።
ለምሳሌ አዴፓ በጉባኤው ያነሳቸውን  ነጥቦች ብናይ 
1.  የፌደራል ስርዓቱ አከላለል የአገሪቱ መሰረታዊ ችግር
      ዋና ምንጭ መሆኑን ተቀብሎ መታረም እንደሚገባው
       ፅኑ አቋም መያዝ ችሏል።
2. አብዬታዊ ዴሞክራሲ የተሰኘው የኢህአዴግ ፕሮግራም
     ሊለወጥ እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጧል።
3. የዜጎች መብት በማንኛውም መንገድ እንዲከበር
     የማንነት ጥያቄ በተሟላ ሁኔታ እንዲመለስ መታገል ቀዳሚ አጀንዳው መሆኑን አስምሮበታል።
4. ለሱዳን ተላልፎ የተሰጠው መሬት እንዲመለስ ሉዓላዊ ግዛት እንዲከበር በቁርጥ እንደሚታገል አሳውቋል።
5. አዲስ አበባ የማንኛውም ብሔር ሳትሆን የአዲስ አበባ ህዝብ መሆኗ ታውቆ እንዲከበር እንደሚታገል ገልጿል።
ኦዴፓ ኦህዴድ በበኩሉ
 
1. በጨቋኝ ተጨቋኝ የብሔር ፖለቲካ ትርክት ላይ  የተመሰረተውን የአብዬታዊ ዴሞክራሲ መሰረት
      እንደማይቀበለው በግልፅ አሳውቋል።
2. ከኢትዬጵያዊነት በመጥበብ ሳይሆን በአፍሪካ እና   በቀጠናው ተፅኖ ፈጣሪ ሆኖ በመውጣት ከፍ ላለ ሃሳብ እንደሚሰራ በመግለፅ የብሔርተኝነትን አደጋ እንደሚታገለው አሳውቋል።
ደህዴን በበኩሉ ሁለቱ የግንባሩ አባላት አዴፓ እና ኦዴፓ እያራመዱት የሚገኘው የለውጥ ጉዞ ሊቀለበስ የማይገባው ብቸኛ የመዳኛ መንገድ ነው ሲል ድምዳሜ ላይ ደርሶ በሊቀመንበሯ በወይዘሮ ሞፎርያት ካሚል በኩል ” ህዝቡ ንግግራችንን ጠግቧል  አሁን በተግባር ውጤት ይጠብቃል” የሚል ድርጅቱ የለውጥ ሂደቱ ወሳኝ አካል መሆኑን አሳውቋል።
ከዚህ የተለየ መንገድ መርጦ በአሮጌው ፖለቲካ ተቸክሎ የቀረው የፓርቲ ርዕዬት ዓለም፣ ህገ ደምብ፣ የአሰራር ስርዓትና የህግ ማዕቀፎች አንድ ፊደል አይነኩብኝ እያለ ያለው ህወሓት ብቻ ነው።
በእኔ እምነት የዶክተር አብይ አመራር  ይህንን ምቹ አጋጣሚ ተጠቅሞ የአገሪቷን ችግር ከስሩ የሚፈታ እንደቃላቸው የኢትዮጵያን መፃዒ እድል የሚወስኑ ቁልፍ ውሳኔዎች እንዲተላለፉ በማድረግ ሊጠቀሙበት የሚገባውን ይህንን ጉባዔ  ሊጠቀሙበት ባለመቻላቸው፣  የጉባዔው አጀንዳ በስልጣን ግብግብ ላይ ብቻ ተወስኗል።
የስልጣን ግብ ግቡ በጥሩ ደረጃ የተገነባውን የለውጥ ኃይል መተማመን እና አብሮነቱ ለአደጋ እንዲያጋልጥ  ለውጥ ቀልባሹ የህወሓት ቡድን ሆን ብሎ በአቶ ደመቀ ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ በመክፈት፣ አክራሪ ብሔርተኛ የሆኑ አንዳንድ የኦዴፓ እና የደህዴን አባላትን ተጠቅመው የጉባዔ ተሳታፊችን በመቀስቀስ የሚዲያ ዘመቻ በመክፈት እርብርባቸውን ቀጥለዋል።
ለውጥ ቀልባሹ ቡድን አቶ ደመቀ ላይ ያነጣጠረው በግለሰብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በጥቅሉ “አማራ ከስልጣን ሊገለል ይገባል አዴፓ በጉባዔ የያዘው አቋም ክልሉ ጉልበት እንዲፈጥር የሚረዳው ስለሆነ የነፍጠኛው ስርዓት ሊውጠን ይችላል”  የሚል አሳፋሪ ዘመቻ መሆኑ የሁኔታውን ከባድነት ከፍ አድርጎት ቆይቷል።  ህወሓትን የወልቃይት እና የራያ ጥያቄ እረፍት ሲነሳው አክራሪ ኦዴፓዎች ደግሞ አዲስ አበባ የአዲስ አበቤው ህዝብ ናት የሚለውን አቋም ለመቀስቀሻ እየተጠቀሙበት ቆይተዋል።
አሁን ያለው መረጃ እንደሚያመለክተው በከፍተኛው የለውጥ አመራር በቲም ለማ መካከል ላለፉት ሁለት ቀናት የታየው ውጥረት ወደ ቀድሞው መናበብ እና መደማመጥ መመለሱን ያረጋግጣል። ይሁን እንጂ ዛሬ አርብ  ከሰዓት በኋላ በሚደረገው ምርጫ የለውጥ ሃይሉ እንደ ቲም እንዳይቀጥል የሚሰራው አፍራሽ ቡድን ተሳክቶለት አቶ ደመቀን ከሃላፊነት በማግለል የቀይ መስመሩ ሰለባ በማድረግ ከተጠናቀቀ ቲም ለማ የሚለው ስም ማክተሚያው የለውጥ አመራር የሚለው አጠራርና ስያሜም ወደ ቀውስ አመራር ያመራል። ይህ አንዳይከሰት የጉባዔው አባላትን የሚያስጠነቅቅ ጫና መፍጠር የሁሉንም አገር ወዳድ ዜጋ እርብርብ ይጠይቃል።
ቸር ያሰማን
Filed in: Amharic