>

የአብይ መንግስት ከምላስ እና ጆሮ ዘመን  ወደ ቀንድና ጥርስ ዘመን በሽግግር ላይ!!! (መሳይ መኮንን)

የአብይ መንግስት ከምላስ እና ጆሮ ዘመን
 ወደ ቀንድና ጥርስ ዘመን በሽግግር ላይ!!!
መሳይ መኮንን
 
* ይህን ያህል ቅቡልነት ካገኘ የአብይ መንግስት ከእንግዲህ ጎፈር ብቻ ሳይሆን ጥርስም ያለው አምበሳ ሆኖ ብቅ ሊል ጊዜው ነው!
ውጤቱ ታውቋል። ከየአባል ድርጅቶቹ የተወከሉ 45 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በድምር 180 ሰዎች ድምጽ የሚሰጡበት ስነስርዓት ተጠናቆ ውጤቱ ተገልጿል። 3 ሰዎች ሲቀሩ 177 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ድምጽ ሰጥተዋል። ከሶስቱ አንደኛው አቶጌታቸው አሰፋ መሆናቸው ይገመታል። ለማንኛው ከ177 ድምጽ ዶ/ር አብይ የ176ቱን ድምጽ በማግኘት የግንባሩ ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል። አቶ ደመቀ መኮንን የ149ኙን ድምፅ አግኘተው በም/ል ሊቀመንበርነት ይቀጥላሉ።
ህወሀቶች ተደምረዋል ማለት ነው። ድምጻቸውን ለዶ/ር አብይ ይነፍጋሉ ሲባል በሙሉ መስጠታቸው አስገራሚ ነው። ሌላው ቀርቶ ቂም ለያዙባቸው ለአቶ ደመቀ መኮንን አንዲት የህወሀት ድምጽ ትደመራለች የሚል ግምት አልነበረም። ሆኖም አቶ ደመቀ ከህወሀቶችም የተወሰኑ ድምጾችን ማግኘታቸውን ከስሌቱ መገንዘብ ይቻላል። ህወሀት ውስጥ የለውጥ ሃይል ቦታውን እየተቆጣጠረ መጣ ወይስ ሌላ ምርጫ ስላልነበራቸው? የሆነ ሆኖ የዶ/ር አብይ መንግስት በዚህ መልኩ የግንባሩን ሙሉ የሆነ ድጋፍ ማግኘቱ መሰረታዊ ለውጦችን ለማምጣት አቅምና ጉልበት የሚሰጠው ነው። የህግ የበላይነትን ከማስከበር አንስቶ ዋና ዋና የዲሞክራሲ ተቋማትን የመገንባቱ የቤት ስራን ለማከናወን እንዲህ ዓይነቱ ሙሉ ድጋፍ ወሳኝ ነው።
ከጉባዔው አንድም የጠበኩት ዶ/ር አብይ በኢህአዴግ ውስጥ ጠንካራ አቅምና ትርጉም ያለው ድጋፍ የሚያገኙበት ይሆናል የሚል ነበር። ይህ ድርጅታዊ ቅቡልነት መንግስታቸው ጥርስ ያለው እንዲሆን ያደርገዋል። በሀገሪቱ በየትኛውም ክፍል ህግና ስርዓትን ለማስከበር ሙሉ ስልጣን እንዲኖረው ያስችለዋል። እንግዲህ ከጠበኩት በላይ ዶ/ር አብይና አቶ ደመቀ በኢህ አዴግ ውስጥ ፍጹም የበላይነትን የተቀዳጁበት ጉባዔ ሆኖ ተጠናቋል። ከዚህ በኋላ ሀገር የማረጋጋትና የተቋማት ግንባታ ጅማሬዎችን የምናይበት መንግስት እንደሚሆን እንጠብቃለን። ህወሀትም ከእንግዲህ የጥፋት ሃይል ከመሆን ተቆጥቦ በለውጡ ውስጥ አወንታዊ ሚና ይጫወታል የሚል ግምት አለኝ። ዶ/ር አብይ ከእንግዲህ ለየትኛውም ስርዓት አልበኝነትም ሆነ መንግስታቸውን ለሚፈታተን ተግባር ክፍተት የሚሰጡ እንደማይሆኑ አምናለሁ።
Filed in: Amharic